Home / Media Posts / ► 002: ሕዝቅኤልና ዘመኑ፡ ታሪካዊው አውድ

► 002: ሕዝቅኤልና ዘመኑ፡ ታሪካዊው አውድ

Posted on

ሕዝቅኤልና ዘመኑ፡ መግቢያ

ዕለቱ July 31, 593 ቅ.ዓ. ነው። ምናልባትም ሕዝቅኤል በእግዚአብሔር ፊት ልቡን ለማፍሰስ ወደ ኮቦር ወንዝ ዳር ሔዶ ሊሆን ይችላል። ይህም ይሆን ይህ የምናውቀው ነገር ቢኖር ሕዝቅኤል ካህን ወይም የካህን ልጅ እንደነበር እና ይህ ቀን ደግሞ የካህኑ 30ኛ የልደት ዓመቱ እንደሆን ነው። የካህኑ የቡዝ ልጅ እንደመሆኑ እድሜ ልኩን ለካህንነት ሲገዘጋጅ እንደ ኖረ መገመት አዳጋች አይደለም።

ሆኖም ግን ከዓምስት ዓመታት በፊት በ597 ቅ.ዓ. ናቡከደነጾር ሁለተኛውን ምርኮ ባደረገ ጊዜ የይሁዳን ንጉሥ ዮአኪንንና ከእርሱ ጋር ወደ 10ሺህ የሚጠጉ የንጉስ ቤተሰቦችንና ሹሟሙንቶችን ተማርከው ወደ ባቢሎንት ተጓዙ። ከነዚህ መካከል የ25 ዓመት ወጣት የሆነው ሕዝቅኤል ነበረበት። ይህ ቀን ኢየሩሳሌም ቢሆን ኖሮ ሰላሳኛውን ዓመት የሚያከብርበት ቀንና ወደ ክህንነት አገልግሎቱ የሚካንበት የሹመት ቀን ይሆን ነበር። አሁን ግን በውርደት ከኢየሩሳሌም መቅደስ ወደ 880 ማይልስ እርቆ ይኖራል። የሚኖረውም በባዕድ ምድር፤ ስደተኞች እንዲሰፍሩ ከተደረጉባቸው ሥፍራዎች አንዱ በሆነውና በኮቦር ወንዝ አቅራቢያ ባለው፤ ቴል አቪቭ በሚባል ሥፍራ ከምርኮኛ ህዝብ ጋር ነው (1:1–3; 3:11, 15)። በምርኮው ዘመን ይሰማ የነበረውን ሰቆቃ ማዳመጥ የሕዝቅኤልን መጽሀፍ በትክክል እንድነረዳና መልክቱን እንድናዳምጥ ያግዘናል። ለምሳሌ ሁለቱን እንመልከት፦

መዝ. 137 “በባቢሎን ወንዞች አጠገብ፣ በዚያ ተቀምጠን ሳለን፣ ጽዮን ትዝ ባለችን ጊዜ አለቀስን። እዚያም በአኻያ ዛፎች ላይ፣ በገናዎቻችንን ሰቀልን። የማረኩን በዚያ እንድንዘምርላቸው ጠየቁን፤ የሚያሠቃዩን የደስታ ዜማ ፈለጉብን፤ ደግሞም፣ “ከጽዮን መዝሙሮች አንዱን ዘምሩልን” አሉን።የእግዚአብሔርን ዝማሬ፣ እንዴት በባዕድ ምድር እንዘምር! ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ብረሳሽ፣ ቀኝ እጄ ትክዳኝ። ላስታውስሽ ብቀር፣ ኢየሩሳሌምን የደስታዬ ቍንጮ ባላደርግ፣ ምላሴ ከትናጋዬ ጋር ትጣበቅ”

ሰቆ. 5 “እግዚአብሔር ሆይ፤ በእኛ ላይ የደረሰውን አስብ፤ ውርደታችንን እይ፤ ተመልከትም። ርስታችን ለመጻተኞች፣ ቤቶቻችን ለባዕዳን ዐልፈው ተሰጡ። ወላጅ አልባና አባት የሌላቸው ሆንን፤ እናቶቻችን እንደ መበለቶች ሆኑ። ለምንጠጣው ውሃ መክፈል ነበረብን፤ ዕንጨታችንንም የምናገኘው በግዢ ነበር። የሚያሳድዱን ከተረከዞቻችን ሥር ናቸው፤ ተጨንቀናል ዕረፍትም አጥተናል። እንጀራ እንጠግብ ዘንድ፣ ለአሦርና ለግብፅ እጃችንን ሰጠን። አባቶቻችን ኀጢአት ሠርተው አለፉ፤ እኛም የእነርሱን ቅጣት ተሸከምን። ባሮች ሠልጥነውብናል፤ ከእጃቸው ነጻ የሚያወጣን ማንም የለም። አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ለዘላለም ትገዛለህ፤ ዙፋንህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል። ስለ ምን ፈጽመህ ትረሳናለህ? ስለምንስ ለረዥም ጊዜ ትተወናለህ? እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ መልሰን፤ እኛም እንመለሳለን፤ ዘመናችንን እንደ ቀድሞው አድስ፤ ፈጽመህ ካልጣልኸን፣ ከመጠን በላይ ካልተቈጣኸን”

▶️ ስለዚህ ምናልባት ወደ ኮቦር ወንዝ መጥቶ ወደ እግዚአብሔር እሮሮውን ሊያሰማ ሊሆን ይችላል። በዚህ ካህን ልብ ውስጥ ብዙ ጥያቄ ከመኖሩ የተነሳ ኋላ ያህዌህ ወደ አገልግሎት ሲልከው እልሀኛ እንዳይሆን አያሌ ማስጠንቀቂያዎችን ይሰጠዋል።
▶️ ብዙ አንገባጋቢ ጥያቄዎች በዚህ ወጣት ልብ ውስጥ እንዳለ መገመት አዳጋች አይደለም። እነዚህን ጥያቄዎች በሁለት መክፈል እንችላለን።

(1) ያህዌህና ሕዝቡን በጥቅሉ እንዲሁም ሕዝቄልን በግል የተመለከቱ ጥያቄዎች
(2) ያህዌህና ኪዳኑን እንዲሁም ማንነቱን የተመለከቱ ጥያቄዎች።

© 2016, Samson Tilahun. All rights reserved.

Like Be the first one who likes this post!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Top