Home / Blog / አማራጭ ንባቦችና ትንታኔያቸው (“ክርስቶስ የሕያው የእ/ር ልጅ” ወይስ “አንተ አንድያ የእግዚአብሔር ቅዱስ”)

አማራጭ ንባቦችና ትንታኔያቸው (“ክርስቶስ የሕያው የእ/ር ልጅ” ወይስ “አንተ አንድያ የእግዚአብሔር ቅዱስ”)

Posted on

ይህ ጥናታዊ ጹሑፍ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 6:69 ላይ ከተለያዩ ቅጂዎች የተወሰዱትን አማራጭ ንባቦችን ይተነትናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ አንባቢዎች ከሆናችሁ ሁለት ነገሮችን በተደጋጋሚ አስተውላችኋል። በመጀመሪያ በመጽሐፍ ቅዱሳችሁ ግርጌ ላይ በተደጋጋሚ፦

 • “አንዳንድ ቅጂዎች__ይላሉ“;
 • “አንዳንድ የጥንት ቅጂዎች __እና __የላቸውም”

የሚሉ ታገኛላችሁ። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ሌላ አይነት ትርጉሞችን ስታመሳክሩ፤ በቀደመው ትርጉም ላይ በግርጌ የነበረው አሁን ጥቅስ ሆኖ፤ ጥቅሱ ደግሞ አሁን ግርጌ ሆኖ ታስተውላላችሁ። ይህንን በተመለከተ ለመነሻ ያህል ዮሐንስ 6:69ን ከአዲሱ መደበኛ ትርጉምና ከ1962ቱ ትርጉም ጋር እናወዳድር።

 • • ”እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ አምነናል አውቀናልም ብሎ መለሰለት” (የ1962 ትርጉም)
 • • “አንተ አንድያ የእግዚአብሔር ቅዱስ እንደሆንህ አምነናል፤ አውቀናልም” (አዲሱ-መደበኛ ትርጉም)
 • • ”Also we have come to believe and know that You are the Christ, the Son of the living God.” (KJV/NKJV)
 • • “And we have believed and know that thou art the Holy One of God” (ASV)
 • • “We have come to believe and to know that you are the Holy One of God.” ( NIV)
 • • “καὶ ἡμεῖς πεπιστεύκαμεν καὶ ἐγνώκαμεν ὅτι σὺ εἶ ┌ὁ ἅγιος τοῦ θεοῦ┐(የግሪክ አዲስ ኪዳን (NA28/UBS4))

ከላይ እንደምናየው እነዚህ ትርጉሞች የተለያዩ አማራጭ ንባቦችን ደግፈዋል። ሆኖም ግን የትኛውን ነው ወንጌላዊው ዮሐንስ የጻፈው? ይህንንስ እንዴት እንዳኛለን? አንደኛውን አነባበብ መምረጣችንስ በሰፊው ስለ ክርስቶስ ያለንን እውቀት በተመለከተ ምን ፋይዳ ያመጣል? ወይም ደግሞ በጠባቡ ስለ ዮሐ. 6:69 ሐቲት በተመለክተ ምን ዓይነት እንደምታ ይሰጠናል? የሚሉትን እንዳሣለን። ይህንን ለመዳኘት በዚህ ጥናታዊ ጹሑፍ ከ20 በላይ የሚጠጉ የግሪክ የእጅ-ቅጂዎችን (manuscripts) በግምት ውስጥ አስገብቻለሁ። ይህንንም በክፍል ሁለት እንመለከታለን።

መግቢያ

በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሰነዳዊ-ሒስ (textual criticism) ሊቅ ተብለው ከሚታወቁት መካከል ዋነኛ በሆነው ብሩስ ሜትዝገር ጥናት መሠረት እ.ኤ.አ. በ2003 የአዲስ ኪዳን ቅጂዎች ዝርዝር ወደ 5735 ተጠግተዋል። ይህ ዝርዝር ብሉይና አዲስ ኪዳናትን ከያዙ ጥራዝ መጻሕፍት (ለምሳሌ ያህል ኮዴክስ ሳይናቲከስ ወይም ኮዴክስ ቫቲካነስ) ጀምሮ በቁርጥራጭ እስከ ተገኙ የግሪክ ክርታሶችን ያካትታል (ወደ 116 ፓፓይረስ፤ በብራና የተጻፉ እንዲሁም ወደ 2432 የሚጠጉ የጉባዔ-ንባባት (Lectionaries))። በተጨማሪም 10,000 የላቲን ቅጂዎች እና 9300 የሚጠጉ አያሌ ትርጉሞች ይገኛሉ። ከእነዚህ ትርጉሞች መካከል ለምሳሌ ያሀል ለመጥቀስ እንደ ሶሪያ፤ ግዕዝ (Ethiopic)፤ ኮፕቲክ (ከእነዚህ አንዱ የሆነውን ሳሒዲክ ጹሑፍ በዚህ ጥናት እናያለን) እና የአርመን ጥንታዊ ቋንቋዎች ይገኛሉ። ከዚህ በተጨማሪ የቤተክርስቲያን አበው አያሌ ደብዳቤዎችን፤ መጣጥፎችን፤ ዕቃቤ-እምነት ጹሑፎችን፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያዎችን ሲጽፉ ቅዱሳት መጻህፍትን መጥቀስ የዘወትር ሥራቸው ስለነበር ጹሑፎቻቸው በእነርሱ ዘመን በእጃቸው ላይ የነበረው የመጽሐፍ ቅዱስ አነባበብ ምን እንደሚመስል ማየት ያስችለናል። በዚህ ጥናታዊ ጹሑፍ ለምሳሌ የጠርጠሉስን ጥቅስ እንቃኛለን (ሊቃውንት እንደሚሉት፤ መጽሀፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ ቢጠፋ፤ አበው ከጻፏቸው መጻህፍት የመጽሀፍ ቅዱስ ጥቅሶች ቢሰበሰቡ እንደገና መጽሀፍ ቅዱስን ማግኘት እንደምንችል ይናገራሉ)። እነዚህ በእጅ የተገለበጡ ቅጂዎች ከ125 ዓ.ም ጀምሮ በጀርመን የሕትመት መሳሪያ እስከ ተሠራበት እስከ 15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ይዘልቃሉ። እነዚህ ጥንት የሆኑ ቅጂዎች የተጻፉት (በግብጽ በብዛት ያድግ ከነበረው ሸምበቆ መሰል-ተክል በተሰራ) በፓፓይረስና (ከእንሥሳ በተለይ ደግሞ ጠቦት ከሆኑት ቆዳ በተሰራ) በብራና ነበር። የፓፓይረስ ዕድሜ ከብራና ጋር ሲነጻጸር አጭር በመሆኑ ምክኒያት አያሌዎቹ የፓፓይረስ ቅጂዎቻችን ቁርጥራጮች ናቸው (የተውሰኑት ወንጌላትን ወይም ደግሞ የሐዋርያው ጳውሎስ ደብዳቤዎችንም ይጨምራሉ)። ሆኖም ግን የብራና ረዥም እድሜ ከሞላ ጎደል ሙሉ መጽሐፍ ቅዱሳትን በአንድ ላይ በመጠረዝ ለብዙ ዓመት ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ ረድቷል። ከእነዚህ መካከል ሦስቱ ጥንታዊ ቅጂዎች ለምሳሌ ያህል ለመጥቀስ፦ ሳይናቲከስ፤ ቫቲካነስ እና የኤፍሬም ጥራዝ በመባል ይታወቃሉ። እነዚህ ጥራዞች ከ4ኛው እስከ 5ኛው ክፍለ ዘመን እንደሆኑ ይታመናል።

እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ያሚያህል አያሌ ምስክሮች ያሉት ምንም ጥንታዊ ጽሑፍ የለም። የሮማውያን ታሪክ ይሁኑ የጥንት ፈላስፋዎች መጣጥፍ ቅጂዎች ቁጥር ሲደመር የመጽሐፍ ቅዱስን ሩብ አያክሉም። ይህ መልካም ሆኖ ሳለ ታድያ፤ አንዳንድ ጊዜ እነዚህ አምስት ሺህ ቅጂዎች እርስ በእርሳቸው ሲነጻጸሩ ልዩነት ይታይባቸዋል። ሆኖም ግን ይህ እጅግ ሊያስደንቀን አይገባም። ከጅምሩ አበክሬ ልናገር የምሻው ግን፤ እነዚህ ልዩነቶች የክርስትናን መሰራታዊ አስተምህሮቶች አንዳቸውንም አያፋልሱም። በሌላ አነጋገር ልዩነቶቹ የክርስቶስን አምላክነት፤ የእርሱን አዳኝነት፤ የውጆቱን ሥራ..ወዘተ አይቃረኑም። ታዲያ እነዚህ ልዩነቶች እንዴት መነጩ? ምንም እንኳ የዚህ ጥናታዊ ጹሑፍ ዓላማ ይህ ባይሆንም በአጭሩ የልዩነቶቹን ምክኒያት ልዘርዝር። በቅጂዎች መካከል ያለው ልዩነት ሆን ተብለው የተደረጉና ያልተደረጉ ልዩነቶች ተብለው በሁለት ጎራዎች ይከፈላሉ (በታች ይመልከቱ)። በቅጂዎች መካከል ላለው ልዩነት ትልቅ አስተዋጾዖ ካደረጉ ምክኒያቶች መካከል በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን የክርስትና መስፋፋት ባልተጠበቀ ፍጥነት መሆኑ ነበር (አንዳንድ እጅግ ጥንት የሆኑ ቅጂዎች በግብጽ መገኘታቸው ይህንን ያንጸባርቃል)።   ይህ ማለት ወንጌል በተሰበከባቸው ሥፍራዎች በሙሉ፤ አብያተ ክርስቲያናት ለጉባኤ ንባብ ይሆን ዘንድ ቅዱሳት መጻህፍትን መፈለጋቸውና ማጠሩ በምናባችን ማየት አዳጋች አይደለም። አሁን ባለንበት የሕትመት ሥራ በተራቀቀበት ዘመን “የመጽሐፍ ቅዱስ ያለ” የሚል የአማኞችና የቤ/ያን ጩሀት ስንሰማ፤ ምን ያህል የመጀመሪያይቱ ቤተክርስቲያን ይሆን? የወንጌል ፍጥነትና የቅዱሳት መጻህፍት ቅጂ ጨርሶ አልተመጣጠኑም። ከዚህ እጥረት የተነሳ የሚነሱ የሥህተት ትምህርቶች በግልጽ የሚታይ ክስተት ነበር። የመጽሀፍ ቅዱስ አስተማሪዎች ከሥፍራ ወደ ሥፍራ እየተዘዋወሩ ማስተማር ግዴታቸው ነበር። በአይሁዳውያን መካከል ይህ የብሉይ ኪዳን ቅጂ ሥራ በተራቀቀ መንገድና ጹሁፍ መገልበጥ ሙያቸው በሆኑ (ጸሐፍት) ሰዎች መሰራቱ ከሞዘረቲክ ማየት ይቻላል። ይህንን በግምት ላይ ስናስገባ ታዲያ ቤተክርስቲያን ገና ከመጸነሷ የመጽሀፍ ቅዱስ ቅጂ መፈለጓ አንድን ክስተት ፈጠረ። በየሥፍራው የሥነ-ጹሁፍ ክሂሎቻቸው በተራቀቀና ባልተራቀቀም ሰዎች ጭምር መጽሀፍ ቅዱስ መቀዳቱ ግድ ነበር። በተጨማሪ አንድ ቅጂ ከተጻፈ በኋላ በራሱ ህይወት አግኝንቷል እንደ ማለት ነው። ይህ ማለት ይኸው ቅጂ ለሚቀጥለው ቅጂ መሰረት መሆኑ አይቀሬ ነው። ከዚህ የተንሳ በአንድ ቅጂ ላይ የተደረገ ለውጥ (ሆን ተብሎ ይሁን ሳይባል) ፤ እርሱን ተደግፈው ለሚቀዱ ሌላ ቅጂዎችም ላይ ይንጸባረቃል። ይህ ለእጅ-ቅጅዎች የ”ዝርያ/genealogical ” ባሕርይ ይሰጣቸዋል ማለት ነው። በዚህ ጥናት ምሁር የሆኑ እነዚህን ተመሳሳይ ባህርያት የሚያንጸባርቁ ቅጂዎች እንደሚከተለው ይመድቧቸዋል፦ አሌክሳንድሪያን፤ ዌስተርንና ቢዛንቲን (Alexandrian, Western and Byzantine) ወዘተ…

ሆን ሳይባሉ የተደረጉ ለውጦች

በመጀመሪያ ደረጃ ጥንታዊ ጸሐፊዎችና ጹሑፍ መገልበጥ ሙያቸው የሆኑ ሰዎች አሁን በዘመናችን እንዳለን መዝገበ-ቃላት አልነበራቸው። ይህ ማለት ቃላትን ሲጽፉ፤ የቃላቶቻቸውን አጻጻፍና የፊደላት አጠቃቀም ወጥ አልነበረም። ከዚህ የተነሳ አንድ ገልባጭ ቃላትን ሲጽፍ በተለየ መልኩ ሊጽፍ ይችላል ማለት ነው። በተለይ ደግሞ ገልባጮች በጋራ ሆንው ሲሰሩ፤ ይህም በመካከላቸው አንድ አንባቢ ቆሞ እያንዳንዱን ቃላት ከዋናው-ቅጂ ሲያንብላቸው ቅጂውን የሚጽፉ ደግሞ የሰሙትን ሲጽፉ ነው። በዋናው ቅጂና በግልባጮ መካከል በጆሮ የሚሰሙት ድምጸት እንጂ በአይናቸው የሚያዩት ንባብ ባለመኖሩ ነው።  ለምሳሌ አንባቢው “ቴዎድሮስ ሳህኑን አጠበ” የሚለውን ዓረፍተ ነገር ቢያንብላቸው ሁለት ቀጂዎች “ቴድሮስ ሣህኑን አጠበ” ወይም “ቴዲሮስ ሰሐኑን አጠበ” ብለው ቢገለብጡ፤ የትኛው ትክክል ነው? የአማርኛ ቋንቋ ሊቅ የሆኑት ስህተቱን ለይተው ሊያወጡ ይችላሉ። ሆኖም ግን ከሦስቱ ዓረፍተ ነገሮች አንዱም ሕጸጸኛ ነው አይባልም።

 • ተመሳሳይ ድምጸት ያላቸው፦ ሌላው ተመሳሳይ ድምጸት ያላቸው ቃላቶች ልዩነትን በቅጂዎች መካከል ያመጣሉ። ለምሳሌ በሮሜ 5:1 ላይ የ1962ቱ ትርጉም “እንግዲህ በእምነት ከጸደቅን በእግዚአብሔር ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እንያዝ  ἔχῶμεν ” ነገር ግን አዲሱ መደበኛ ትርጉም “ሰላም አለን – ἔχομεν ይላል። ይህ ልዩነት የመነጨው ከሁለት ቅጂዎች የተነሳ ነው፡፡ አንዱ ቅጂ “ἔχομεν – አ፟መን” ሲል ሌላው ደግሞ “ἔχῶμεν – አ፟መን” ይላል። በግሪክ ቋንቋ የመጀመሪያው “አለን” የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ “ይኑረን” ይላል። ልዩነቱ በአንድ ፊደል ለውጥ ምክኒያት ነው። ሁለቱም ተመሳሳይ ድምጸት አላቸው።
 • ተመሳሳይ ፊደላት፤ ለአይን ግር የሚሉ ቃላትና አጽሕሮተ-ቃላት፦  በግሪክ ቅጂዎች ላይ ስሞችን አሳጥሮ መጻፍ (አጽሕሮት) የተለመደ ነው። ለምሳሌ እግዚአብሔር የሚለውን ቃል በአማርኛ እ/ር ብሎ መጻፍ የተለመደ ሆኗል። እንደዚሁ “አምላክ፤ ልጅ፤ ዳዊት፤ ኢየሩሳሌም፤ ሰው..ወዘተ…”  በግሪክ ቀጂዎች አሳጥረው ይጽፋሉ። ለምሳሌ ያህል የ1ጢሞ 3:16 አረፍተነገር ባለቤት በሁለት ቅጂዎች ላይ ይህንን ይመስላል፡ Θ̅Σ̅ vs. ΟΣ. የመጀመሪያው አምላክ ለሚለው ቃል አጽሕሮት ሲሆን ሁለተኛ ግን “እርሱም/who” የሚለው ቃል ነው።

ሆን ተብለው የተደረጉ ለውጦች

 1. በቅጂ ሥራ ላይ የሚሳተፉ ሰዎች ሆን ብለው ካደረጓቸው ለውጦች መከካልከል የመጀመሪያው የስሞችና የቦታዎች እንዲሆም የስዋስው ማስተካከያዎች ናቸው። የቋንቋ ጠበብት የሆኑ አንዳንድ በዮሀንስ ራዕይ ላይ የግሪክ ስዋስው ሕግ አልተከተለም በማለት ለማረም ሙከራ አድርገዋል። ሊሰመርበት የሚገባው፤ መልክቱን ለማረም መመኮራቸው ሳይሆን፤ የስዋስው ሕግ እንዲጠብቅ አድርገዋል። ከዚህ የተነሳ አንድ ቅጂ ከሌላ ሊለይ ይችላል ማለት ነው። ሆኖም ግን አንዳንድ ሙሁራን (e.g. Greg Beale) ዩሐንስ በራዕይ የስዋስው ሕጉን የጣሰው ሆን ብሎ እንደሆን ያበክራሉ። ሊያስተላልፈው የሚፈልገውን መልክት ማስተላለፉ የስዋስው ህግ እንዲጥስ አድርጓል።
 2. በተለይ ደግሞ አንዳንድ ገልባጮች (በተለይ ደግሞ ከተወሰኑ አካባቢና ዘመን ይኖሩ የነበሩ) በአዲስ ኪዳን ይቃረናል ብለው ያሰቡትን አረፍተነገሮች ሊያጣጥሙ መሞከራቸው ነው። ይህንን በዮሐ 6:69 ላይ በሰፊው እንመለከታለን። ለምሳሌ በማቴ. 16:16 ላይ ጴጥሮስ “አንተ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብሎ ሲመልስ ዮሐንስ ወንጌል ላይ ግን ጴጥሮስ “አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ” ብሎ ይመልሳል። አንዳንድ ገልባጮች ይህንን ለማረምና ለማጣጣም ዮሐንስ ማቴዎስ ላይ እንዳለው አነባበብ ለመለወጥ ሙከራ አድርገዋል። ለዚህ ሰፊ ማብራሪያ በክፍል ሁለት ላይ እንመለከታለን።
 3. አልፎ አልፎ ቤተክርስቲያን በከረረ የዶክትሪን ክርክር ውስጥ በምታልፍበት ወቅት አንድናድ ጸሐፊዎች እነርሱ የሚሉትን እንዲያንጸባርቅ ሙከራ አድርገዋል።

በመጨረሻ አስምሬ ልናገር የምወደው ቢኖር፤ እነዚህ ከ5ሺህ በላይ የሆኑ ምስክሮች ለእነዚህ አለመስማማቶች እልባት ይሰጣሉ ባይ ነኝ። በእጃችን ያለን ቅዱሳት መጻህፍት ሙሉ በሙሉ ቃለ-እግዚአብሔር ነው። እነዚህ ልዩነቶች የእምነታችን መሰረት ፈጽመው አያናጉም። ይህ አስምሮ የኒናገረው ነገር ቢኖር ለዚህ ሙያ (ቅጂዎችን የማወዳደር ሙያ) ራሳቸውን ሰጠው ጥናት የሚያደሩትን ሰዎች ቤተክርስቲያና ልታመስግን ይገባታል። ከዚህ ቀጥለን የዮሐ. 6:69 በሰፊው እንመለከታለን።

© 2016, Samson Tilahun. All rights reserved.

Like 1 People Liked this
avatar

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Top