Home / Portfolio / Articles / -1- የወንጌል ማዕከላዊነት

-1- የወንጌል ማዕከላዊነት

Posted on

መግቢያ

(አስቀድሜ እነዚህን መጣጥፎች ከእንግሊዝኛው በጥሩ አማርኛ ለተረጎመልን ለወንድማችን ለካሳሁን መኩሪያ ጌታ ይባርክህ እላለሁ። እነዚህ ተከታታይ ትምሕርቶች አስቀድሜ በእንግሊዝኛ አዘጋጅቼ ያቀረብኋቸው ናቸው።)

(If you would like to read the whole article in English, click here AcrobatPDF The Story of the Gospel)

‘ወንጌል’ የሚለውን ቃል በጣም ከመለመዱ የተነሳ ‘ወንጌል የብዙ ነገሮች ገላጭ ቃል ሆኖ ሲውል ይደመጣል። ሁልጊዜም እንደሚባለው፤ አንድ ቃል ብዙ ነገሮችን እንዲወክል በተጠቀምነው ቁጥር የቃሉ ይዘትና ክብደት ይቀንሳል። ለምሳሌ ያሕል፤ ጸጋ የሚለውን ቃል በንግግራችን CentralityOftheGospelእንዴት እንደምንጠቀመው እንመለከት። ዝናሽና አስቴር ወደ ዋናው አዳርሽ እየገቡ ሳሉ፤ ዝናሽ ዘወር ብላ ለአስቴር “ዛሬ ደግሞ በጣም አምሮብሻል!?” ትላታለች። ዝናሽ ደግሞ ትከሻዋን ነቅንቃ “ጸጋው ነዋ!” ትላታለች። ይህ እየሆነ ሳለ ሁለት አብሮ አደግ ጓደኛሞች ከተለያዩ ከብዙ ዓመት በኋላ በጌታ ሲገናኙ፤ እርስ በርሳቸው ተያይተው “የድሮው ሕይወታችን ትተን ትዳር ይዘን እንኖራለን!” ብለው ሲጥያየቁ፤ የሰጡትን መልስ አውቃችሁታል “ጸጋው ነው”። አበራ ደግሞ ከአምልኮ ፕሮግራም በኋላ ለዮሴፍ “ዛሬ ፕሮግራም ስትመራ ድምጽህ በጣም ቆንጆ ነበር” ሲለው የዮሴም መልስ ከዝናሽ የተለየ አይደለም። አሁንም መልሱን አውቃችሁታል። እነዚህ ሰዎች “ጸጋ” የሚለውን ቃል በተለያየ መልኩ አውለውታል። ለሁሉም በርቀት ሊሉ የፈለጉት ነገር፤ “ይህ የሆነልን ነገር ከእኛ ውጪ በሆነ አሰራር ነው” ለማለት ነው የፈለጉት። ዝናሽ ከዝነጣ ጋር፤ ዮሴፍ ከታለንት/ክሕሎት ጋር እንደዚሁም ደግሞ አብሮአደግ ጓደኛሞቹ ከሥነ-ምግባር ለውጥ ጋር አያይዘውታል። ከዚህ የተነሳ “ጸጋ” የሚባለው ቃል የትርጉም ቅርጹ መደብዘዝ ብቻ ሳይሆን ሰሚውን “እንዴ!? ይህ ጸጋ የሚባለው ነገር ምን ማለት ይሆን?” ብሎ እንዲጠየቅ ይገፋፉታል። ጸጋ ሁሉም ነገር ከሆነ ጸጋ ትርጉሙን ያጣል።

በአዲስ ኪዳን ግን “ጸጋ” የሚለው ቃል ውሱን ትርጉም ያለውና ቅርጽ ያለው ቃል ነው። እውነት ነው ጸጋ ነጻ-ሥጦታ ነው። ነገር ግን ነጻ የሆነ ማንኛውም ነገር ግን ጸጋ አይደለም። ጸጋን ጸጋ እንዲሆን ያደረገው በነጻ የተገኘው “ሥጦታው” ነው እንጂ ነጻ መሆኑ በቻ አይደለም። ጸጋ “እግዚአብሔር በሚወደው ልጁ፤ በክርስቶስ ኢየሱስ የመቤዠት ሥራ አማካኝነት የተገኘ ነጻ በረከት ነው።” ከዚህ የተነሳ ጸጋ በክርስቶስ ሕልውናና ሥራ ላይ ያነጣጠረ ነው።፡“በውድ ልጁም እንዲያው የሰጠን የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ ይህን አደረገ።በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት።ጸጋውንም በጥበብና በአእምሮ ሁሉ አበዛልን።” ስለዚህ ይህ አንዱ ጸጋ በእግዚአብሄር አብ አስቀድሞ አዋቂነት ከዘመን ዘመናት በፊት የተሰጠን፤ ይህም ስጦታ በእግዚአብሄር ወልድ የውጆት ሥራ የተከናወነ፤ ደግሞም ይህ አብ በነጻ የሰጠንን፤ ወልድ ደግሞ የፈጸመውን ስጦታ በእግዚአብሄር መንፈስ ቅዱስ የመቀደስ አገልግሎት አሁን በነጻ የምንካፈለውን በረከትና አሰራር አዲስ ኪዳን “ጸጋ” ይለዋል። ትርጉሙ መጠበቅ አለበት። ከላይ የጠቀስኳቸው ወገኖች ሁሉም ቃሉን በትክክል ተጠቅመውት ሊሆን ይችላል። ይህም ሊሉ የፈለጉት ነገር እንዲህ ከሆነ ብቻ ነው። ለዝናሽና ለአብሮ አደግ ጓደኛሞቹ “ጸጋ” ወደ አምላካቸው ተመልሰው ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን ከድሮ የመቅበዝበዝ ሕይወት ወጥተው ወደ ነፍሳቸው እረኛ ይመለሱ ዘንድ በልባቸው ላይ እንዲሁ በነጻ ከተለቀቀው መለኮታዊ ሐይል የተነሳ ያገኙት ለውጥ ለማለት ፈልገው ከሆነ፤ እሺ ይሁን አላለሁ። ምንም እንኳ ጸጋን በዚያው መልኩ እንዲጠቀሙ ባላደፋፍርም። ምክኒያቱም ትርጉሙ ድብስብስ ብሎ (domesticated ሆኖ) ቅርጹን እንዳያጣ ። ለዮሴፍም ያለኝ ምክር ድምጽ እግዚአብሔር ሲፈጥርህ ልጁን ታከብርበት ዘንድ የሰጠህ ታለንት እንጂ የጸጋ-ሥጦታ አይደለም። ግን ልትለው የፈለግከው፤ ወደ ጌታ ከመጣህ ጀምሮ ጌታን ለማክበር ከመፈለግህ የተነሳ እለት እለት ድምጽህን እየሳልሀው አሁን ጥሩ መዘመር ከቻልህ፤ ልትል የፈለከው ገብቶኛል። ምክሬ ግን አሁንም ያንን ቃል በርሱ ላይ ባታውለው መልካም ነው። የቃሉ ዋና ትርጉም አንዳይደበዝዝብህ!

ወንጌልን መተርጎም ያስፈልግ ይሆን?

በዚሁ መልኩ “ወንጌል” የሚለውም ቃል በሁሉ ነገር ላይ ከተጠቀምነው የወንጌል ይዘትና ቅርጽ ይደበዝዝብናል። መጽሀፍ ቅዱስ ወንጌልን “የእግዚአብሔር የጸጋው ወንጌል” ይለዋል። ይህ ማለት ወንጌል ስለ እግዚአብሔር የነጻ ስጦታ የሚያውጅ የምስራች ቃል ነው። ከላይ እንዳየነው ጸጋ እግዚአብሔር ስለክብሩ ሲል ለዚህ ለጠፊው ዓለም የሰጠው የነጻ-ሥጦታ የሆነው አንድያ ልጁ ነው። ስለዚህ አሁንም “ወንጌል” የሚለውን ቃል በሁሉም ነገር በፈለግነው መንገድ ስንጠቀምበትና እንዲገባን በመረጥነው መንገድ ስንረዳው፣ ወንጌል እንደ ተራ-ብሂል ይሆንብናል። ይህም ለማለት በፈለግነው ነጥብ ላይ በማተኮር ግልጽነት በጎደለውና በተድበሰበሰ መንገድ ወንጌል ነጥባችንን እንዲደግፍልን ትርጉሙን ስንለጥጠው ነው።

በመጀመሪያ ደረጃ ወንጌልንና ወንጌል ከእኛ የሚፈልገውን ወይም ወንጌልንና ወንጌል በሕይወታችን ከሚያፈራው ፍሬ መለየት አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ያህል የቀረበው የቃል አገልግሎት ጠንከር ብሎ “ራስ መካድና የራስን መስቀል ይዞ መከተልን ቢያካትት “የዛሬው መልእክት ንጹ ወንጌል ነበር” የሚል አነጋገር መስማት የተለመደ ነው። ይሁን እንጂ እንደዚህ ያለው የቅድስና-ሕይወት-ግዴታ ራሱ ወንጌል በእኛ ውስጥ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የሚያፈራው ፍሬና ከዳንን በኋላ ላዳነን ጌታ የምንመልሰው አማራጭ-የለሽ አጸፋ ነው እንጂ ወንጌል አይደለም። የዳንነው ወንጌልን አምነን ነው፤ ቅድስና ወንጌል ከሆነ የምስራቹ ቃል “ለመዳን ተቀደሱ” ማለት ይሆንብናል። እንደዚህ ከሆነ ደህንነት ስጦታ ሳይሆን ደሞዝ መሆኑ ነው። ይህን ስል በቅድስና ላይ ላላ ማለቴ አይደለም። በተቃራኒ የወንጌልን ቃል ይዘት መጠበቃችን ወንጌሉ በብዙ ሐይል እንዲሰራ መንገድ ይከፍትለታል። “በወንጌል አላፍርምና፤ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው፥ ለሚያምኑ ሁሉ ለማዳን የሚችል የእግዚአብሔር ኃይል ነውና።” አያችሁ፤ የወንጌሉ ቃል፤ ባዶ ቃል አይደለም ለመቀደስ፤ ለመለውጥ የሚችል “ሐይል” ነው፡፤ ይህ ሐይል እንዲሰራ ግን የወንጌል ይዘቱ በንጽህና መጠበቅ አለበት። የገላትያ ቤተ/ ክርስቲያን ችግር የወንጌሉን ይዘት መቀነሷ ሳይሆን በክርስቶስ ላይ መጨመሯ ነበር። ከዚህ የተነሳ የተጨመረበት ወንጌሏ “በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ ወደ ልዩ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ እንዴት እንዳለፋችሁ እደነቃለሁ፤ ….ይህን ብቻ ከእናንተ እንድማር እወዳለሁ፤ በሕግ ሥራ ወይም ከእምነት ጋር በሆነ መስማት መንፈስን ተቀበላችሁን? ….ልጆቼ ሆይ፥ ክርስቶስ በእናንተ እስኪሣል ድረስ ዳግመኛ ስለ እናንተ ምጥ ይዞኛል። …ስለ እናንተ አመነታለሁና አሁን በእናንተ ዘንድ ሆኜ ድምፄን ልለውጥ በወደድሁ።ስለዚህ ወንጌልና ወንጌል ከእኛ የሚፈልገውን ወይም ወንጌልንና ወንጌል በሕይወታችን ከሚያፈራው ፍሬ/ውጤት መለየት አለመቻል ሲስተዋል “ወንጌል ምንድነው?” የሚለውን ጥያቄ መመለስ ግድ ይሆንብናል።

በሁለተኛ ደረጃ፤ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ “ወንጌል” የሚለው ቃል የክርስቲያን መሰረታዊና የመጀመሪያ አስተምህሮቶች (እምነት፤ መዳን፤ የክርስቶስ ሞትና ትንሣዔ፤ የኃጢአት ስርየት፤ ጥምቀት፤ ወዘተ…) በመወከል የጥቅል መጠሪያ ስም ሆኖ ጥቅም ላይ ሲውል ይደመጣል። ከዚህ የተነሳ ወንጌል ለአዳዲስ ክርስቲያኖችና ገና ላልበሰሉ ሕጻናት የሚሰጥ የመጀመሪያ ወተት ይሆንብናል (የደሕንነት/የጥምቀት ትምህርት)፤ አጥንቱ ግን በሌላ ጠንከር ባሉና አዳዲስ ነገሮች ላይ ያርፍብናል። ስለዚህ ቅዱሳን ልንጠነቀቅ ያስፈልጋል ማለት ነው። ከዚህ የተነሳ ወንጌል የክርስቲያን ህልውናና ሁለንተና የሚያካትት፤ ብሎም ለዕለት-ዕለት ሕይወታችን በቂ የሆነ፤ ሁሉን አቀፍ እውነታ መሆኑ ላይታየን ይችላል። ነገር ግን በክርስቶስ የተወደዳችሁ ቅዱሳን የክርስቶስ ወንጌል የሕይወትን ሁለንተናዊ ይዘትና ቅርጽ የምናይበት ሁሉን አቀፍ የሆነ ንጽረት-ዓለም ነው። ወንጌል የሰውን አስተሳሰብ የሚቃኝ (ቆላ 3:1-2፤ ሮሜ 12:1-4)፤ የሕይወትን አቅጣጫ የሚቀይስ (ኤፌ 2፡ 11-19፤ 1ጴጥ 2፡9-10 )፤ የቤተክርስቲያን ተልዕኮ (ማቴ 28:18-20)፤ የቤተሰብ መዋቅር ንድፍ (ኤፌ 5፡21-6:9)…ወዘተ… ነው። ወንጌል ጠቅላላ ኑሮአችንን የሚቃኝ መሪ ነው።ወንጌል ሁሉን ይቃኛል፤ ነገር ግን ራሱ በምንም አይቃኝም። ወንጌል የእግዚአብሔር ጥልቅ ሚስጥር አሰራር ነው። አስተውላችሁ ከሆነ “የእግዚአብሔር ጥልቅ ነገሮች” የምንላቸው ትኩረታቸው በወንጌል ላይ አይደለም። ብዙ ጊዜ ወንጌል ማለት የክርስትና መጀመርያ ሲሆን አማኞችም ወዲያው በአፋጣኝ ሁኔታ “ የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገሮች” ወደ ማወቅ እንዲሻገሩ ይበረታታሉ። ከላይ እንዳየነው እነዚህ “ጥልቅ ነገሮች” ከወንጌል ውጭ ያተኮሩ ናቸዉ። ሁኔታው በቅርበት ሲታይ ግን ወንጌል የሚያስፈልገው ላልዳኑ ነፍሳት ወይም ለአዲስ አማኝ ብቻ የተባለ ይመስላል። በዚህ አመለካከት መሰረት የክርስቲያን እድገት የሚለካው አማኙ በሂደት ውስጥ “የእግዚአብሔር አምሳል የሆነውን ክርስቶስን ፣ የክብሩን ወንጌል ብርሃን ( 2 ቆሮ. 4፥ 4)” ምን ያህል ለማየት መቻሉን በመለካት አይደለም። ወይም የአንድ አማኝ እድገት አማኙ ስለወንጌል ጥልቅ ምስጢር ምን ያህል ጭብጥ እንዳገኘ በመመዘን አይለካም። ስለዚህ ጉዳይ ሐዋርያው ጳዉሎስ ሲጸልይ ግን፤

“ የክርስቶስ ፍቅር ስፋቱ፣ ርዝመቱ ፣ከፍታውና ጥልቀቱ ምን ያህል እንደሆነ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር የመገንዘብ ኃይልን እንድታገኙ ነው” ( ኤፌ. 3፥14-19) ብሎአል ።

ሐዋርያው ጳውሎስ ስለዚህ ወንጌል እንዲህ ብሏል፤

“ከዘመናትና ከትውልዶች ተሰውሮ ምስጢር ሆኖ ቆይቶ አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጧል”( ሮሜ. 16፥25-26፤ ቆላ.1፥26)

ይህን መገለጥ እንዲያስተምር ለጳውሎስ በኃላፊነት የተሰጠው ሲሆን ይህም፤

“ተሰውሮ የነበረውን የእግዚአብሔርን ምስጢር ጥበብ ነው፤ ይህም ጥበብ እግዚአብሔር ከዘመናት በፊት ለክብራችን አስቀድሞ የወሰነው ነው ” ( 1 ቆሮ. 1፥26)።

ያም…

“ እግዚአብሔር የዚህ ምስጢር ክብር ባለጠግነት በአሕዛብ መካከል ምን ያህል እንደሆነ ለማሳወቅ መረጠ፤ እርሱም የክብር ተስፋ የሆነው በእናንተ ውስጥ ያለው ክርስቶስ ነው። ….ይህም ምስጢር አሕዛብ በወንጌል አማካኝነት ከእስራኤል ጋር አብረው ወራሾች፣ አብረው የአንዱ አካል ብልቶች፣ እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነው ተስፋ አብረው ተካፋይ መሆናቸው ነው” ( ቆላ. 1፥27፣ ኤፌ.3፥6)።

ይህ ሁሉ የተሰራው…

“ሞትን ደምስሶ በወንጌል አማካይነት ሕይወትንና ኢመዋቲነትን ወደብርሃን ባመጣው በጌታችን በኢየሱስ መምጣት “ ነው (2ጢሞ. 1፥10)።

ሐዋርያው ጳውሎስ ሲደመድም…

“ በወንጌል አላፍርም፣ ምክንያቱም ለሚያምን ሁሉ ለድነት የሚሆን የእግዚአብሔር ኃይል ነው” (ሮሜ. 1፥16) ብሏል።

– ወንጌል እንደ ንጽረተ-ዓለም –

እነዚህ እንግዲህ የእግዚአብሔር ቃል ስለ ወንጌል ከሚመስክራቸው ለናሙና ያህል የተወሰዱ ናቸው። እውነቱ ግን ወንጌል የእግዚአብሔር አላማ ምስጢር ሲሆን ይህም ለዘመናት ተሰውሮ የቆየ አሁን ግን በክርስቶስ መምጣት ይፋ ሆኖ የሚታወጅ የምሥራች ቃል ነው። ይህም በእርሱ ሕልወትና ሥራ በክብር ተገልጧል፤ (ይህም መገለጥ በቅደም ተከተል:- በሕልወተ ክርስቶስ ፣ በሰራቸው ተአምራት፣ በሞቱና በትንሳኤው እንደዚሁም በዳግም ምጽዓቱ ላይ የተመሰረተ ነው)።  የእግዚአብሔር ቃል ስለ ወንጌል-ተቀዳሚነትና ዋነኛነት ብዙ ምስክርና ማስረጃ ቢያቀርብም እኛ ግን አዲስ ኪዳን ልዩ ትኩረት በመስጠት በግንባር ቀደምትነት የሚያስቀምጠውን ወንጌል በሞላ ጎደል ያነሰ ትኩረት ስንሰጠው፤ በአንጻሩ ደግሞ አዲስ ኪዳን መለስተኛ ትኩረት የሚሰጣቸውን ነገሮች ግምባር ቀደም አድርገናቸው አብይ ትኩረት ስንሰጣቸው እንታያለን። በምድር ላይ የተሳካና በድል የተሞላ ኑሮ ለመምራት የሚያስችለንን “ቁልፍ” ነገር ያለማሰለስ እንፈልጋለን። እስከ አሁን ብዙ “ቁልፎች” ተገኝተዋል፤ እነርሱም በሌላ አዲስ “ቁልፎች” ተተክተዋል። እንደብርቅ ታይተው የተጠበቁ ብዙ ዘዴዎችና ብልሃቶች ተስተምረዋል። ይህ ሲሆን ግን ገና ከጅምሩ ወደ ኋሊት ወደ ሕግ-አጥባቂነት/አትንካና አትቅመስ (legalism) እያመራን መሆናችንን አላስተዋልንም። ልባችን ከጨበጥነው ያለፈ የተለየ አዳዲስ ተግዳሮቶችን ይመኛል (to-do-list) ይፈልጋል። ይህን ስናደርግ ግን የጥንቱን አሮጌው ነገር በዑደት (recycling) ውስጥ እያለፈ እንደሆነ አንገነዘብም። አትንካና አትቅመስ በጓሮ በር ገብቶ በፊት ለፊት ፀጉሩን ለውጦ ሲወጣ እንደ አዲስ አስተርእዮ ስንቀበለው ከረዥም ጊዜ በፊት ጀምሮ ራስን ለመርዳትና በራስ ለመጽደቅ ጥቅም ላይ የዋለ መሆኑን አናስተውልም። ይሁን አንጂ፤ ከእነዚህ ዘዴዎችና ብልሃቶች፤ የተለወጠች ሕይወት መኖር እንደሚገባት አዲስ ኪዳን የሚያዘውን መንገድ አንዳቸዉም የሚተኩ ቀርቶ በርቀት እንኩዋን የሚቀርቡት አይደሉም።  ዘዴ ሕይወትን አይቀይርም። ኢየሱስ ግን ሕይወትን ይለውጣል። ኢየሱስ የቅዱሳት መጻሕፍት ማዕከለኛ ነው “መጻሕፍት…ስለ እኔ ይመሰክራሉ!” ዮሐ 5፡ 39

እንደ ሰው ሥርዓትና ትምህርት። አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ ለሚሉት ትእዛዛት በዓለም እንደምትኖሩ ስለ ምን ትገዛላችሁ? እነዚህ ሁሉ በመደረግ ሊጠፉ ተወስነዋልና።  ይህ እንደ ገዛ ፈቃድህ በማምለክና በትሕትና ሥጋንም በመጨቆን ጥበብ ያለው ይመስላል፥ ነገር ግን ሥጋ ያለ ልክ እንዳይጠግብ ለመከልከል ምንም አይጠቅምም…እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ።  በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም።

ወንጌል ግን የመለወጥ ሐይል ያለው የጉልበት ቃል ነው። በጨለማ ብርሃን ይሁን ብሎ በቃሉ የፈጠረው እግዚአብሔር አሁን በወንጌል ቃል ብርሃን ይሁን ይላልና ነው። ሳይመለሱ የቀሩ ጥያቄዎች ዛሬም እንዳሉ ናቸው፤ “ታዲያ ከእነዚህ ዘዴዎች ባሻገር ወንጌል ውስጣዊ ማንነታችንን መለወጥ የሚችል በቂ ኃይል አለው ወይስ የለውም? ወንጌል የእግዚአብሔር ኃይል አይደለምን? ዘዴዎች ሳይለጠፉበት ብቻውን የመስቀሉ ቃል የውስጥ ማንነታችንን የመለወጥ ኃይል አለው አይደለምን?”

በሌላ በኩል፣ የሐዋርያው ጳውሎስን “ወንጌል” የሚል ቃል አጠቃቀም ስንቃኝ ሙሉ በሙሉ የተሳሳትን መሆናችንን እንገነዘባለን። አዎ! በእርግጥም የሚያስፈልገን ወንጌልና ወንጌል ብቻ ነው፤ በሕይወታችን የወንጌልን አስፈላጊነት ስንናገር በማናቸዉም መመዘኛ ያለልክ ያጋነንነው ሆኖ ሊታየን አይገባም፣ እስቲ አነዚህን እናስተውል፤

  • የእግዚአብሔር ወንጌል (ሮሜ 1:1; 15:16; 2 ቆሮ 11:7; 1ተሰ 2:8; 1ተሰ 2:9; 1 ጴጥ 4:17)
  • የእግዚአብሔር መንግስት ወንጌል (ማቴ 24:14)
  • የክርስቶስ ወንጌል (ሮሜ 15:19 ; 9:12; 2 ቆሮ 2:12; 9:13; 10:14; ገላ 1:7; ፊል 1:27; 1 ተስ3:2)
  •  የሰላም ወንጌል (ኤፌ6:15)
  •  የድነት ወንጌል (ኤፌ 1:13)
  • የጌታችን ወንጌል  (2 ተስ 1:8)
  • የእግዚአብሔር ልጅ ወንጌል (ሮሜ 1:9)
  • ብሩክ የሆነው የእግዚአብሔር ክብር ወንጌል (1 ጢሞ 1:11)
  • የክርስቶስ ክብር ብርሃን ወንጌል (2 ቆሮ 4:4)
  • የጸጋ ወንጌል (ቆላ. 1:6)

ጳዉሎስ እንደሚያስገነዝበን ወንጌል ለክርስትያን ሁሉን አቀፍ እውነታ ነው። ሁሉንም ነገር የሚይዝና የሚሸፍን ድንኳን ነው። ወንጌልን ተምረን ልንጨውርሰው አንችልም። የወንጌልን ምስጢርና ጥልቀት ሙሉ በሙሉ ማወቅ አንችልም። ምንጩ ዘላለማዊ የሆነው ሱሉስ አምላክ እንደመሆኑ ወንጌል የሚደረስበት ዳርቻ የለውም።

“…. መጽሐፉን ልትወስድ ፣
     ምሕተሞቹን ልትፈታ ይገባሃል፣
ምክንያቱም ታርደሃል፣
      በደምህ ከነገድ ሁሉ፣ ከቋንቋ ሁሉ፣
    ከወገን ሁሉ፣ ከህዝብ ሁሉ
  ሰዎችን ለእግዚአብሔር ዋጅተሃል።
ለአምላካችንም መንግስትና ካህናት አድርገሃቸዋል፤
እነርሱም በምድር ላይ ይገዛሉ።” (ራዕ. 5፥ 9፣ 10)

አንድ ጸሃፊ አንዴት ቤተ ክርስቲያን ከእምነት ወደ ስህተት እንደምታመራ ሲጽፍ እንደዚህ አለ:

“ቤተ ክርስቲያን ከጤናማ ትምህርት ወደ ክህደት እንድታፈገፍግ ሶስት ትውልድ ይጠይቃል። የመጀመሪያው ትውልድ በታማኝነትና በሕይወት ይጠብቀዋል፡ ሁለተኛው ትውልድ ግን የመጀመሪያውን ትውልድ መንፈሳዊ ጎን ተደግፎ፤ ጤናማውን ትምህርት ያምናል ነገር ግን በአጽንዖት አያውጀውም፤ አጽንዖቱና ትኩረቱ ግን በትርፍ ነገሮች ላይ ይሆናል። ሶስተኛው ትውልድ ግን ዋናውን ትምህርት፤ ሁለተኛው ትውልድ አጽንዖት ያደረገበት ትርፍ ነገር ላይ ይሆንና፤ ጤናማውን ግን ይክዳል።”

ለዚህ ቀውስ ተጠያቂ ማነው? ሁለተኛው ትውልድ ነው። ትኩረቱ ያነጣጠረው በዋናው ነገር ላይ ስላልሆነ ነው። ለዚህ ነው ብዙዎቻችን ከእንቅልፍ የመንቃት ያሕል “እንዴት እዚህ ደረስን?” ብለን እየጠየቅን ነው። በርግጥ በሦስተኛው ትውልድ ላይ ቆመናል። እንዴት ነው በሺዎች የሚቆጠሩ የሚታደሙበት ጉባኤ ላይ ከሳምንት እስከሳምንት ክርስቶስ ሳይሆን “አይዞህ በርታ…ትችላለህ…ትወርሳለህ…ትፈወሳለህ…ሀብታም ትሆናለህ…’ነው ያልሀው ይሆናል’…’ቃልህ ይፈጥራል’…’እንደ እግዚአብሔር ያለ እምነት ያዝ’…!” ሑለት ነገሮች ይተኮሩ ዘንድ ይገባል፤ እኛ አምላክ ስላይደለን ቃላችን የመፍጠር ጉልበት የለውም። ከአንዱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ቃሉ የመፍጠር ጉልበት ያለው ፍጡር የለም። ይህ ራሳችንን ጣዖታት ማድረጋችን ነው። (ለዚህ ነው እምነት የሰው እድል ፈንታ የሆነው። እምነታችን ተናግሮ በሚፈጥረው አምላክ ላይ ነው) ሁለተኛ እግዚአብሔር “በእምነት አይሰራም፤ እርሱ ማንንም አያምንም። እምነት ማለት መታመን፤ መደገፍ ማለት ነው። ለዚህ ሁሉ መፍትሔው ሐዋርያው በኤፌሶን ከሦስት ዓመታት በላይ ያደረገውን አርዓያ አድርገን ብንወስድ ይረዳናል፡

“የእግዚአብሔርን ምክር ሁሉ ነግሬአችኋለሁና፥ ምንም አላስቀረሁባችሁም።  በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ስለዚህ ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሠጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ።  አሁንም ለእግዚአብሔርና ያንጻችሁ ዘንድ በቅዱሳንም ሁሉ መካከል ርስትን ይሰጣችሁ ዘንድ ለሚችል ለጸጋው ቃል አደራ ሰጥቻችኋለሁ።(ሐዋ 20:27–32)

..በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበርና…እምነታችሁም በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ እንዳይሆን፥ ቃሌም ስብከቴም መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነበረ እንጂ፥ በሚያባብል በጥበብ ቃል አልነበረም።

…እኛም በክርስቶስ ፍጹም የሚሆን ሰውን ሁሉ እናቀርብ ዘንድ ሰውን ሁሉ እየገሠጽን ሰውንም ሁሉ በጥበብ ሁሉ እያስተማርን የምንሰብከው እርሱ ነው።…

ስለዚህ ከሁሉ አስቀድመን አንድ ማድረግ የሚገባንና የምንችለውም ነገር አለ፤ ይህም የብሩክ እግዚአብሔርን የክብር ወንጌል ምን እንደሆነ ለመማር (1 ጢሞ. 1፥ 11) በቂ ጊዜ መወሰን መቻል አለብን። በዚህ በቁርጠኝነት በወሰነው የመማር ጊዜና ሂደት ውስጥ ክርስቲያናዊ ህልውናችን ከወንጌል የተገኘና በንጌልም ላይ የተመሰረተ መሆኑን የምንደርስበት አብይ ነጥብ ይሆናል። ወንጌል የማንነታችንና የህልውናችን ማዕከል እና በዚህ ሕይወት ለምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ የብርታታችን ብቸኛ ምንጭ መሆኑን ማወቅ አለብን። ከዚህ ጋር በማያያዝ የተወደዳችሁ የክርስቶስ ቅዱሳን፤ እነዚህ ነገሮች ስለማታውቁ አልጽፍላችሁም፤ ነገር ግን በሐዋርያው ጴጥሮስ ቃል ላበረታታችሁ እውዳለሁ “ ወዳጆች ሆይ፤ ይህ አሁን የምጽፍላችሁ….ቅን ልቦናችሁን እንድታነቃቁ ለማሳሰብ ነው፤ ደግሞም ቀድሞ በቅዱሳን ነቢያት የተነገረውን ቃል እንዲሁም በሐዋርያታችሁ አማካይነት በጌታችንና በአዳኛችን የተሰጠውን ትዕዛዝ እንድታስቡ ነው” ( 2ጴጥ.3 ፥ 1-2)

(ከዚህ ቀጥሎ ወንጌል በብሉይ ኪዳን እንዴት እንደተሰበከ በክፍል ሁለት እንመለከታለን)

© 2013 – 2014, Samson Tilahun. All rights reserved.

Like Be the first one who likes this post!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Top