Home / Portfolio / Articles / የይሁዳ መልክት – መንደርደሪያ ነጥቦች

የይሁዳ መልክት – መንደርደሪያ ነጥቦች

Posted on
► QUESTION: ሳሚየ እቺ እስቲ ኣስረዳኝ- “ከረጅም ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንድ ሰዎች ሾልከው ወደ እናንተ ገብተዋልና፤ እነርሱ ፈሪሀ እግዚአብሔር የሌላቸው፣ የአምላካችንን ጸጋ በርኵሰት የሚለውጡና እርሱ ብቻ ልዑል ገዣችንና ጌታችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚክዱ ናቸው” ይሁዳ 4 “ምን ማለት ነዉ ከረጅም ጊዜ በፊት ለዙህ ፍርድ የተጻፉ ሲል? ጸጋ ብርኩሰት መለወጥስ? የጌታ የሱስ ጌትነት መካድ እንዴት ነዉ?” (Azeb Berhane)

መግቢያ

“ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ። ከብዙ ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንዶች ሰዎች ሾልከው ገብተዋልና፤ ኃጢአተኞች ሆነው የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት ይለውጣሉ ንጉሣችንንና ጌታችንንም ብቻውን ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ”

የይሁዳ መጽሐፍ ይዘት በሦስት ወይም በአራት አበይት ክፍሎች ራሱን ይከፍላል

 • ሠላምታና መግቢያ (1-3) – ተወደውና ተጠብቀው ለተጠሩ
 • የኃጥያተኞች መንገድና ጥፋት (4-16) – ለዚህ ፍርድ የተጻፉአንዳንድ ሰዎችብዙ ቀለም ባለው ዘይቤ ይመስላቸዋል
 • በክርስቶስ ለመጽናት የቀረበ ጥሪና የስንብት ባርኮት (17-25)

የይሁዳ መልክት ሰለ ሁለት ዓይነት ሰዎች ይናገራል። የመጀመሪያዎቹ በእግዚአብሔር አብ ተወደው ለኢየሱስ ክርስቶስም ተጠብቀው ለተጠሩ” ሲሆን፤ ሁለተኞቹ ደግሞ “አንዳንድ ሰዎች” እና ሾልከው የገቡበሚል ስያሜ በደፈናው የሚጠራቸው ስም-የለሽ ሰዎች ናቸው። እነዚህ ከእ/ር ህዝብ ጋር ድርሻ የላቸውም። ከቁ. 4-16 ላይ ባህሪያቸውንና ሥራቸውን በሚገልጽ የተለያየ ስያሜ ይገልጻቸዋል

 • ከብዙ ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ
 • ኃጢአተኞች
 • የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት የሚለውጡ
 • ኢየሱስ ክርስቶስን የሚክዱ…ወዘተ.

ከዚህ የተነሳ፤ ይሁዳ መልዕክቱን ሲጀምር፤ በእነዚህ በሁለት ዓይነት ሰዎች መካከል፤ ደማቅ ቀለም በማስመር ነው። ይህ አስምሮ የሚያሳየን፤ በእውነተኛ አማኞችና በእነዚህ ‘አንዳንድ ሰዎች’ መካከል (በሐሰተኛ ወንድሞች/እህቶች፤ ሐሰተኛ አስተማሪዎች፤ ሐሰተኛ ሐዋርያትና ሐሰተኛ ነብያት) መካከል ያለው ልዩነት “የድነት” ልዩነት እንደሆነ ነው። ይህ ልዩነት በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የተለየ አመለካከት ስላላቸው ሳይሆን፤ መሠረታዊ በሆነ ጉዳይ ላይ ያለ ልዩነት ነው፤ “ብቻውን ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ”

የእውነተኛ አማኞች ማንነት (1-3)

በእግዚአብሔር አብ ተወደው ለኢየሱስ ክርስቶስም ተጠብቀው ለተጠሩ (ይሁዳ 1)

በመጀመሪያ ደረጃ፤ እነዚህ የክርስቶስ የሆኑት፤ በአብ “የተወደዱ” ፤ “የተጠበቁ” እና “የተጠሩ‘ ናቸው። ሆኖም ግን ይሁዳ ሲጽፍ እነዚህን ሦስት ቃሎች እርስ በርሳቸው አቆላልፎ ቅደም ተከተል ሰጥቷቸዋል። የአዲሱ መደበኛ ትርጉም ይህንን ትሥሥር በመፍታት “የተወደዱ” ፤ “የተጠበቁ” እና “የተጠሩ’ ይላል። ሆኖም ግን በ1962ቱ ትርጉም፤ ከሦስቱ ቃሎች መካከል ዋና አጽንዖት ያረፈው “ለተጠሩ” በሚለው ቃል ላይ እንደሆነ በግልጽ ያሳየናል። እነዚህ ይሁዳ የሚጽፍላቸው አማኞች የክርስቶስ ስለ መሆናቸው ማስረጃው፤ ድሮ በአንድ ወቅት ያደረጉት ውሳኔ ሳይሆን፤ ያ ከመጀመሪያ የነበረው እምነታቸውንና መሰጠታቸውን እ/ር እስከ አሁን የጠበቀላቸው መሆኑ ነው። ይህንንም ከቃሉ ግሥ ማየት እንችላለን። ቃሉ ሃላፊ ብቻ አይደለም “ተወደዋል … ተጠብቀዋል” ወይም በአሁን ግሥ አሊያም በወደ ፊት “የሚወደዱ…የሚጠበቁ” አይልም። ይሁዳ ሲጽፍ የተጠቀመባቸው ቃላቶች “ተወደው…ተጠብቀው…ለተጠሩ” የሚሉ ናቸው። እነዚህ በአማርኛ የስዋስው ሕግ “ቦዝ አንቀጽ” ወይም “Participle’ ይባላሉ። ለምሳሌ ያህል “ተጠብቀው” የሚለው ቃል፤ በአንድ ወቅት የተከናወነ ነገር ግን ቀጣይነት ያለው “ቦዝ አንቀጽ” ግሥ (Perfect Passive Participle) ነው። የዚህ ዓረፍተ-ነገር ዋና ግሥ “የተጠሩ” የሚለው ቃል ሲሆን ይህ “መለኮታዊ መጠራት” ግን በሌሎች ሁለት የእ/ር መለኮታዊ ሥራዎች ጋር የታጀበ ነው፤ “ተወደውተጠብቀው -› ለተጠሩ”። ይሁዳ በመልዕክቱ፤ የአማኞች ጥሪ ሁለት ነገሮች ገንዘቡ ያደረገ ነው፡- የእግዚአብሔር አብን ፍቅር እና ጥበቃ። ለምሳሌ ይህንን አረፍተ ነገር የተለያዩ የእንግሊዝኛ ትርጉሞች እንዲህ ብለው ይተረጉሙታል፦

 • kept for Jesus Christ” (NASB/NRSV/ESV/NIV)
 • preserved in Jesus Christ” (NKJ)
 • keeps you safe in the care of Jesus Christ’ (NLT)

ስለዚህ አማኞች ያመኑ ብቻ ሳይሆን አምነው የክርስቶስ ይሆኑ ዘንድ፤ ያ እንዲያምኑ ያደረጋቸው ፀጋ ዕለት ዕለት እንደ ነዳጅ እምነታቸውን እያቀጣጠለ እንዲቀጥል ያደርገዋል። አማኞች መለዮአቸው “በአንድ ወቅት እጄን አውጥቼ ጌታ ተቀብዬ ነበር” ማለታቸው ሳይሆን፤ ያ ድነት ዛሬም በሕይወታቸው መቀጠሉ ነው። ይህም ራሱ የጸጋ ሥራ ነው። ስለዚህም ይሁዳ በርግጠኝነት፤ እነዚህ የሚጽፍላቸው ሰዎች ከእርሱ ጋር አብረውት ድነትን የሚካፈሉ መሆናቸው ሲገልጽ “ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ” ይላል። ሆኖም ግን ‘ድኛለሁ ያለ ሁሉ ድኗል’ ማለት እንደማንችል ይሁዳ ሲያስጠነቅቀን እንዲህ ይላል፤ “ከግብፅ አገር ሕዝቡን አድኖ የማያምኑትን በኋላ እንዳጠፋቸው ላሳስባችሁ እወዳለሁ”። ከግብጽ የወጣ ሕዝብ ከ6 መቶ ሺህ እስከ 2 ሚልዮን ይገመታል። ያ ሁሉ ግን በምድረበዳ ረገፈ። ለምን? ምክኒያቱም የመጀመሪያ መንፈሳዊ ምልክት በላዩ የታየበት ሁሉ ‘አማኝ ነው’ ማለት አይደለም። የእውነተኛ አማኝ መለዮ ልክ በምድረ በዳ በፈተና እንደጸኑት እስራኤላውያን ይመስላል። እነርሱም በጣም ጥቂቶች ነበሩ። ይሁዳ የሚጽፍላቸውም እስከ አሁን ድረስ ለኢየሱስ ክርስቶስ ይለዩ ዘንድ የጸኑ ናቸው።

በሁለተኛ ደረጃ፤ የእውነተኛ አማኞች ሌላው መለዮ ደግሞ፤ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በክርስቶስ ለመጣው መለኮታዊ አስተርዕዮ (መገለጥ፤ ትምህርት፤ እውነት) ያላቸው፤

 • ጥልቅ መረዳት (ሁሉን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ምንም የተማራችሁ ብትሆኑ… ቁ.5)
 • እና ተጋድሎ ናቸው (ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ….ቁ.3)

ለእነዚህ አማኞች ይሁዳ “ስለ ሚካፈሉት መዳን” ጥልቅ የሆነ ሚስጢር ሊጽፍላቸው ጉጉት ቢኖረውም፤ ነገር ግን ያንን ወደ ጎን አድርጎ ስለ ሌላ ጉዳይ ለመጻፍ ግድ ይለዋል። ይህንን ከጹሁፉ መረዳት እንችላለን። አማርኛ ትርጉማችን ላይ (በተለይ በ1962 ትርጉም) አረፍተ ነገሩ በ “” ሲጨርስ ልብ ይበሉ (ስለዚህ ጉዳይ በቅርቡ ማስተማር እጀምራለሁ)። ይሁዳ እንዲህ ይላል፤

ከብዙ ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንዶች ሰዎች ሾልከው ገብተዋል

አረፍተ-ነገር በ “ና” ሲጨርስ ከላይ ያለውን ሐሳብ ለማጠናከር ወይም ለመግለጽ የተሰጠ ማብራሪያ ነው። በሌላ አነጋገር፤ “ስለዚህ ጉዳይ ልጽፍ ጓጓሁሆኖም ግን በዚህኛው ጉዳይ ላይ ግን መጻፍ ግድ ሆነብኝ” ለምን? በ “ና” ያለቀው ዓረፍተ ነገር ማብራሪያ ይሰጠናል፤ “አንዳንዶች ሰዎች ሾልከው” ስለገቡ ነው። ስለዚህ ይሁዳ ከቁ.4-16 የሚጽፈው ስለ እነዚህ ሾልከው ስለገቡ “አንዳንድ ሰዎች” ማንነት ነው። በይሁዳና በአዲስ ኪዳን በጥቅሉ የሐሰተኛ ነብያት ማንነት በሁለት አበይት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል።

 • በባሕሪያቸው ምን አይነት ሰዎች ናቸው? ሃጥያተኞች (ጸጋን ተገን በማድረግ ሐጥያት ያደርጋሉ)
 • በአስተምሮቶቻቸውስ ምን አይነት ነው? ከሐዲዎች (ስለክርስቶስ መሰረታዊ የሆነውን ይክዳሉ)

ይሁዳ እነዚህን ሰዎች በአራት መንገድ ስራቸውንና መንገዳቸውን ይኮንናል። እነዚህ ሰዎች

 1. . 4-7 በቅዱሳት መጻህፍት የተኮኑን ናቸው። እነዚህም
  1. መጽሐፍ ቅዱስ ከግብጽ ወጥተው በምድረበዳ ስለቀሩ “ሰዎችን” ይኮንናል
  2. መጽሐፍ ቅዱስ ኃጥያት የሠሩ መላዕክትን ይኮንናል
  3. መጽሐፍ ቅዱስ ሶዶምና ጎሞራ መሰሎችን ይኮንናል (ስለሰሩት ክፋትና ስለ ወረደባቸውን ታላቅ ፍርድ ይናገራል)።ሰለዚህ እነዚህ ሰዎች ይፈረድባቸዋል።
 2. በሚለውጡት ነገር የተኮኑን ናቸው (ይህም ታላቅ የሆነውን፤ የእ/ር ጸጋ ለመሰሰን፤ ለመዘሞት፤ ትርፍ ለማግኘት ምክኒያት ማድረጋቸው ራሱ ይኮንናቸዋል)። ይህ ይሁዳ ነካ አድርጎ የሚያልፈው “የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት ይለውጣሉ ጉዳይ በተለይ ሐዋርያው ጳውሎስ አበክሮ የተናገረው እና የጳውሎስን መልዕክት በትክክል ያልተረዱም ሰዎች ጳውሎስን የከሰሱት ጉዳይ ነው። ሐጥያት ሲበዛ ጸጋ በዛ። ይህ ግን አይገለበጥም። ጸጋ ሲበዛ ግን ሐጥያት አይበዛም። ሐዋርያው በዚህን ጊዜ፤ በሮሜ 6 ላይ፤ “በጭራሽ!” የሚል ሙግት ያቀርባል። ጸጋ ምንም እንኳ ለሐጥያተኛ ሰው ቢሰጥም፤ ጸጋ ግን ለሐጥያት መንጃ-ፈቃድ አይደለም። ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ ለአርነት ተጠርታችኋልና፤ ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ፥ ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ (5:13–14)” 1 Pet. 2:16
 3. ልዑል የሆነውን ጌታ ኢየሱስ ክርቶስን መካዳቸው ይኮንናቸዋል። አንድ ሰው ከሐዲ ለመሆን “ኢየሱስ ጌታ አይደለም!” ማለት የለበትም ። ክህደት ብዙ አይነት ገጽታ አለው። ለምሳሌ አንድ የሞርሞን እምነት ተከታይ ሰው፤ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማዳን ሲመሰክር ብንሰማ “”ይህ በጣም የተባረከ ሰው ነው” ማለት ሁሉ ሊቃጣን ይችላል። ከሐዲዎች የሚለዩት በሚያምኑት ሳይሆን በሚክዱት ነው። “ኢየሱስ በሥጋ እንደመጣ የማይታመን” የካደው “ኢየሱስ ጌታ ነው” የሚለውን አይደለም። በርግጥ ይህ ዮሐንስ የሚናገርለት ህጹጽ ሰው “ኢየሱስ መለኮት ነው” ብሎ ያምናል። የካደው ግን የክርስቶስን ሙሉ ስብዕና ነው። ይህ ከእምነት አስወጥቶታል። ስብዕናውን የካደ ምንም እንኳ በአምላክነቱ ቢያምንም ከሐዲ ነው። ለዚህ ነው ይሁዳ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለተሰጠን እውነት ተጋደሉ የሚለን። የእ/ርን ሙሉ ምክር መጨበጥ ለአማኞች ምርጫ አይደለም። በእያንዳንዱ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ምስባክም ላይ ነገረ-መለኮት ለአማኞች እንደ ትምህርት ሊሰጥ የሚያስፈልገው ለዚሁ ነው።
 4. . 8-10 በጸያፍ ስነምግባራቸው የተኮኑን ናቸው፦ ይሁዳ በእነዚህ ሰዎች ላይ ፍርድ እንደሚወርድ ከመናገር ባሻገር፤ ምን ዓይነት ፍርድ እንደሆነ ከመናገር ግን ይቆጠባል። አትኩሮቱ ያነጣጠረው ፍርድን ወደ ሚጋብዘው ባሕርያቸው ምን እንደሆነ በመዘርዘር ላይ ነው። በሌላ አባባል፤ እኛ ፈራጆች አይደለንም። አንድ ፍራጅ እ/ር ብቻ ነው። ሆኖም ግን እኛ ባሕርይን እንፈርዳለን። ፍርድ የተገባው ባህርይ ምን እንደሆነ እና ሐጥያትን ሐጥያት ነው ብለን መፍረድ ይጠበቅብናል። ሦስት ዓበይት ሐጥያተኛ ማንነቶችን ይሁዳ አስምሮ ይናገራል፦ (ሀ) ዝሙትና ሴሰኛነት (ለ) የእ/ርንና የክርስቶስን ጌትነት መካድ (ሐ) ተሳዳቢነትና ለስልጣን አለመገዛት ናቸው።

በባሕሪያቸው ምን አይነት ሰዎች ናቸው (4-16)

ይሁዳ፤ ከላይ እንደጠቀስኩት፤ እነዚህን “አንዳንድ ሰዎች” ብሎ የሚጠራቸው ጠፊዎች፤ ከሚጽፍላቸውና መዳን አብረውት ከሚካፈሉት ጉባኤ፤ ሙሉ በሙሉ ውጪ ያደርጋቸዋል። ሦስት አይነት መንደርደሪያ ስያሜ ሰጥቷቸዋል።

 1. “ከብዙ ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ
 2. ኃጢአተኞች (ይህም የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት የሚለውጡ) እና
 3. ንጉሣችንንና ጌታችንንም ብቻውን ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚክዱ ናቸው።

ከብዙ ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ

ይህ አነጋገር በተለያየ መልኩ ሊተረጎም ይችላል። አንደኛ፦”ለዚህ ፍርድ የተጻፉ” የሚለው ቃል ከላይ ለአማኞች ከተጻፈው ቃል ጋር ተነጻጻሪ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ይህም አማኞችን ልዩ ያደረጋቸው በራሳቸው “ምርጦች” መሆናቸው ሳይሆን በእ/ር መመረጣቸው ነው። ስለዚህ አለም ሳይፈጠር በፊት በፊቱ ነውር አልባ እንድሆን አስቀድሞ በክርስቶስ መረጠን የሚለው የአዲስ ኪዳን የመለኮታዊ ምርጫ በይሁዳም መልክት ላይ ተንጸባርቋል። ስለዚህ ይህ አመለካከት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ የሚለውን ቃል፤ “ለአመጻቸው ታልፈው የተሰጡ” ወይም “በእ/ር ያልተመረጡ” ሰዎችን ለማመልከት ተፈልጎ ነው ይላሉ። ሆኖም ግን ይህ አመለካከት ከብዙ ነገሮች አንጻር ትክክል አይደለም። ጴጥሮስ ለምሳሌ በመልዕክቱ እንደዚያ ይላል። ይሁዳ ግን አላለም። ይሁዳ ያለው “ከዘላለም ለፍርድ የተጻፉ” ሳይሆን “ከብዙ ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ” እንጂ። ስለዚህ መቼ ነው ይህ “ከብዙ ጊዜ በፊት”? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል ማለት ነው።

ሁለተኛ፦ “ለዚህ ፍርድ የተጻፉ” የሚለው ቃል አብሮት “ከብዙ ጊዜ በፊት” በሚለው ቅጽያ እና ከዚህ በኋላ ይሁዳ የሚጽፈው አውዳዊ ትንታኔ እንደሚያሳየን “ከዚህ በፊት የተጻፈ” የሚለው “ብሉይ ኪዳንን” ያመለክታል። የእኔም ድምዳሜ ይህን ሁለተኛውን ትንታኔ ይደግፋል። ይሁዳ “አንዳንድ ሰዎች” የሚላቸው (እነዚህ ሐሰተኛ ነብያት/ ሐሰተኛ መምህራን/ ሐሰተኛ ሐዋርያት) (ምንም እንኳ ይሁዳ እነዚህን ስያሜ ባይሰጣቸውም) የአዲስ ኪዳን ክስተቶች ብቻ አልነበሩም። ይሁዳ የሚለን፤ “እነዚህ አሁን በመካከላችሁ ሾልከው የገቡ ሰዎች፤ ገና ድሮ በቅዱሳትም መጽሐፍ የነበሩ ደግሞ እንደሚነሱ የተተነበየባቸው” ሰዎች ናቸው። የቃል ኪዳን ህዝብ ከተመሰረተበት ቀን ጀምሮ፤ ገና ከጥንት ጠዋት እነደነዚህ አይነት ሰዎች በእ/ር ሕዝብ መካከል ነበሩ። በእነዚህም ሰዎች ደግሞ፤ እ/ር ሲፈርድባቸው መጽሐፉ አሳይቶናል። በብሉይ ሐሰተኛ ነብያት በሁለት መልኩ ተጠቅሰዋል። አንደኛ፤ ያህዌህ በህዝቡ መካከል በሃይል እየሰራም እንኳ ‘መኖራቸው’ የማይካድ እውነታ እንደ ነበር ብሉይ ይነግረናል። ነብዩ ኤርሚያስ እና ሕዝቅኤል ባገለገሉበት ዘመን፤ የሕዝቡን ልብ ለያህዌህ እንዳይገዛ ያደነደኑ ሐሰተኛ ነብያት ነበሩ (ኤር. 6:14; 8:11; 23:17; ሕዝ. 13:10, 16; ሚክ. 3:5)። እነዚህ ነብያት በሕዝቡ መካከል ምልክቶችን፤ ትንቢትን፤ የማጽናናትን ቃል እያመጡ ታዋቂነት ያተረፉ ሰዎች ነበሩ። በብዙኋኑ የተወደዱ እና እውነተኛ ነብያት ጥግ ይዘው እስኪቆሙ ድረሱ የበረቱም ነበሩ። ሁለተኛ ፤ (በተለይ ለይሁዳ መልክት ወሳኝ የሆነው ጉዳይ)፤ በብሉይ የነበሩ ሐሰተኛ ነብያት ገና ወደ ፊት ለሚነሱ አውራሐሰተኛ ነብያት ጠቋሚዎች ነበሩ። ልክ እውነተኛ ነብያቱ፤ ስለ ክርስቶስ እና በክርስቶስ ስለሚመረቀው ዘመን አስቀድመው ምልክት እንደነበሩ፤ እነዚህም ሐሰተኛ ነብያት በዘመን መጨረሻ (በክርስቶስ የመጀመሪያ ና ዳግም ምጻት ያለው ዘመን በጥቅሉ ለማለት ነው) ስለሚነሱ ነብያት አመልካቾች ነበሩ። ከዚህ አንጻር ነው ይሁዳ “ከብዙ ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንዶች ሰዎች ሾልከው ገብተዋልናያለን። ለምሳሌ ያህል ጳውሎስ በተመሳሳይ መልኩ መንፈስ ግን በግልጥ፤ በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፥ ሃይማኖትን ይክዳሉ ይላል (1 ጢሞ. 4:1–2)” መቼ ነው ይህ የተባለው? መንፈስ ቅዱስ ‘ከጥንት ጀምሮ’ ስለዚህ የመጨረሻ ዘመን ተናግሯል። ስለ ሐሰተኛ ነብያት ተጽፏል። ይመጣሉ። ሆንም ደግሞ አበክረን ልንናገር የሚያስፈልገው ነገር ቢኖር፤ ምንም እንኳ ሁለቱም (የብሉይ ሐሰተኛ ነብያት ይሁኑ የአዲሱ) በከባድ ፍርድ ቢወድቁም፤ ክህደታቸው ግን አንድ አይደለም። ስለዚህም የፍርዳቸው ክብደት ይለያያል። የንጉሱን መልክተኛ “እምቢ” ማለት ያው ንጉሱን አምቢ ማለት ነው። ደግሞ ንጉሱን ፊት ለፊት እያዩ “እምቢ” ማለት ደግሞ፤ ሌላ ደረጃ ነው። ሁለቱም በንጉሱ ላይ ማመጽ ነው። ሁለተኛው ግን በጣም ከባድ ፍርድ ላይ ይጥላል። ለዚህ ነው፤ ለምሳሌ ዕብራውያን ላይ “በመላእክት የተነገረው ቃል ጽኑ ከሆነ፥ መተላለፍና አለመታዘዝም ሁሉ የጽድቅን ብድራት ከተቀበለ፥ እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ መዳን ቸል ብንለው፥ እንዴት እናመልጣለን?” የሚለውን። ሁለቱም አለመታዘዝ ነው። ነገር ግን በልጁ ለመጣው መልክት እምቢ ማለት ደግሞ መዘዙ አይታሰብም። የብሉዩ ሐሰተኛ ነብይ መሆን አንድ ነገር ነው። የአዲስ ኪዳን ሐሰተኛ ነብይ መሆን ግን “የማይታሰብ” ጉዳይ ነው።

 

እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ (17-25)

ምንም እንኳ አማኖች “የተመረጡ’ እና “የተጠበቁ” ቢሆንም፤ ይህ ማስጠንቀቂያ ግን በፊታችን አለ። ይህም የተቀበልነውን ጸጋ እስከመጨረሻው የመጠበቅ ግዴታ ነው። ይህ ግዴታ የህይወትን ለውጥና የአስተምህሮትን ጥራት ገንዘቡ ያደረገ ነው። እናም፤ ለአማኞች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የተሰጠውን ሐይማኖት ለመጠበቅ እንታገል። ዕለት ዕለት ክርስቶስ ለመምሰል በቅድስና እንትጋ። እነዚህ ሁለቱ ገንዝቡ የሆኑ አማኝ “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት (ቁ.21)” በእውነት የእርሱ ነው። ከቁ.20-21 ላይ ያሉት የማበረታቻ ቃሎች አጽንዖት ያተኮረው “በእግዚአብሄር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ” በሚለው ዋና ግሥ ላይ ነው። ይህንን ለማድረግ አጃቢ ቃሎችን ተጠቅሟል፤ “በተቀደሰ ሃይማኖት ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ፣ በመንፈስ ቅዱስ እየጸለያችሁ፤ የኢየሱስን ምህረት ስትጠባበቁ...በእግዚአብሄር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ”። ቅዱሳን እርስ በርሳችን እየተደጋገፍን “በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችንን እንጠብቅ!”

“ሳትሰናከሉም እንዲጠብቃችሁ፥ በክብሩም ፊት በደስታ ነውር የሌላችሁ አድርጎ እንዲያቆማችሁ ለሚችለው ብቻውን ለሆነ አምላክና መድኃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም ይሁን፤ አሜን።

 

© 2017, Samson Tilahun. All rights reserved.

Like Be the first one who likes this post!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Top