Home / Blog / ▶ ወንጌል ስለ ልጁ ሹመት የምሥራች ቃል ነው፡- በሰማይና በምድር ኢየሱስ ጌታና ክርስቶስ ሆኖ ተሹሟል

▶ ወንጌል ስለ ልጁ ሹመት የምሥራች ቃል ነው፡- በሰማይና በምድር ኢየሱስ ጌታና ክርስቶስ ሆኖ ተሹሟል

Posted on
“ወንጌሉም ስለ ልጁ፣ በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ሆነ፣ በቅድስና መንፈስ ደግሞ ከሙታን በመነሣቱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ በኀይል ስለ ተገለጠው ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” 1:3-4


 
ይህ የምንናገርለት ወንጌል ባለቤትና ይዘት ዓለው። ወንጌል የእግዚአብሔር ነው “ለእግዚአብሔር ወንጌል የተለየ…” (1:1)። ወንጌል ባለቤት፤ ምንጭና ይዘት ስላለው የአንድ ተቋም ይዞታ አይደለም፤ ባለቤቱም እግዚአብሔር አብ ነው! ከዚህ የተነሳ ይህንን ወንጌል ማንም ሥጋ ለባሽ “የእኔ ነው” ሊለው አይችልም። እንደዚሁም ወንጌል “ባለቤት” ብቻ ሳይሆን፤ “ይዘትም” አለው! ይዘቱ ደግሞ አንድያ ልጁ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው! “በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ሆነ…ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው”። ይህ ይዘት በሌላ ነገር ሊተካ በፍጹም አይቻልም። ይዘቱ የተቀያየጠ ወንጌል፤ በገላትያ መጽሐፍ መሠረት፤ እንግዳ ወንጌል ነው። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ይዘቱ ያላደረገ ወንጌል፤ የሚሰብክ መልዓክ ቢኖር እንኳ “ርጉም ይሁን!” ይለናል። ይህ ከሁሉ የላቀ ታላቅ ሐጥያት ነው።
 
ስለዚህ ወንጌል ያነጣጠረው በሰባኪው አሊያም በተሰባኪው ላይ አይደለም። ሆኖም ግን ወንጌል ለሰው ልጅ መፍትሔ ነው። ወንጌል ለሐጥያታችንና ለበደላችን መልስ ስለሆነ ግን ሰው-ተኮር ነው ማለት አንችልም። ወንጌል የእግዚአብሔር ነው፤ ይዘቱም “ስለ ልጁ ነው።” ይህ በልጁ ላይ ያተኮረው ወንጌል አላማ ግን ለአብርሀም የተሰጠውን ተስፋ፤ ይህም የምድር ወገኖች ሁሉ (አህዛብ) የአብርሃምን አምላክ አምላካቸው በማድረግ በረከቱ፤ ይደርስላቸው ዘንድ ነው። ከእነዚህም አሕዛብ መካከል በወንጌል አማካንነት በጸጋው ከተጠሩት አንዱ እኛ ስለሆንን፤ ተደፍተን ክብርን ከመስጠት በስተቀርና ለወንጌሉ ይዘት ታማኞች ከመሆን ባሻገር ምን ምላሽ አለን? ለዚህ ነው በቁጥር 5-6 ላይ ሐዋርያው ዜግነታቸው ሮማውያን ለሆኑትና ከተስፋው ርቀው ወደነበሩት አሕዛብ እጆቹን ጦቁሞ፡
 
“በእርሱ በኩል ስለ ስሙ ከአሕዛብ ሁሉ መካከል ሰዎችን በእምነት አማካይነት ወደሚገኘው መታዘዝ ለመጥራት ጸጋንና ሐዋርያነትን ተቀበልን።እናንተ ራሳችሁም ለኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሆኑ ከተጠሩ መካከል ናችሁ።” (ሮሜ. 1:5-6)
 
በቀዳሚነት ደረጃ (1 ቆሮ.15:1-5) ወንጌል “ለእኛ” ቢሆንም “ስለ እኛ” ግን አይደለም (በቀዳሚነት በሚለው ቃል ላይ አንባቢዬ እንዲያተኩር እሻለሁ)። በታሪካችን፤ ክርስቶስን የወንጌል አስኳል ካለ ማድረግ የተነሳ፤ የሚከተሉትን እንቅስቃሴዎች እንዲነሱ አድርጓል። ለናሙና ያህል “በሰዎች ማሕበራዊ ቀውስ” ላይ ያተኮረ ወንጌል (the social gospel)፤ “በሰው ልጅ ሰብዓዊ መብት” ላይ ያተኮረ ወንጌል (the liberation gospel)፤ “በኢኮኖሚ ብልጽግና ላይ” ያተኮረ ወንጌል (the prosperity gospel)፤ “በሰው ሥነ-ልቡናዊ ቀውስ” ላይ ያተኮረ ወንጌል (the therapeutic gospel)..ወዘተ። ችግሩ ታድያ ምኑ ላይ ነው? ምን አለበት ወንጌል ያበለጽጋል ቢባል? ምን አለበት ወንጌል የሕብረተሰብን ቀውስ ይፈውሳል ቢባል? ምን አለበት ወንጌል የበታችኝነትን ስሜት ያቃልላል ቢባል? መልሱ ቀላል ነው። ምክኒያቱም በመጀመሪያ ደረጃ የወንጌሉ ባለቤት “እግዚአብሔር በመሆኑ” ወንጌል ምን ማለት እንደሆን እርሱ ይንገረን እንጂ! የእኛ እድል ፈንታ መስማት ብቻ ነው! በሁለተኛ ድረጃ የእነዚህ ሁሉ ችግር የወንጌልን ትኩረት “በሰውና በችግሮቻችን ላይ” በማኖራቸው ነው። ቤተክርስቲያን የወንጌል ባለአደራ እንጂ የወንጌል ደራሲ አይደለችም። ወንጌል የአንድ ቤተ-ዕምነት አንቀጽ አይደለም። ወንጌል የቤተክርስቲያን መሠረቷ እንጂ የምትጽፈው መተዳደሪያ ደንብ አይደለም። ሐዋርያት ተሰብስበው “ለእኛ መልካም መስሎ ታይቶናልና” ብለው የጻፉት ለወቅቱ አንገብጋቢ ችግር መፍትሔ አልነበረም። የወንጌል ይዘት አያድግም፤ አይለወጥም፤ ምክኒያቱም ታሪክና ዘመን መጠቅ ስለሆነ። ወንጌል የሰውን ልጅ አመጽ የሚሰርዝበትና እግዚአብሔር በልጁ አማካኝነት የሚነግሥበት የምሥራች ቃል ነው። ለዚህ ነው “በእምነት ወደ ሆነ መታዘዝ…” ያለን። ወንጌል ሕዝቦችን ወደ አምላክ ያስታርቃል።
 
ከኤደን ገነት የጀመረው አመጽ ሲፈረድ አየን ግን በጸጋው ተስፋ ተሰጠ (ዘፍ. 3፡15)። በኖህ የውሃን ጥፋት የሰው ልጆች በደል ምን ያህል ግዙፍ እንደሆን ምድር በሙሉ ሲደመሰስ አየን፤ ግን በጸጋው ኖህና ቤተሰቡ ሲተርፉ አቤት አልን (ዘፍ 6-9)። በዘፍ 11 ላይ ደግሞ ይህ አመጽ ጫፍ ሲደርስ በባቢሎን ግምብ ላይ ተመለከትን፤ ግን ፍርዱ ሲገለጥ ብቻ እንጂ በኤደንና በውሃ ጥፋት ዘመን እንደነበረው፤ የአመጽ-›ፍርድ-›ጸጋ ቀመር በዘፍ 11 ላይ ሲሰራ አናይም። ምክኒያቱም ይህ ጸጋ “በምርጫ” ተገለጠ። የአብርሃም ተስፋ ከዘፍጥረት 3-11 ላይ ላለው አሰቃቂ አመጽ መልስ ነበር (ዘፍ. 12 – ራዕ 22) “በዘርህ የምድር ወገኖች ሁሉ ያባረካሉ”…ሲል ወንጌልን ለአብርሃም ሰበከለት ይለናል። ይህም ዘር በሥጋ ከዳዊት ዘር የሆነው ክርስቶስ ነው!
 
ስለዚህ የሰው ልጅ ቀውስ በመጀመሪያ ደረጃ ኢኮኖሚያዊ አይደለም። ሕብረተሰባዊም አይደለም። ስነ ልቡናዊም አይደለም። ሆኖም ግን እነዚህ ሁሉ የሐጥያት መዘዞች ናቸው። የሰው ልጅ ዋነኛ ችግሩ ‘ሐጥያት’ ነው። ወንጌል በሰው ልብ ላይ ድል ሲጎናጸፍ፤ እውነት ነው የሰዎች ጥላቻና ዘረኛነት ፈውስ ይገኝለታል፤ ከሁለቱ አንድን ሰው በመፍጠር የጥልን ግርግዳ አፍርሷልና። ርግጥ ነው ከክርስቶስ ጋር አንድ መሆኗን የተረዳች ነፍስ ከሥነ-ልቡናዊ ቀውሷ ትፈወሳለች።
 
ስለዚህ በመጀመሪያ ሐጥያት ምንድር ነው? የሚለውን ጥያቄ ማንሳትና መመለስ ግዴታችን ይሆናል። በ11ኛው ክፍለ ዘመን እንደ ምሶሶ ተደርገው ከሚቆጠሩት የቤተክርስቲያን አበው መካከል አንዱ “ከካንትቤሪ የሆነው አንሰልም”፤ “ለምን አምላክ ሰው ሆነ?- Cur Deus Homo” በተሰኘው መጽሐፉ ከብዕር ጓደኛው ጋር ሲወያይ እንዲህ ብሎ ጻፈ።
 
“የሰው ልጆች መዋጀት ከራሱ ከእግዚአብሔር በስተቀር በሌላ ሰው አሊያም [በፍጡር] መልአክ አማካይነት ሊከናወን አይችልም። ከዘላለም ሞት ያዳነን ከእግዚአብሔር ሌላ የሆነ አካል ቢሆን ኖሮ፤ የዳኑት ለዚህ ላዳናቸው አካል (ሰው ወይም መልአክ) አዳኜ ብለው ባርያ በሆኑለት ነበር። ታድያማ ይህ እንዴት መዳን ይባላል?! ምክኒያቱም የዳኑት ከእግዚአብሔር ሌላ ለሆነው ባርያ ናቸውና” [ይህ አሁን እንደሆነው ማለት ነው…በአየሩ ላይ ላለው አለቃ፤ ለሐጥያትና ለተለያዩ ምኞቶች ሰዎች ይገዛሉና] ”
 
ይህ የቤተ-ክርስቲያን አባት አስምሮ የተናገርው ነገር ምንድር ነው፤ የሰው ልጆች ሐጥያት እምብርት “አመጽ” ስለሆነ፤ ይህም ለእግዚአብሔር አለመገዛት፤ ከእግዚአብሔር ሥልጣንና አገዛዝ ማፈንገጥ፤ የእግዚአብሔርን ክብር በሌላ በተፈጠሩ ነገሮች መመሰል እንደዚሁም የእግዚአብሔርን መለኮታዊ እውነት በሐሰት መለወጥ እስከሆነ ድረስ፤ ሰው አልተዋጀም። እውነተኛ መዋጀት እነዚህ ነገሮች ያስተካከለ እንደሆን ብቻ ነው። አንድ ሰው እንበልና ሐብታም ቢሆን፤ ጤነኛ ቢሆን፤ ደስተኛ ቢሆን…ከሰማይ በታች ባሉት መልካም ነገሮች በሙሉ ነፍሱ ብትጠግብ…ይህ ሰው ከንቱ ነው። አልተዋጀም። ሰው ወደ እግዚአብሔር ሥልጣን ሲመለስ፤ ተንበርክኮ ይህንን አምላክ አዳኜ ያለ እንደሆን ብቻ ነው እውነተኛ “መዳን” ያገኘው። አንሰልም ጥሩ አይቷል። በነብዩ ኢሳያስም ያህዌህ እንዲህ ይላል፦
 
“እናንተ ከአሕዛብ ወገን ሆናችሁ ያመለጣችሁ፥ ተሰብስባችሁ ኑ በአንድነትም ቅረቡ፤ የተቀረጸውን የምስላቸውን እንጨት የሚሸከሙና ያድን ዘንድ ወደማይችል አምላክ የሚጸልዩ እውቀት የላቸውም…ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ እኔ ጻድቅ አምላክና መድኃኒት ነኝ፥ ከእኔም በቀር ማንም የለም። እናንተ የምድር ዳርቻ ሁሉ፥ እኔ አምላክ ነኝና፥ ከእኔም በቀር ሌላ የለምና ወደ እኔ ዘወር በሉ ትድኑማላችሁ። ቃሌ ከአፌ በጽድቅ ወጥታለች፥ አትመለስም። ጕልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፥ ምላስም ሁሉ በእኔ ይምላል ብዬ በራሴ ምያለሁ” (ኢሳ. 45:20-25)
 
ይህ የያህዌህ ተስፋ “ጌታ” አድርጎ በሾመው ልጁ ተፈጽሟል “እናንተ የሰቀላችሁትን…ጌታና ክርስቶስ አድርጎታል”። አሁን አሕዛብ “ኢየሱስ ጌታ እንደሆነ” በማመን ድነትን መቀበል እንችላለን። በዚህች ሰዓት ይህንን ንባብ እያነበባችሁ ነገር ግን በብዙ መከራ ያላችሁ ብትኖሩና በወንጌል አምናችሁ የዳናችሁ ከሆናችሁታላቅ የምሥራች አለኝ “በበጉ ደምና በምስክርነታችሁ ቃል፣ ድል ነሥታችኋል!”…ይህም ምሥክርነት ዮሐንስ በራዕይ ሲነግረን “እነርሱም የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁና የኢየሱስን ምስክር አጥብቀው የያዙ ናቸው” ይለናል። በርግጥ እውነት ነው በክርስቶስ አማካንነት ከእግዚአብሔር ጋር ዕርቅ ስታገኙ ሌላ ጠላት አፍርታችኋል “ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቈጣ፤ ከቀሩት ልጆቿም ጋር ሊዋጋ ሄደ” ሆኖም ግን ከአምላካችሁ ቁጣ በክርስቶስ ሥርየት አግኝታችሁ ታርቃችኋል። የምሥራች! ድል ከነሳው ጋር በክብር በሰማያዊው ሥፍራ ከክርስቶስ ጋር ተቀምጣችኋል። ምናልባት ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር በክርስቶስ ያልታረቃችሁ በትኖሩ “ከእግዚአብሔር ጋር በኢየሱስ በኩል ታረቁ” ብዬ ወደ ተሰቀለው ክርስቶስ በማመላከት እማጸናችኋለሁ። ይሄው የምህረቱ ጌታ አንድ ቀን በሰማያት ድንገት ይገለጣልና። የዚያን ጊዜ በወንጌል አማካንነት ላልታረቁ ሁሉ ታላቅ የምጥ ቀን ነው። ሐጥያታችሁን በመስቀል ተሸክሞ በሞተው በኢየሱስ ስም በማመን በንሥሃ ተመለሱ እላለሁ።
 
ስለዚህ የወንጌል ማዕከል ሰው ሳይሆን የእግዚአብሔር ክብር ነው! የወንጌል ማዕከሉ የሰው ልጆች ፍላጎት አይደለም። እኔና እናንተ አይደለንም። ወንጌል አነጣጥሮ ፍንትው አድርጎ የሚያበራው በክርስቶስ ፊት ላይ ነው። ስለዚህ ነው ሐዋርያው
 
“የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፥ የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን አሳብ አሳወረ….በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን እንዲሰጥ [ግን] በልባችን ውስጥ የበራ፤ በጨለማ ብርሃን ይብራ ያለ እግዚአብሔር ነውና” 2ቆሮ 4:4
 
ያ በዘፍጥረት ላይ “ብርሃን ይሁን” ያለው ሐያሉ የእግዚአብሔር ቃል፤ አሁን በወንጌል-ቃል አዋጅ አማካይነት ሙታንን አዲስ ፍጥረት ያደርጋል። ይህም አዋጅ-ቃል ፍንትው የሚያደረገው የሥጋ ለባሽን ግርማ ሳይሆን የክርስቶስን ፊት ነው። እርሱም የእግዚአብሔር አምሳልና ክብር የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው! ስሙ ለዘለዓለም ይባረክ! ስለዚህ ነው ወንጌል “ስለ ክርስቶስ ነው የምለው!” ሲቀጥልም ሐዋርያው
 
“ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታ እንደ ሆነ እንጂ ራሳችንን አንሰብክምና፥ ስለ ኢየሱስም ራሳችንን ለእናንተ ባሪያዎች እናደርጋለን።” 2ቆሮ 4:5
 
ስለዚህ ከሮሜ 1:1-5 የምንማረው
__ ወንጌል የእግዚአብሔር አብ መሆኑን
__ወንጌል ስለ ልጁ መሆኑን
__ወንጌል ይዘት ያለው መሆኑን ነው። ይህም ይዘት፡
______አስቀድሞ በነብያቱ አፍ በቅዱሳት መጻሕፍት የተሰጠ ተስፋ ነበር
______አሁን ግን በሥጋ ከዳዊት ዘር ሆኖ መወለዱ
______በቅድስና መንፈስ ደግሞ ከሙታን በመነሳቱ በልዩ መንገድ ‘የእግዚአብሔር ልጅ’ መሆኑ መረጋገጡ (ትንሳኤውና እርገቱ)
 
ልናስተውል የሚገባው በኤደን ገነት በሰይጣን አነሳሽነት የተፈጸመው የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ እንደ እግዚአብሔር ለመሆን ነው። በኤደን ገነት መካከል የተተከለችው ዛፍ ለአዳምና ለሔዋን የእግዚአብሔርን ሉዓላዊ ሥልጣኑን ማዕከል ያደረገች ምሳሌ ነበረች። ከውድቀት በፊት እግዚአብሔር ለሰው ማዕከላዊ ነበር። ሐሳቡ የተቃኘው በአምላኩ ነበር። ከዚያም የተነሳ እርስ በርስ ትክክለኛ ግንኙነት ነበራቸው (ሁለቱም አይተፋፈሩም ነበር)። ሆኖም ግን ሐጥያት (አመጽ) መርገምን አመጣ። የሰው ልጅ ማዕከል እኔነቱና የገዛ ፍላጎቱ ሆነ (ኤፌ 4፡ 17-23፤ ሮሜ 1:21፤ 1 ጴጥ. 1:18፤ ቆላ. 2:18፤ 2 ጴጥ. 2:18)። ከዚህ ፍርድ ሰዎችን ነጻ ለማውጣትና የእግዚአብሔርን ሥልጣን በሰማይና በምድር ማዕከላዊ አድርጎ ለመመለስ ወንጌል የሰውን ልጆች እይታ ሥልጣንን ሁሉ ተጎናጽፎ መንግሥት ሆኖ ወደ ተገለጠው ወደ እግዚአብሔር ልጅ ይመልሳል። ስለዚህ ወንጌል በአመጽ ሥር የወደቀውን የሰውን ዘር ማዕከሉን ወደ ቀድሞ ቦታው የሚመልስ ነው ማለት ይቻላል። ይህም ማዕከል ክርስቶስን እንጂ እኔንና እናንተን አይደለንም። አሊያ የወንጌል ትኩረት ተገላብጦ መልዕክቱ ‘ኢየሱስ እኔን እኔ ሊያደርግ መጣ” ይሆንብናል። (If we turn the gospel to mean that Jesus came to make “me”, ME is idolatory)።
 
ስለዚህ፣ ወንጌላችን በተቀዳሚነት በሁኔታዎቻችንና በችግሮቻችን ላይ ያነጣጠረ መሆን በፍጹም የለበትም። ለምሳሌ ያህል ሰው ሊሰማው የሚገባው የመጀመሪያ መልዕክት “ለሕይወትህ ዓላማ እንዲኖርህ ትፈልጋለህ? ና ወደ ኢየሱስ” “ከሁኔታህ ውስጥ መውጣትና የተሻለ ሕይወት መምራት ትፈልጋለህ? ና ወደ ኢየሱስ” “የዝቅተኝነት ስሜትህ እንዲወገድልህ ትፈልጋለህ? ና ወደ ኢየሱስ” “ፈውስ ትፈልጋለህ? ና ወደ ኢየሱስ” “መንግሥተ ሰማያት መግባት ትፈልጋለህ? ና ወደ ኢየሱስ……” ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች ምን አልባት ለወንጌል መገፋፊያ “a form of apologetic” የሰዎች ጆሮ ለማግኘት ይጠቅም ይሆናል። ነገር ግን እነዚህን ሁሉ የማይፈልግ ማን አለ? እነዚህን ሰው ሁሉ ይፈልጋል ነገር ግን ክርስቶስን አይፈልግም። ይህን ሁሉ ማትረፍ ይፈልጋል ነገር ግን ክርስቶስ እግር ሥር ተደፍቶ “ጌታዬ አምላኬ” በማለት በሥልጣኑ ዘንግ ሥር በመገዛት ሕይወቱን እንዲመራ አይፈልግም። ወንጌል ግን የሚሰጠን ክርስቶስን ነው። እንዲያውም “የተሰቀለ ክርስቶስ – a crucified messiah!“ ይህ ለአይሁድ መሰናክል ለግሪኮች ደግሞ ሞኝነት ነው። አብሮ የማይሔዱ እውነታዎች ናቸውና። ንጉሥ ይነግሳል እንጂ እንደ ወንጀለኛና እንደ ደካማ ባሪያ አይሰቀልም። ወንጌል ግን ሐይልንና ድካምን፤ ክብርንና ውርደትን፤ ዙፋንና መስቀልን፤ አንድ ያደርጋል። በወንጌል አማካይነት ክርስቶስን በመስቀል ድካም የተመረቀ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አናየዋለን! ወንጌል ጣቱን ቀስሮ የሚያመለክተን ስለ አባቱ ፈቅድ ሲል የሰው ልጆችን ሐጥያት ያስተሰርይ ዘንድ ከመላእክት አንሶ የነበረውን ነገር ግን አባቱ ከሙታን አስነስቶ ባረጋገጠለትና ጌታም ክርስቶስም እንዲሆን በሾመው በአንድያ ልጁ ላይ ነው። እንደዚህ ተብሎ የተሰበከለት ትውልድ “መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ” የሚለውን የደቀ/መዝሙርነት መፎክር እንደ ሽንፈት ይቆጥረዋል። በርግጥ የዘመናችን የደ/መዝሙር ችግር ምና አልባት ከወንጌላችን ጋር ግንኙነት ይኖረው ይሁን?
 
ወንጌል በተቀዳሚነት የሚያቀርበው የሰውን ፍላጎትማ ቢሆን ኖሮ መስቀል መሰናክል መሆኑ በቀረ ነበር! እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ጥቂቶቹ ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ፣ ወንጌል ያስገኛቸው ጥቅሞች/ ፍሬዎች ናቸው ማለት ይቻላል፤ ነገር ግን አንዳቸውም ወንጌል አይደሉም። ኢየሱስ በኑሮ ውስጥ እንዴት ዓላማ ሊኖረን እንደሚችል ሊያሳየን አልመጣም፤ በእርግጥ እርሱን ካገኘን በኋላ ለምን መኖር እንደሚገባን ያሳየናል። ወንጌል እኛን ከእግዚአብሔር ጋር ማስታረቅ ብቻ ሳይሆን እርስ በርሳችንም ሊኖረን ስለሚገባውም እርቅ (በክርስቶስ አዲስን ሰው በመፍጠር በሰውነቱ የጥልን ግርግርዳ እንዳፈረሰ) ይናገራል (ኤፌ. 2፥11-14) ። እነዚህ የወንጌል ፍሬዎች ናቸው። ከላይ የተዘረዘሩትን የሰው ልጆችን ቀውስ በርግጥ ወንጌል ይፈታል (ሆኖም ግን ደግሞ አዲስ ኪዳን የተሥፋ ቃሉን መፈጸም በሁለት ዘመናት እንደተከፈሉ አንባቢዬ ልብ እንዲል እመክራለሁ። አሁን በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ተስፋችንን መቅመስ ጀመርን እንጂ ተስፋችን ገና አልተጠናቀቀም። ሙሉ በሙሉ ተስፋችንን የምንረከበው ግን ጌታ ሲመለስ በምንገባበት ዘመን ውስጥ ነው)። ነገር ግን ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ይህ ነው። ወንጌል እነዚህን የሰው ልጆችን ቀውሶች የሚፈታው (እርቅ ከእግዚአብሔር ጋር፤ እርቅ እርስ-ከእርስ ጋር፤ እርቅ ከፍጥረት ጋር – በዚሁ ቅደም ተከተል)፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነውን ኢየሱስን ማዕከል በማድረግ ነው። ኢየሱስን ካገኘነው በኋላ ግን በእርሱና በደሙ ያለን እምነት ወደ ነፍሳችን እረኛ ይመልሰናል።
 
ስለዚህ የመጀመሪያው ተግዳሮት መቀበል ሳይሆን ‘መንበርከክ ነው!” ብዙውን ጊዜ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ።” የሚለውን ቃል ስንጠቅስ ሰዎችን ከክርስቶስ የሚያገኙትን በረከቶች ጎላ አድርጎ ለማሳየትና የሰዎችን ልብ ለመማረክ ነው። ትኩረቱ ግን በመጀመሪያ “ወደ እኔ ኑ!” ላይ ነው። ከዚያ ነው “እኔም….” የሚሉት በረከቶች የሚከተሉት። (በትምህርታችን እንደተመለከትነው፤ ይህ እረፍት በሁለት ዘመናት ተከፍሏል። አሁን በዚህ በዘመን መጨረሻ መንፈሳዊ እረፍትን አግኝተናል ነገር ግን አንድ ቀን ዳግም በመምጣቱ ወደ አዲሲቱ ሰማይና ምድር ወደ ተስፋይቱ ምድር በመግባት ፍጹም እረፍት እናገኛለን!)
 
በወንጌል አማካኝነት የአብ ፍላጎት ልክ እነ ሙሴ፣ እነ አብርሃም፣ እነ ዳዊት … “ሁሉ አብን እንዳከበሩ ወልድን ያከብሩት ዘንድ ነው፤ ወልድን የማያከብር፣ የላከውን አብንም አያከብርም…” (ዮሐ. 5፡23) ይህ የአብ ውሳኔ ነው። ለዚህ ነው ወንጌል ክርስቶስ-ተኮር የሆነው። የወንጌል ዓላማ የእግዚአብሔርን ልጅ ክብር መግለጥ ነው። ስለዚህ፣ በወንጌል የተገለጠው ፍቅር በሱሉስ እግዚአብሔር ማካከል ያለው የፍቅር ልውውጥ ነው። የአብ ውሳኔ የራሱን ዕቅድና ሥራ ለልጁ በመስጠት ለልጁ ያለውን ፍቅር ለማሳወቅ ነው። ይህም የሚሆነው “ሁሉ አብን እንደሚያክብሩ ወልድን ያከብሩት ዘንድ ነው። በተመሳሳይ መልኩ ፣ የወልድ ዓላማ ደግሞ አባቱ የሰጠውን ሥራ በመፈጸም ለአባቱ ያለውን ፍቅር ማሳወቅ ነው። ይንንም በትክክል የፈጸመው እራሱን ባዶ አድርጎ የባሪያን መልክ በመያዝና ትሑት በመሆን በመስቀል ላይ እስከመሞት ድረስ በመታዘዝ ነው። ኢየሱስ ቀጥሎ ያለውን የጸለየውም ለዚሁ ነው፤
 
“የሰጠህኝን ሥራ በመፈጸም በምድር አከከበርሁህ ። እንግዲህ አባት ሆይ ዓለም ሳይፈጠር ከአንተ ጋር በነበረኝ ክብር በአንተ ዘንድ አክብረኝ” (ዮሐ. 17፥4-5)
 
የዚህ መታዘዝ ዓላማ አባቱ ከሰጠው አንድም እንኳን እንዳይጠፋ ነው ፤
 
“ መልሼ ለማንሳት ሕይወቴን አሳልፌ ስልምሰጥ አባቴ ይወደኛል። ሕይወቴን በራሴ ፈቃድ አሳልፌ እሰጣለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፤ አሳልፌ ለመስጠትም ሆነ ለማንሳት ስልጣን አለኝ፤ ይህን ትእዛዝ የተቀበልኩትም ከአባቴ ነው።”
 
ኢየሱስ ሊያድነን የመጣበት ዋንኛው ዓላማ ትኩረታችንን ራሳችንን ከማምለክ (from self-idolatry) ወደ አባቱ ክብር ለማምጣት ነው። አብ ወልድን ይወደዋል ፣ ወልድም አብን ይወደዋል፤ እኛ ደግሞ የዚህ የአብና የወልድ ፍቅር ልውውጥ የሚካሄድበት መሳሪያዎች ሆነናል። “ኦ ይህ ታላቅ ክብር ነው!” ለዚህም ነው በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውና በጉ ፊት በፊታችን ተደፍተን የምናመልከው። እኔና እናንተ ከልጁ ሥራ የተነሳ በዙፋኑ ፊት ቆመን ራሳችንን እናገኘዋለን። ክፉዎች የነበርነው ወልድ የአባቱን ፍቅር የገለጠበት፤ አብ ደግሞ ለልጁ ያለውን ፍቅር ያሳየበት ምክኒያቶች ሆንን! ኢየሱስ ለእኛ ሲሞት፤ አባቱን ለማክበር ለአባቱ ካለው ፍቅር የተነሳ ነው። አብ ደግሞ እኛን ያዳነን፤ ልጁን በጣም ስለሚወደው ስለልጁ ሥራ ሲል ነው። እኛ የዚህ ፍቅር መግለጫ እቃዎች ሆነን እራሳችንን አግኝተንዋል።
 
ወንጌል እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት የሠራው ሲሆን ድርጊቱም የልጁ ሞትና ትንሣዔ ላይ ያነጣጠረ ነው። ስለዚህ በመጀመሪያ በተነሳሁበት ነጥብ አጠቃልላለሁ።

© 2016, Samson Tilahun. All rights reserved.

Like Be the first one who likes this post!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Top