Articles,  Blog,  የቀዳሚው ኪዳን ነገረ-መለኮት,  የብሉይ ኪዳን ሐቲት

ባሪያዬ ይከብራል ከፍ ከፍም ይላል

“እነሆ፥ ባሪያዬ በማስተዋል ያደርጋል፤ ይከብራል ከፍ ከፍም ይላል፥ እጅግ ታላቅም ይሆናል።” (ኢሳያስ 52:13)

አብዛኛውን ጊዜ ስለ ጌታ ባሪያ ሥቃይና መከራ ስናስብ የምንጠቅሰው ኢሳ 53:1-12 ነው። ሆኖም ግን ኢሳ 53 መጀመር የነበረበት በ53:1 ላይ ሳይሆን 52:13 ላይ ነበር። ይህን ማስተዋል ምን ፋይዳ አለው? ፋይዳው፣ በብሉይ ኪዳን ላይ ስለ ክርስቶስ ትንሳኤና ዕርገት በግልጽ ፍርጥ አድርገው ከሚናገሩ ጥቂት ክፍሎች መካከል (ከመዝ 110:1 ቀጥሎ) አንዱ ኢሳ 52:13 በመሆኑ ነው። ይህ ጥቅስ የአራተኛውና የመጨረሻው የጌታ ባሪያ መዝሙር (42:1-4; 49:1-6; 50:4-7; 52:13-53:12) የመጀመሪያ ስንኝ ነው። የዚህ አራተኛ መዝሙር (ኢሳ 52:13 – 53:12) የመጀመሪያውና የመጨረሻው ስንኝ፤ በከፍታ-ውርደት ጀምሮ በውርደት-በከፍታ ይደመድማል። ይህንን ቁልፍ ዕሳቤ ኢሳ 53:1 ላይ ከጀመርን አናስተውለውም።

  • የባሪያው መከናወን፡ ከፍታ ከውርደቱ በኋላ (52:13-15)
  • የባሪያው ሥቃይ (53:1-9)
  • የባሪያው መከናወን፡ ከፍታ ከሥቃዩ በኋላ (53:10-12)

ይህ ክፍል እንደሚያስረዳን፣ መዝሙሩ የሚጀምረው በባሪያው መከናወን፣ መክበርና ከፍ ከፍ በማለት ነው። ይህ ከዚህ በፊት ለነበረው (51:17-52:12) “ተነሺ-ተነሺ” ለሚለው ክፍል፣ ይኽም የሕዝቡን መከራ በመሸከም ያስገኛቸው በረከቶች (ከዚህ ቀደም ልጠፋዬ ላይ በሰፊው እንዳተትሁ) እንደሆኑ ያስረዳናል።

ሆኖም ምዕራፉ 53:1 ላይ በመጀመሩ፣ የባሪያውን ከፍታ (52:13-15) ከባሪያው ሥቃይና መከራ (53:1-9) ሳናውቅ እንድንነጥለው ያደርገናል። ቁጥሮችና ምዕራፎች ጠቃሚ እንደሆኑ ሁሉ አንዳንዴም እክል የሚሆኑብን ጊዜያት አሉ። በመጽሐፍ ቅዱሳችን ላይ የምናያቸው የምዕራፍ ክፍፍሎች ያስቀመጠልን በ13ኛው ክፍለ ዘመን የካንትቤሪ ሊቀ-ጳጳስ የነበረው እስጢፋኖስ ላንግተን (Stephen Langton) ነበር። አከፋፈሉ እጅግ ሊደነቅ ያስፈልጋል። አብዛኛውን ጊዜ ትክክል ነው። ሆኖም ግን ደግሞ አልፎ አልፎ በጣም ወሳኝ በሆኑ ምንባባት ላይ የምዕራፍ አከፋፈል ሲሳሳት ግን ይከዳናል። ከነዚህ መካከል፣ ከላይ እንዳየነው፣ ኢሳያስ 53 ነው።

  • የባሪያው መከናወን፡ ከፍታ ከውርደቱ በኋላ (52:13-15)
    • የባሪያው ውርደትና ሥቃይ (53:1-3)
      • የባሪያው-መከራ መልዕክትና
        የአድማጩ የተሳሳተ ድምዳሜ (1-3)
      • የባሪያው ስርኤታዊ መከራና
        የመከራው ምክኒያት ሲብራራ (4-6)
    • የጻድቁ ባሪያ መከራው ለሌሎች ስለ መሆኑና
      የባሪያው ፈቃደኝነት (7-9)
  • የባሪያው መከናወን፡ የጌታ ባሪያ ከፍታ ከሥቃዩ በኋላ (53:10-12)

► “ባሪያዬ ይከብራል ከፍ ከፍም ይላል፥ እጅግ ታላቅም ይሆናል”

ኢሳያስ በዚህ በአራተኛው መዝሙር ላይ ስለ ባሪያው ከፍታና መክበር መጀመሩ፣ ስለ ባሪያው ሥራ መከናወንና ስለ ማንነቱ አድምቆና አስምሮ ሊናገር ፈልጎ ነው። በዚህ ክፍል ውስጥ ባሪያው ከመከራ በኋላ ሦስት ነገሮች እንደ ሚጠብቁት ይነግረናል፦ (1) ይከብራል፣ (2) ከፍ ከፍ ይላል፣ (2) እጅግ ታላቅ ይሆናል። በተለይ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ቃሎች በጥምረት በዚሁ በኢሳያስ ላይ ለያህዌህ ጥቅም ላይ ውለዋል።

ኢሳ 52:13 – “እነሆ፥ ባሪያዬ…”ይከብራል ከፍ ከፍም” (ያሩም ቨ ናሳ) ይላል”
ኢሳ 6:1 – “ንጉሥ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን “ከፍ ባለና በከበረ” (ራም ቨ ኒሳ) ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት”
ኢሳ 57:15 – “ለዘላለም የሚኖር ስሙም ቅዱስ የሆነ፥ “ከፍ ያለው ልዑል” (ራም ቨ ኒሳ) እንዲህ ይላል”

በ6:1 ላይ እና በ57:15 ላይ የእነዚህ ሁለት ግሦች ባለቤት “ከፍ ከፍ” ያለው እና “የከበረው” ያህዌህ ብቻውን ንጉስ ሆኖ የተቀመጠበት ልዕልና ነው። ይህ ልዕልና ሁሉን አስተዳዳሪ የሆነው መለኮታዊ ዙፋኑ ነው። በዚህ አውዳዊ አጠቃቀም ሥር ታዲያ፣ ለያህዌህ በተነገረበት አገላለጽ ባሪያውም ከመከራው በኋላ ስለ ሚያገኘው ከበሬታ ሲናገር “ከፍ ከፍ – ይከብራል” ይላል። ባሪያው ከሞተና ከተቀበረ በኋላ (53:9) “ከፍ ከፍ” ብሎ ይከብራል (52:13; 53:12)። ይህም ከመከራው በኋላ ያህዌህ ወዳለበት ልዕልና ይወጣል። ከዚህ የተነሳ በዮሐ 12፡28-41 ላይ፣ ዮሐንስ ከኢሳ 53:1 ጠቅሶ ካበቃ በኋላ፣ ኢሳ 6፡10ን በመደረብ የተናገረው፣ ይህ እይታ ትክክል እንደሆነ ያስረግጥልናል። ዮሐንስ እንዲህ ይላል፦

“ኢሳይያስ ይህን ያለው የኢየሱስን ክብር ስላየ ነው፤ ስለ እርሱም ተናገረ።”

በኢሳ 6:1 ላይ ኢሳያስ የተመለከተው የያህዌህን የክብር ልዕልና ከሆነና በኢሳ 52:13 ላይ ባሪያው በዚሁ የክብር ለዕልና ከተገለጸ፣ ኢየሱስም የኢሳያሱ መጽሐፍ ባሪያ ከሆነ፣ ኢሳያስ ያየው “የኢየሱስን ክብር” ነው። የዮሐንስ ሎጂኩ እንዲህ ይመስላል።

ይህ መሰረታዊ ነገረ መለኮታዊ ድምዳሜ፣ “ከመከራው በኋላ ባሪያው ወደ ያህዌህ ምጡቅ ዙፋን ማረጉ” በአዲስ ኪዳን ላይ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ነገረ-ክርስቶሳዊ አስተምህሮ መነሻ ነው። ኢየሱስ ከመስቀሉ ስቃይ በኋላ በአብ ዙፋን ላይ መቀመጡ፣ ወደ ነበረበት ክብር መመለሱ ነው። ይህም የሆነው በትንሳዔውና በዕርገቱ አማካኝነት ነው። ኢየሱስ ከሙታን መካከል ባይነሳ እና ወደ አብ ዙፋን ከፍ ብሎ በቀኙ ባይቀመጥ ኖሮ፣ የመስቀሉ መከራ ከሌሎች መከራዎች ባልተለየ ነበር። ከበሬታው ለሥርኤታዊ ሥራው ማኅተም ነው። ይህ ከበሬታ ስለ ኢየሱስ ሥራና ማንነት ይናገራል።

ለኤማሁስ መንገደኞች፦ ክርስቶስ ከመከራው በኋላ ወደ ክብሩ ገብቷል

“እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የማታስተውሉ ሰዎች፣ ልባችሁም ነቢያት
የተናገሩትን ሁሉ ከማመን የዘገየ፣ ክርስቶስ ይህን መከራ መቀበልና ወደ ክብሩም
መግባት አይገባውምን?” ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ በቅዱሳት መጻሕፍት ስለ
እርሱ የተጻፈውን አስረዳቸው” (ሉቃ 24:25–27)

ጌታችን ኢየሱስ ስለ ራሱ የነበረው ግንዛቤ ከመከራው በኋላ ወደ ክብሩ “በትንሳኤውና በዕርገቱ” አማካኝነት ወደ ክብሩ መመለሱ ነው። ለዚህም ኢሳ 53:12 ቁልፍ ክፍል ነው።

በተጨማሪም ጳውሎስ ኢሳ 53:12ን፣ ይህንን የውርደት-ከበሬታ ዕሳቤ፣ በፊልጵስዩስ 2:9 እንዴት ከክርስቶስ ሥራና ማንነት ጋር እንዳዛመደ እንመልከት፦

“እነሆ ባሪያዬ ይከብራል ከፍ ከፍም (ὑψωθήσεται) ይላል፥ እጅግ ታላቅም ይሆናል” (52:13)

“ስለዚህ [ከከፍታ-ወርዶ-መከራን ስለተቀበለ] እግዚአብሔር እጅግ ከፍ አደረገው (ὑπερύψωσεν)፤ ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጠው” (ፊል 2:9)

ከመከራው በኋላ ጌታችንን አብ እጅግ አከበረው። እንዴት? በትንሳኤውና በዕርገቱ አማካኝነት እግዚአብሔር “አከበረው” ወደ ሰማያዊ ልዕልና በዙፋኑ ቀኝ አስቀመጠው። አከበረው። እንዴት? ከስም ሁለ በላይ የሆነውን “ጌታ (ያህዌህ)” በሚለው ስም እንድንሰይመው አደረገ። ይህም ጉልበት ያለው ሁሉ ለአብ እንደሚበረከክ፣ በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ፣ ራሱን በማዋረዱ ለኢየሱስም ይንበረከክ ዘንድ ነው።

ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣምና፥ ነገር ግን እርሱ። ‘ጌታ ጌታዬን። ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው’ አለ። እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ። (ሐዋ. 2:34–36)

ሃሌ ሉያ! እነሆ ለሞተውና ለተነሳው ለምድርና ለሰማይ ጌታ ለኢየሱስ ክብር ይሁን!

One Comment

  • grum saved

    For the grace of God that bringeth salvation hath appeared to all men,
    12 Teaching us that, denying ungodliness and worldly lusts, we should live soberly, righteously, and godly, in this present world;
    13 Looking for that blessed hope, and the glorious appearing of the great God and our Saviour Jesus Christ;

    ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤
    12 –
    13 ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤
    ሳሚ ተባርከሃል!

Leave a Reply

Your email address will not be published.