Home / Portfolio / WOG / (05) ምጡቅ እግዚአብሔርና ቃሉ (Audio)

(05) ምጡቅ እግዚአብሔርና ቃሉ (Audio)

Posted on

የማጥኛ ጽሑፍ: የዚህን ጥናት ማብራሪያ ጹሑፍ ለማግኘት እዚህ ይጫኑ

“እግዚአብሔር ከመታወቅ በላይ የመጠቅ አምላክ ነው (Ps. 145:3፤ Ps.139:6; 139:17; ሮሜ. 11:33)”

“ራሱን በልጁ በሙላት የገለጠ አምላክ በመሆኑ እግዚአብሔርን እናውቀዋለን (ኤር. 9:23–24; ዮሐ. 17:3; 14:23; 1ዮሐ. 5:20; 1 ዮሐ. 2:3; 1 ዮሐ. 4:8; ገላ. 4:9; ፊል. 3:10)”

እነዚህ ሁለቱ አረፍተ ነገሮች የሚጋጩ ይመስላሉ።በርግጥ የምናመልከው እግዚአብሔር ባይሆን ኖሮ፤ ህጸጸኛ በሆኑ ነበር። ሆኖም ግን ክርስትንና ከሌሎች እምነቶች እንዲለይ ያደረጉ እውነቶች ናቸው። ስለ እግዚአብሔር አምላካችን ስንነጋገር፤ ይህንን አምላክ ከሌሎች የለዩ እንደ ምሶሶ የሆኑ ሦስት እውነታዎች አሉ። (1)፡እግዚአብሔር ምጡቅ ነው (Transcendent) (2) እግዚአብሔር ሉዓላዊ ነው (Sovereign) (3) እግዚአብሔር ሕያው ሕላዌ (Personal) ነው።

የእግዚአብሔር ምጡቅነትና የበላይነት

ፍጡር ፈጣሪን በመዳፉ አይቆጣጠረውም። በፍጡርና በፈጣሪ መካከል ልዩነት አለ። ፍጡር ፈጣሪ አይሆንም። በፈጣሪም መደብ አይቀመጥም። እርሱ ከሁሉም የተለየ አምላክ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን እውነት ለማንጸባረቅ “ቅዱስ” የሚለውን ቃል ይጠቀማል። ቅዱስ የሚለው ቃል በመጀመሪያ ደረጃ የሚያሳየን የእግዚአብሔርን ፍጹም ልዩነት ነው። ይህም ስሙ ያህዌህ የተባለ አንድ አምላክ/ኤሎሒም አለ። ለእኛ አንድ ብቻ ጸሐይ እንዳለችን ሁሉ፤ እርሷንም ማንም መጠጋት እንደማንችል፤ እግዚአብሔርም ማንም ሊቀርበው የማይችል አንድ ብቻውን አምላክ ነው። ከእርሱ ሌላ አምላክ የለም። ከእርሱ ሌላ መድሃኒት አያቅም። ፍጡር ሁሉ ጅማሬና ፍጻሜ አለው። ለህላዌነቱ መጀመሪያ ውል አለው። እግዚአብሔር ግን ዘላለማዊ ሕልው ነው! ስለዚህ ምጡቅ ነው። ፍጡር ሁሉ ይለወጣል፤ ያረጃል፤ ይሻሻላል። እግዚአብሔር ግን አይለወጥም። ስለዚህ ምጡቅ ነው። ፍጡር ሁሉ በሕይወት ለመኖር ከእርሱ ውጪ የሆኑ ብዙ ነገሮች ያስፈልጉታል። እግዚአብሔር ግን በራሱ ምሉዕ ነው። የሚያስፈልገው ምንም ነገር የለውም። የሰው እጅ በሰራው ነገር አይገለገልም። የምንም ነገር ረሃብና ፍላጎት የለውም። አብ በዘላለም ከልጁና ከመንፈሱ ጋር በክብርና በፍቅር ልውውጥ፤ በሐሴትና በፍጹም መለኮታዊ ደስታ፤ እንዲሁም ሊቋረጥ በማይችል ሕብረት የሚሮር፤ በራሱ ምሉዕ የሆነ አምላክ ነው! ስለዚህ ምጡቅ ነው። ማንም በዚህ ልዕልና የሚኖር የለም።

የእግዚአብሔር አብሮነትና መገኘት

ነገር ግን ይህ ብቻውን አንድ አምላክ የሆነው አብ በዘመን መጨረሻ ልጁንና መንፈሱን ወደ ምድር በመላክ ራሱን በሙላት ገልጦልናል። ከዚህ የተነሳ እግዚአብሔርን እናውቀዋለን። በርግጥ እናውቀዋለን! የምናውቀውም እውቀት እንደ ጉም የማይጨበጥ ሳይሆን፤ እጆቹን ዘርግቶ እነሆኝ ብሎ ፍንትው ብሎ ነግሮናል። ያ በጥንት ራሱን ሁሉን እንደሚችል ኤልሻዳይ የአብርሃም የይሥሃቅና የያቆብ አምላክ በመባል ለአባቶች የተገለጠው፤ ደግሞም በቁጥቋጦ እሣት “ያለና የሚኖር አምላክ” ሆኖ ከፈርዖን እጅ ህዝቡን በመታደግ ከህዝቡ ጋር ወርዶ መኖር የጀመረው፤ ስሙም ያህዌህ የተባለው የእስራኤል አምላክ፤ ደግሞ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ምድር ወርዶ በሚወደው ልጁ በኩል ራሱን ገለጠልን! ሕዝቡን በፋሲካ ደም፤ በእንጨት፤ በትር በሙሴ አማካኝነት የታደገው ያህዌህ፤ በፀዓተ-ዘዳግም (ሁለተኛ መውጣት/ Second Exodus) ልጁን ልኮ በደሙ በተደረገ ቤዛነት የሐጥያትን ይቅርታ እንድናገኝ ሐጥያታችንን በእንጨትላይ በሰውነቱ ተሸክሞ ሙሉ ስሙን ገለጠልን፦ አሁን በስሙ “በአብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ” ራሱን ለአህዛብ ይገልጣል። የአባቶች አምላክ፤ የእስራኤል አምላክ፤ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት!

ስለዚህ እግዚአብሔር ምጡቅ እንደመሆኑ ሁሉ ራሱንም ገልጦልናል። “ምሥጢሩ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው፤ የተገለጠው ግን…እናደርግ ዘንድ ለእኛ ለዘላለምም ለልጆቻችን ነው” እግዚአብሔርን በምጡቅነቱ ማንም ሊያውቀው አይችልም። ምጡቅነቱ ሚስጢር ነው። መገለጡ ግን ገንዘባችን ነው! ርስታችን ነው! ለልጆቻችን የምናወርሰው ሐብታችን ነው! አብን በሙላት ያለተከፍሎና ያለ ገደብ በምጡቅነቱ የሚያውቁት ሁለት አካላቶች ብቻ ናቸው። እነርሱም ወልድ (ማቴ. 11:25-26)ና መንፈስ ቅዱስ (1 ቆሮ. 2:10–12) ናቸው። ከሰማይ የመጡ እነዚህ ሁለት አካላት፤ እግዚአብሔርን በሙላት ገልጠውልናል። በወልድ ማንነት፤ ቃልና ሥራ “አስተርዕዮተ-እግዚአብሔር” አገኘን። መንፈስ ቅዱስ በልባችን በማደሩ ደግሞ የውስጥ ብርሃን “አብርሖተ-እግዚአብሔር” አገኘን። ግዴታችን በክርስቶስ መምጣት የተሰጠንን አስተርዕዮ (Revelation) ማወቅና መታዘዝ ነው። ይህም ዕውን የሚሆነው በመንፈስ ቅዱስ የልቡና ዓይን በማብራት (illumination) አገልግሎት ነው። አምልኮአችን ለዚህ ለተገለጠልን አምላክ የሚመጥን ይሁን። መዝሙራችን የተገለጠልንን አምላክ መልሶ መላልሶ በትውልዳችን ይሳል። ስብከታችን በመንፈስ ቅዱስ ሐይል በክርስቶስ የተገለጠውን እንደገና ደግሞ፤ ደግሞ፤ ደግሞ ይግለጥ። ይህም የሚሆነው የስብከታችን ሆነ የመዝሙራች ይዘት፤ አስተርዕዮተ-እግዚአብሔርን ገንዘቡ ያደረገ እንደሆን ብቻ ነው! ከዚህ የተነሳ አገልግሎት የፈጠራና የብልሃት ጉዳይ ሳይሆን፤ ራሱን የገለጠልንን አምላክ፤ በገለጠልን መንገድና በገለጠልን ቃላት፤ ሳንጨምርና ሳንቀንስ መልሶ የመግለጥ አደራና ታማኝነት ነው። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ሙላት ነው። ኢየሱስ ከሰማይ የመጣ፤ በጴንጤናዊው ጲላጦስ ፊት እውነትን የመሰከረ ታማኝ ምስክር ነው። የመሰከረውም እውነት ነው። ምክኒያቱም እርሱ ከምጡቅ መጋረጃ ወጥቶ፤ ከአባቱ እቅፍ ወርዶ፤ በአካል አባቴ እነሆኝ ብሎ ተርኮልናል። ከዚህ የተነሳ “ከላይ የመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሚሆነው የምድር ነው የምድሩንም ይናገራል። ከሰማይ የመጣው ከሁሉ በላይ ነው። ያየውንና የሰማውንም ይህን ይመሰክራል፥ ምስክሩንም የሚቀበለው የለም። ምስክሩን የተቀበለ እግዚአብሔር እውነተኛ እንደ ሆነ አተመ። እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራልና፤ እግዚአብሔር መንፈሱን ሰፍሮ አይሰጥምና። አባት ልጁን ይወዳል ሁሉንም በእጁ ሰጥቶታል። በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም”
ለዚህ ነው ብዙ ከመናገር ብዙ መስማት ተቀዳሚ የሆነው። መስማትም በክርስቶስ ቃል ይሁን። ሳኦል ከመንግሥት ሥራ የታገደው ለዚሁ ነበር። የመንግሥቱ ሐሳብ አልገባውምና “ማዳመጥ ከአውራ ስብ ይበልጣል” ይህ ልንሰማው ግድ የምንባለው ቃል፤ አባቴ እንዲህ ነው ብሎ በሙላት በተረከልን በክርስቶስ ቃል ነው። ይህ ቃል ሕግና ነብያት የመሰከሩለትና የሕግና የነብያት ፍጻሜ ቃል ነው። ይህንንም ቃል ለህዝቦች ሁሉ እንድናውጅ አደራ ተሰጥቶናል “”ያስተማርኳችሁን ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው (ማቴ. 28:20)” ይህንንም ቃል እንድንረዳ በሐጥያት የደነዘዘውንና የደነደነውን እውሩን ልባችንን አብርቶ ኢየሱስ የተናገረውን እንድንረዳ የሚያስችለን፤ እንድናስታውስ የሚረዳን፤ እንድናምንና እንድንታዘዝ ጉልበት የሚሆነን መንፈስ ቅዱሱ ከበዓለ ሐምሳ ጀምሮ ቆርጦ ተነስቷል። መንፈስ ቅዱስ የልጁ መንፈስ ነው። አላማው የእግዚአብሔርን ልጅ ማክበር ነው። ተልዕኮው የእ/ርን ልጅ መልክ እንድንመስል ከክብር ወደ ክብር መለወጥ ነው!

© 2013 – 2015, Samson Tilahun. All rights reserved.

Like Be the first one who likes this post!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Top