Home / Portfolio / Articles / የኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነት ሐቲት: ክፍል አንድ

የኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነት ሐቲት: ክፍል አንድ

Posted on

ኢየሱስ ግን። አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ ብሎ መለሰላቸው።  እንግዲህ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ደግሞ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ። እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ፥ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር።  ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና። አብ ወልድን ይወዳልና፥ የሚያደርገውንም ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ትደነቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራ ያሳየዋል።  አብ ሙታንን እንደሚያነሣ ሕይወትም እንደሚሰጣቸው፥ እንዲሁ ወልድ ደግሞ ለሚወዳቸው ሕይወትን ይሰጣቸዋል።  ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ፥ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም። ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም።  እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም።  እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ።  አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና።  የሰው ልጅም ስለ ሆነ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን ሰጠው።  በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ።  እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ ፍርዴም ቅን ነው፥ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና። (ዮሐ 5: 17-30)

መግቢያ

የደቀ መዝሙርነት/ የደህንነት መሠረቱ ሆነ መስፈርቱ አሊያም ዓላማው እግዚአብሔር ከልጁ ጋር ያለው የፍቅር ግንኙነትና ጥምረት ነው! የዚህን ሚስጢር መረዳት የህይወታችንን ዓላማ ከመረዳት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው።

ዮሐ 17፡ 23-26:  “የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ፤ እንዲሁም ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ያውቃል። አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ እኔ ባለሁበት የሰጠኸኝ እነርሱ ደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ። ጻድቅ አባት ሆይ፥ ዓለም አላወቀህም፥ እኔ ግን አወቅሁህ  እነዚህም አንተ እንደ ላክኸኝ  አወቁ፤ እኔንም የወደድህባት ፍቅር በእነርሱ እንድትሆን እኔም በእነርሱ፥ ስምህን እንዲያውቁ አድርጌላሁ፤ እንዲአውቁም አደርጋለሁ አስታውቃቸውማለሁ።”

ደ/መዛሙርቱ የተወደዱበት መወደድና ልኩ ወልድ የተወደደበት ፍቅር ነው (ቁ 23):

“አብ እንደ ወደደኝ እኔ ደግሞ ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬ ኑሩ። 10 እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር፥ ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ። 11 ደስታዬም በእናንተ እንዲሆን ደስታችሁም እንዲፈጸም ይህን ነግሬአችኋለሁ።” (ዮሐ 15: 9-11 ) (ማብራሪያ ቁ.2/ ምስል 1 ይመልከቱ)

 • ወደ ዘላለም መንግስቱ የምንገባው የኢየሱስን ክብር ለማየት ነው – ክብሩም ዓለም ሳይፈጠር የተወደደበት መወደድ ነው (ቁ 24)
 • የኢየሱስ አባቱን ማወቁ ኢየሱስ “የተላከ” መሆኑን ደቀ መዛሙርቱ ከማወቃቸው ጋር ይነጻጸራል-ቁ25 (ይህም የሰውን ልጅ ማን ይሉታል…)
  • ዮሐ 10፡14-15  መልካም እረኛ እኔ ነኝ፥ አብም እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ ነፍሴንም ስለ በጎች አኖራለሁ።
  • ዮሐ 17፡3  እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።
 • ዮሐ 17: 20-23  ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ፥ ከቃላቸው የተነሣ በእኔ ስለሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለ እነዚህ ብቻ አልለምንም፤ አንተ እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ፥ አንተ፥ አባት ሆይ፥ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፥ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ። እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ፤ እኔም በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ፥ የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ
  • የደ/ መዛሙርቱ አንድነት የተመሰረተው በአብ-ወልድ አንድነት ነው
  • የደ/ መዛሙርቱ ተልዕኮ የተመሰረተው አብ-ወልድን የላከበት ዓላማ ነው: “ወደ ዓለም እንደ ላክኸኝ እንዲሁ እኔ ወደ ዓለም ላክኋቸው፤ 17: 18

የኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነት <“…እግዚአብሔር አባቴ ነው…”፤

1- ኢየሱስ የሰንበትን ሕግ ስለመሻሩ የቀረበ ክስ:- <ስለዚህም በሰንበት ይህን ስላደረገ አይሁድ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር ሊገድሉትም ይፈልጉ ነበር። >ለ38 ዓመት በሽተኛ የነበረው ሰው መፈወስ (ቁ8 – 10)ና አልጋውን መሽከም የሥልጣን ጥያቄን ቀሰቀሰ

 • ይህም አስደናቂ ታምራት -“ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው”- በሚለው፦ ትዕዛዝንና ሃይልን ባዘለ “ቃል” ተከናውኗል።
 • ዓራተኛው ምልክት መሆኑን ነው።  (ማብራርያ ቁ. 1 ይመ.) የሰንበት ዓላማና ምንነት በወግና በትወፊት መቀየጡ፤ አይሁድ በዚህ ጊዜ ወደ 39 የሚጠጉ የሰንበትን ደንቦችን አውጥተው ነበር፤
 • ከነዚህም ትውፊት አንዱ ስለ ሸከም ነበር፤ ሸክም እስከትከሻ ከደረሰ እንደ – ሥራ- ይቆጠር ነበር። ነገር ግን ብሉይ ስለ ሰንበት የሚከለክለው “የሙያ ሥራን” ነው። ይህ ቀን ለእ/ር የተቀደሰ “የዕረፍት” ቀን ነውና (ዘፍ 2፡ 2-3፤ ዘፀ 20፡ 11፤ ዘዳ 5፡ 12-15፤ ዕብ 4፡ 3-10) ሰንበት በሥድስቱ ቀናቶች የሚሰራውን ሥራ በሰባተኛው እንዳይሰሩ ያዛል
 • ጥያቄው እ/ር በሰባተኛው ቀን አረፈ ይላልና፤ ‘እ/ር ሰንበትን ያከብራል?’

2- ኢየሱስ ጉዳዩን ከሰንበት ጥያቄ ወደ ማንነት ጥያቄ ለወጠው ፡ <ኢየሱስ ግን። አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ ብሎ መለሰላቸው።>

 • ኢየሱስ ለዚህ ለቀረበበት ክስ በተለየ መልኩ መመለስ ይችል ነበር፡ ለምሳሌ:
  • ሕግ ቅደም ተከትልን ያስተናግዳልና መፈወስ ተፈቅዷል ብሎ መመለስ ይችል ነበር:  “ኢየሱስ መለሰ አላቸውም። አንድ ሥራ አደረግሁ ሁላችሁም ታደንቃላችሁ።  ስለዚህ ሙሴ መገረዝን ሰጣችሁ፤ ከአባቶችም ነው እንጂ ከሙሴ አይደለም፤ በሰንበትም ሰውን ትገርዛላችሁ።  የሙሴ ሕግ እንዳይሻር ሰው በሰንበት መገረዝን የሚቀበል ከሆነስ ሰውን ሁለንተናውን በሰንበት ጤናማ ስላደረግሁ ትቈጡኛላችሁን?  ቅን ፍርድ ፍረዱ እንጂ በመልክ አትፍረዱ። (ዮሐ 7፡ 21 -24)”
  • የሰው ልጅ በሰንበት ላይ ሥልጣን አለው  ብሎ መመለስ ይችል ነበር – ማር 2፡ 23-28
  • በሰንበት መልካም ማድረግ ተፈቅዷል ብሎ መመለስ ይችል ነበር – ለ18 ዓመት የጎበጠችዋ ሴት መፈወስ
  • የኢየሱስ መልስ ግን ምልልሱን ወደ ሚፈልገው አቅጣጫ እንዲያመራ አደረገ: “ኢየሱስ ግን። አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ ብሎ መለሰላቸው።” እግዚአብሔር አባቴ ብሎ በግሉ መጥራቱና በሰንበት “ለመስራቱ” መብትና ሥልጣን መሰረት ያደረገው “የአባቱ መሥራት” ነው።

3 – እግዚአብሔርን አባቱ በማድረጉ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር ማስተካከሉ: <እንግዲህ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ደግሞ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ። እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ፥ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር።>

 • በብሉይ ራስን እንደ አምላክ ማድረግ ትልቅ ፍርድን ያስከትላል፡- ፈርዖን የግብጽ ንጉስ (ሕዝ. 29:3)፤ የጢሮስ ገዥ (ሕዝ. 28:2) ፤ ናቡከደነፆር የባቢሎን ንጉስ (ኢሳ 14: 14)
 • አይሁድ በዚህ ወቅት እጅግ ከሚገባው በላይ “ለአምልኮተ ጣዖት” ጠንቃቃ ነበሩ። እስራኤል ለምርኮ ታልፋ የተሰጠችው በዚህ ሐጥያት ሥለነበር በዚህ ረገድ ጥንቃቄ ያደርጉ ነበር
 • ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ ይህም “እግዚአብሔርን አባቱ በማድረጉ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር ማስተካከሉ
 • ኢየሱስ ከአብ ‘በተነጠለ’ መልኩ፤ ሁለተኛ አምላክ (እ/ር ቁ. 2) ተደርጎ ሊወሰድ አንደማይገባ በሚቀጥሉት ክፍሎች (ከቁ 19 ጀምሮ) ያብራራል
  • ይህም ኢየሱስ ከአብ ሳይነጠል ነገር ግን ከአብ ጋር “እኩል” መሆኑን እንዴት አድርገን መረዳት እንዳለብን ያስጠነቅቃል! ይህ ዝንጉነት እነዚህን ቤተ እምነቶችን ወደ ስትህተት መርቷቸዋል  Jehovah Witness/ Mormon v. Islam
  • አይሁድ ግን የገባቸው በነጠላነት “አምላክ” መሆኑን ነበርና ሊገድሉት ፈለጉ። ጉዳዩ ከክስ ወደ ግድያ አመራ።

ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ስንል ታድያ ምን ማለታችን ነው? እግዚአብሄር ልጅ አለው?

 • መላዕክት የእ/ር ልጆች ተብለዋል፤ (ኢዮ 1፡ 6፤ 38:6-7) በተጨማሪም የሙሴ ኪዳን የተሰጠው በመላዕክት መካከለኛ ዕጅ ነበርና መላዕክት በአይሁድ ሥፍራ ነበራቸው።
 • የባሕርይና የግብር አንድነት፦
  • አሁን ባለንበት በሠለጠነው ዓለም “ልጅ” ሲባል በመጀመሪያ ወደ አይምሮአችን የሚመጣው “የዘር ልጅነት” ነው። የደምና የሥጋ ወህደት ነው። ልጆች የገዛ ዝንባሌአቸውንና ፍላጎታቸውን እንጂ የወላጆቻቸውን ፈለግ እንዲከተሉ አይደፋፈሩም ወይንም አይገደዱም። ነገር ግን በጥንታዊው ዓለም “ልጅ” በሁሉ-ረገድ የአባቱን ፈለግ የሚከተል ነው። የአባትና የልጅ ግንኙነትም “በደምና በሥጋ” ጀምሮ የሚያበቃ  አንድነት ብቻ አልነበረም። ሥለሆነም ልጅ በጥንታዌው ዓለም፡
   • የአባቱን የባሕርይ ፈለግ ይወርሳል –  (ዘጸ 34 የአባቶችንም ኃጢአት በልጆች እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድም በልጅ ልጆች የሚያመጣ አምላክ)
   • የአባቱን መንገድ (የአኗኗር ዘዬ) ይወርሳል – (የአባቱን የዳዊትን መንገድ ተከተለ፤
    የአክዓብን መንገድ ተከተለ)
   • የአባቱን ሙያ ይወርሳል (የያዕቆብና የዮሐንስ አባት ዘብድዮስ አሳ አጥማጅ ነበር ልጆቹም አሳ አጥማጆች ነበሩ፡ ኢየሱስ የአናጺው የዮሴፍ ልጅ ተብሎ ይጠራ ነበር ኋላም ራሱ፡ “አናጺው ኢየሱስ አይደለምን?”)
  • ጽድቅ የሆነውን ነገር የሚያደርጉ በዚያ ረገድ የእ/ር ልጆች ያሰኛቸዋል ማቴ 5፡9 / 1 ዮሐ 3፡ 8-10 (በእኩይ ሥራ ጸንቶ እየኖረ አንድ ሰው እምነት ስላለኝ ከእ/ር ልጆች ጋር እቆጠራለሁ ማለት አይችልም
  • ክፉ የሆነውን ነገር የሚያደርጉ ደግሞ “የዲያብሎስ ልጆች” አሰኝቶአቸዋል ዮሐ 8፡44
 • እስራኤል በጥቅል የእ/ር የበኩር ልጅ ተብላለች
  • እስራኤል በአብርሃም ተስፋ መሰረት የተወለደች የመጀመሪያ የተስፋ-ልጅ ነበረች – ዘጸ 4፡ 22-23 (ለፈርዖን የበኩር ልጅህን ለበኩር ልጄ)፤ አሞ3፡ 1-2/ ኤር 2፡ 3/ ዘዳ 1፡ 31፤ 8፡ 5
  • በኩር የሆነ ሁሉ የሚቀደሰው በዚህ ምክኒያት ነበር
  • የእስራኤል ጥሪዋንና ተስፋዋን የተላበሰች ብትሆንም እንኳ በአመጿ ታልፋ ተሰጠች ሚል1:6/ ሆሴ 11፡ 1-2
  •  እስራኤል ምንም እንኳ በኩር ብትሆንም ብኩርናዋን አቃለለች፡ ሆሴ 1፡1-11
  • ኢየሱስ የእስራኤልን ብኩርና፣ ጥሪ፣ ተስፋና ተልዕኮ ተላበሶ ተገለጠ ማቴ 2፡ 14-15፤
   • በምድረበዳ እስራኤልን መስሎ ፈተናውን ዓለፈ ‹የእ/ር ልጅ ከሆንህ…› (ዘዳ 8:3፤ ዮሐ 4፡33-34፤ ማቴ 4:4)
   • እስራኤል ሙሴን ለመተባበር በባሕር እንደተጠመቀች ኢየሱስ እስራኤል በሰውነቱ ለመወከል ተጠመቀ።
   • ከውሃው ውስጥ ሲወጣም -አንተ ልጄ ነህ- የሚል ድምጽ ሰማ
   • ዕውነተኛው የወይን ግንድ እኔ ነኝ (ዮሐ 15:1-2) በማለቱም መራራ ፍሬ ያፈራችውን እስራኤልን (ኢሳ 5፡ 1-8) መወከሉን ያመለክታል። ይህም “እውነተኛ” የሚለው ተቀጽላ ሐሳቡን አጉልቶ ያሳያል
 • ተተክቶ በዳዊት ዙፋን ላይ የተቀመጠው የእስራኤል “ንጉሥ” በግል የእ/ር ልጅ ተሰኝቷል
  • 2ሳሙ 7፡ 14፤ 2 ሳሙ 23፡ 1-7፤ መዝ 89፤ 1-52፤ መዝ 132፡ 10-14
  • ሉቃ 1፡ 32፤ ሉቃ 3፡ 22/ ሐዋ 2፡ 30-31፤ ሐዋ 4፡ 25-28፤ ሐዋ 13፡ 32-33/ ዕብ 1፡ 5፤  ዕብ 5፡ 5
  • መልካም እረኛ እኔ ነኝ (ዮሐ 10፤ ሕዝ 34፤)
  • የአሥራ ሁለቱ ነገድ በአንድ እረኛ (ንጉስ) ዙሪያ መሆንና የ12 ሐዋርያት መጠራት ሕዝ 37፡ 18-28

ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ የእ/ር ልጅ ነው ሲል በሦስት መንገድ ይገልጸዋል፡

 1. የዳዊት ልጅ በመሆኑ የእ/ር ልጅ ተብሏል (The Messianic Son)
 2. የመለኮት የባሕርይ ልጅ በመሆኑ የእ/ር ልጅ ተብሏል (The Devine Son)
 3. በሐይል ከሙታን በመነሳቱ የእግዚአብሔር ልጅ ተብሏል (ይህም 1ና 2ን በአንድ ላይ በግለጡ ነው) (The Exalted Son)

ሙሉውን መጣጥፍ ለማግኘት እዚህ ይጫኑ: Jesus the son of God

(For the Advanced readers I here direct you to the more intensive study on Christ’s Sonship)

© 2013 – 2015, Samson Tilahun. All rights reserved.

Like Be the first one who likes this post!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Top