Home / Portfolio / Articles / -2- ወንጌል የብሉይ ኪዳን ተስፋና የመንግሥቱ የድል-ምስራች ዜና ነው

-2- ወንጌል የብሉይ ኪዳን ተስፋና የመንግሥቱ የድል-ምስራች ዜና ነው

Posted on

 (If you would like to read the whole article in English, click here AcrobatPDF The Story of the Gospel)

– ወንጌል የእግዚአብሔር መንግስት የምስራች ዜና ነው –

በአንድ አዲስ ግኝት በስተጀርባ የፈጠራው ባለቤት ወይም አዲስ ነገር ያገኘው ሰው አለ። ያ ሰው አዲሱን ነገር ለማግኘት የተነሳሳውና ያከናወነው ደግሞ አንድ የተከሰተ ችግርን ለመፍታት ነው። ስለዚህም ከአንድ አዲስ ግኝት በስተጀርባ አድራጊው ወይንም ተመራማሪው ብቻ ሳይሆን ለግኝቱ መነሻ ምክንያት የሆነና የግድ መፈታት ያለበት አንድ ችግር አለ ማለት ነው። እናም ግኝቱን በተሻለ መልኩ ለመረዳት ግኝቱ ምን ችግር ለመፍታት እንደተሰራ በሚገባ መረዳት ስለ ግኝቱ ጥሩ እይታ ይሰጣል ማለት ነው። የአዲስ ግኝት ጥበብ ይህ ነው። በተመሳሳይ መልኩ በአንድ ትልቅ አመራር በስተጀርባ ትልቅ መሪ ለመሆን የተወለደ ሰው ዘወትር አናገኝም። ታላላቅ መሪዎችም እንዲፈቱት በተጠሩበት ቀውስ (crisis) ይቀረጻሉ። ስለዚህም በትልቅ አመራር በስተጀርባ ታሪክ አለ ማለት ነው፤ የቀውስ ታሪክ፣ የህመም ታሪክ፣የስቃይ ታሪክ ፣የመስዋዕትነት ታሪክ፣ ወዘተርፈ።

goodnewsበተመሳሳይ መልኩ ስለወንጌል ምንነትና እንዴት እንደሚሰራ ለማወቅ ወንጌል በመጀመሪያ ደረጃ ይፈታ ዘንድ አግዚአብሔር የወሰነውን ችግር ማጤን/ ማወቅ አለብን። በቅርበት የምናጤነውም ችግር ወይም ታሪክ ወንጌል መልካም ዜና (የምስራች ዜና) አንዲሆን ያደረገውን  አውድ (context) ይሰጠናል። ከዚህ ቀጥሎ አንደምንመለከተው ወንጌል የሰውን አመጽ አስወግዶ ቁጣን የሚያበርድ የምስራች ቃል ነው። የምሥራች ያደረገውም ሰው ከአመጽ ወደ እርቅ መምጣቱ ነው። ይህን መልካም ዜና መልካም ዜና ያደረገውን ( የምስራቹን የምስራች ያሰኘዉን) አውድ (context) በማያሻማ መልኩ ካልተረዳን በስተቀር ወንጌል የሚሰጠን ትርጉም በጣም ውሱን ይሆናል።

ለብዙ ዓመታት በከተማችን ቤተክርስቲያንችን በምታዘጋጀው የወንጌል ሥርጭት ላይ ተሳትፌያለሁ። በተጨማሪም ሰዎች ወንጌልን ለማያምኑ ሰዎች ስያካፍሉም ሰምቻለሁ። ለምሳሌ ያህል ለማያምነው ሰው የሚቀርቡ ጥያቄዎች ይህን ይመስላሉ። “በልብህ ሰላም አንዲሰማህ ትፈልጋለህ?” “ደስታን ማግኘት ትፈልጋለህ?” “በሕይወት አላማ አንዲኖርህ ትፈልጋለህ?” “ከዚህ በሽታ መፈወስ ትፈልጋለህ?” “ከተስፋ ቢስነት መዳን ትፈልጋለህ?” ዝርዝሩ ይቀጥላል። ወንጌል በርግጥ እነዚህን ሁሉ ይፈታል። ነገር ግን ወንጌል ሊፈታ የመጣው ዋነኛ ችግር ግን አይደለም። በሌላ አባባል የሰው ልጆች ቀውስ ከነዚህ ሥር የሰደደ ነው። ኢየሱስ በዋነኛ ደረጃ  የመጣው እነዚህን ለመፍታት ቢሆን ኖሮ አላስፈላጊ በሆን ነበር። ለነዚህ ችግሮች በሞላ ጎደል ያለ ደም መስዋአት መፈታት በተቻለ።

ለዚህ ነው በመጀመሪያ ወንጌል ሊፈታ የመጣውን ቀውስ መረዳት ወንጌል ምን እንደሆነ እንድናውቅ ይረዳናል። የሰው ልጆች መፍትሔ የሌለው ቀውስ ከእግዚአብሔር ጋር ያለ ጥበኝነት ነው። ይህም ጠበኘት የመነጨው ከሰው ልጆች በባህሪያቸው ከወረሱት አመጽ (idolotry) ነው። ለዚህ ነው መጽሀፍ ቅዱስ ስለ ሰው ልብ የሚናገረ። ሰው በባሕሪይው ገና ከሕጻንነቱ በልቡ በእግዚአብሔር ላይ እንትፍ የሚል አመጸኛ ነው። ይህ አመጽ በትምህርታችን አንደተመለከትነው ለሉዓላዊው አምላክ ስልጣን መንግስት አለመገዛት ነው። ወንጌል በመጀመሪያ በዚህ አመጽ በሰለጠነበት ዓለም ላይ ኪዳናዊ መንግስቱ ሁሉን ይገዛ ዘንድ መገለጡን (ኢሳ 40: 1-10፤ ኢሳ 52: 7-10) የሚያውጅ የምሥራች ቃል ነው “አምላክሽ ነግሷል!”። የአግዚአብሔር ንግሥና ግን በመጀመሪያ ለሐጥያተኛው የሰው ዘር “አስደንጋጭ ዜና” ነው።  ሰው የእግዚአብሔር ጠላት ነውና። ይህ ንጉሡ በጽድቅ የሚገዛ ንጉሥ ነው። በጽድቅ ይፈርዳል፥…በቅንነት ይበይናል፤ በአፉም በትር ምድርን ይመታል፥ በከንፈሩም እስትንፋስ ክፉዎችን ይገድላል። የወገቡ መታጠቂያ ጽድቅ፥ የጎኑም መቀነት ታማኝነት ይሆናል።”  ሆኖም ግን የዚህ መንግሥት አገላለጥ በሁለት ዘመናት ተከፍሏል።  የንጉሡ የመጀመሪያ መምጣት፤ ይህም በእምነት ጽድቅ የሚገኝበት የምህረት ዙፋን ሲሆን ሁለተኛው ግን ሁሉን የሚጠቀልል የፍርድ ዙፋን ነው። አስከዚያው ድረስ አሁን ያለንበት የዘመን-መጨረሻ በ ፪ ቆሮ ምዕራፍ ፮ ላይ “የመዳን ቀን አሁን ነው ይላል!”። ይህ “አሁን” የሚለው ቃል የሚያመለክተው (በልማድ አንደሚባለው ሳይሆን)  የዚህን በመጀመሪያና በዳግም ምጽአቱ መካከል ያለውን ዘመን ማመልከቱ ነው። ዳግም አስካልተመለሰ ድረስ “በአሁን” ሰዓት ውስጥ አለን። የምህረት ዙፋን የተዘረጋበት ፤ ምህረትን ማግኘት፤ የሐጥያትን ይቅርታ መቀበል የሚቻልበት ዘመን ነው። ስለዚህ ነው ምሕረትን አንድንቀበል “አሁን” የአዲስ ኪዳን ዋስ ሆኖ በግራማው ቀኝ ወደ ተቀመጠው ጌታ ጸጋ ዙፍን ፊት በእምነት የምንቀርበው። ለሁለተኛ ሲመለስ ግን ይህ ዕድል ያበቃል። ስለዚህ በመጀመሪያ ሊጠየቅ የሚገባው ጥያቄ፡ “ፈውስ ትፈልጋለህ? ሰላም ትፈልጋለህ?…” አይደለም። የመጀመሪያው ሊሆን የሚገባው “አሁን ተብሎ ቀን ሳለልህ፤ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ትፈልጋለህ?”። ኢየሱስ የዚህን የተበደለውን አምላክ ቁጣ ማብረድና መዓቱን መመለስ የቻለ ጻድቅ ንጉስ/ አንበሳ/ እና ፍጹም መሥዋዕት /የታረደ በግ/ ነው። ሕይወቱ በአመጽ የጎደፈ የተራ ሰው ሕይወት ሳይሆን በማያልፍም ሕይወት ኃይል – የወልድ ሕይወት – ቅዱስና ያለ ተንኮል፤ ነውርም የሌለበት፤ ከኃጢአተኞችም የተለየ፤ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ፥ እንደዚህ ባለ ሊቀ ካህናት በኢየሱስ በሚሻል ኪዳን ዋስ የተገኘ ሥርየት  በመሆኑ፤ ደሙ የብዙ ሰዎችን በደል ያስተሰርያል። ተመልከቱ በመጽሀፍ ቅዱስ የእንሥሳት ደም መፍሰስ ሥርዓት ሲሰጥ በዘጸ 24 ላይ

“ሙሴም የደሙን እኵሌታ ወስዶ በቆሬ ውስጥ አደረገው፤ የደሙንም እኵሌታ በመሠዊያው ረጨው።  የቃል ኪዳኑንም መጽሐፍ ወስዶ ለሕዝቡ አነበበላቸው፤ እነርሱም። እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን እንታዘዛለንም አሉ።  ሙሴም ደሙን ውስዶ በሕዝቡ ላይ ረጨው። በዚህ ቃል ሁሉ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ያደረገው የቃል ኪዳኑ ደም እነሆ አለ።”

ይህ ማለት በአውዱ መሰረት፤ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ብንተላለፍ በላያችን የተረጨው የኮርማ ደም የኛ ደም ይሁን ማለታቸው ነው። ቃል ኪዳኑን ሲተላለፉ እግዚአብሔር በምድረበዳ የፈጃቸው በዚህ ምክኒያት ነው። አሁን የተረጨው ደም የእንስሣ ነው፤ ብንተላለፍና በአንተ ብናምጽ ፍርድህ ቅን ፍርድ ነው ማለታቸው ነው። መጽሀፍ እንደሚል የሰው ዘር በሙሉ በእግዚአብሔር ላይ ያመጸ በፍርድ ዘንግ ስር የወደቀ ፍጥረት ነው። ለዚህ ነው ወንጌል የሚአስፈልገው። ወንጌል የምስራች የሆነው፤ የኔና የእናንተ ደም በመፍሰስ የእግዚአብሔር ቁጣ መአት መረድ ነበረበት። በፈንታው ግን ወልድ ሐጥያቴን፤ የእናንተን ሐጥያት በሰውነቱ በእንጨት ላይ ተሸከመ። ፍርዳችንን ወሰደልን። በኛ ደም ፈንታ የእርሱ ደም ፈሰሰ። ስለዚህ ለሐጥያት ስርየት የሆነ መስዋእት ተገኘ። አሁን በልጁ ላይ ባለ እምነት፡ በደሙ ላይ ባለ መታመን ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ስለሆነልን ከልጁ የተነሳ አባ አባት ብሎ የሚጮሀውን የልጁን መንፈስ ወደ ልባችን ላከ። ይህ መንፈስ ቅዱስ መንፈስ እንደሆነ ሁሉ፤ ወደ ቅድስና ይመራናል። እለት እለት ክርስቶስን እንድንመስል ይለውጠናል። ይህ ሁሉ በረከት የተገኘው ከወንጌል የተነሳ ነው።

በአሁኑ ሰዓት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሥነ ልቡናዊ አስተያየት በማስ-ሚዲያ (በተለይ በቶክ-ሾው ፕሮግራሞች) ላይ በመቅረብ ጥሩ የሚመስሉ ምክሮችን በመለገስ ሰዎችን መርዳት ሲፈልጉ ሳይ ትልቅ ጥያቄ ይሆንብኛል። እንድትረዱልኝ የምፈልገው ነገር፤ በሳይንስ አምናለሁ። ነገረ-መለኮትና ሳይንስ የማይጣሉ አብረው የሚሰሩ እውነታዎች ናቸው። ለምሳሌ ያህል Nancy R. Pearcey (The Soul of Science) ለሳይንስ መንገድ በመቀየሰ ነፍስ የሰጠው የክርስትና አስተምሕሮት እንደሆነ በጥሩ ማስረጃ አቅርባለች። ምክንያቱም ክርስትና ይህ የሚታየው ተፈጥሯዊ ዓለም በአግዚአብሔር አደተሰራና ሰዎችንም ይሰሩባት ዘንድ አንዳኖራቸው ደግሞም ተፈጥሮ ራሱ የማይታየው አምላክ ክብር አንደሚገልጥ ስለሚያስተምር ነው። ስለዚህ ሰዎች በሕክምና በሥነ-ልቡና እርዳታ ሊያገኙ ይችላሉ። ለዚያ ቦታ አለው፤ አግዚአብሔር በቸርነቱ ይህን አንድያደርጉ የጠራቸውም ሰዎች አሉ። ጥያቄዬ የተመሰረተው ግን አገልጋዮች ግን ለሰው ልጆች መድሃኒት ያልተገኘለት በሽታ መፍትሄ በእጃቸው ክርስቶስ ኢየሱስ አስረክቧቸዋል (ማቴ 20:18-20)። አነዚህ አገልጋዮች የክርስቶስ እየሱስ አንደራሴዎች ናቸው። ሰውን ከአግዚአብሔር ጋር ታረቁ የሚሉ ወኪሎች ናቸው። ጥሩ ጥሩ የስነ ልቡና ምክር ሲሰጡ ሰሚውን ያለክርስቶስ ሕይወትህ ይለወጣል እያሉ ነው። ያለክርስቶስ መፍትሄ አለ እያሉ ነው። ነገር ግን ያው ምክር ግን በሌላ ሰው በኩል ቢመጣ ችግር የለብኝም። የኛ ትልቁ ቀውስ አካላዊ በሽታ አይደለም። ስነልቡናዊ ችግር አይደለም። የትዳር ችግር አይደለም። አነዚህ ሁሉ መሰረታዊና መፍትሄ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ናቸው። ዋናው ጉዳይ ግን በቀኑ መጨረሻ ቤተክርስቲያን እውነተኛ መድኃኒት በእጇ አላት። ወንጌል የሰው እውነተኛ ቀውስ መድኃኒት ነው። ይህም በወንጌል ሰው ከአምላክ ጋር ይታረቃል። መታረቅንም ባገኘንበት በዚህ አዲስና ሕያው መንገድ እውነተኛ የሕይወት ለውጥ ይገኛል!

 

የወንጌል ዕድገት በብሉይ ኪዳን

መጽሐፍ ቅዱስ “ወንጌል” የሚለውን ቃል ወደ 120 ጊዜ ጥቅም ላይ ውሎ እናያለን። በብሉይ ኪዳን ብቻ “ብሦራ(ህ)” ( בְּשֹׂרָה bĕśōrâ) tidings” የሚለውን የእብራይስጥ ቃል 30 ጊዜ ያህል ተጠቅሟል። [ “ ብሥራት” የሚለው የአማርኛ ቃልም የተገኘው ከዚሁ ከእብራይስጥ ቃል ነው]። የብሉይ ኪዳን ይህን ቃል ሲጠቀም ማንኛውንም አይነት ‘ዜና’ ለማመልከት ሲሆን፤ በተቃራኒው አዲስ ኪዳን ግን ቃሉን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ የሚያውጅ መልካም ዜና (የምስራች) ለማመልከት ነው። በብሉይ ኪዳን የሥነመለኮት መዝገበ ቃላት መሰረት:

“ብሦራ” የሚለው ስርወ ቃል በሴማዊ ቋንቋ በስፋት የታወቀ ሲሆን ይሄውም በአካድያን፣ በአረብኛ ፣በኡጋርኛ፣ በኢትዮጵይኛ፣.. ውስጥ ይገኛል። የስርወ ቃሉ ትርጉም በተለይ ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ጋር የተያያዙ ዜናዎችን ማምጣት ማለት ነው። (Theological Wordbook of the Old Testament (R. L. Harris, G. L. Archer, Jr. & B. ፥K. Waltke, Ed.)

በብሉይ ኪዳን ውስጥ ይህ ቃል ቀደም ባሉት ጊዜያት በሥራ ላይ የዋለው በሳሙኤልና በነገሥታት ታሪካዊ መጽሐፍት ውስጥ ከንጉሥ ዳዊት ጋር በተያያዘ መልኩ ነበር። መልእክተኞች ዜና ይዘው ሲመጡና ሲነግሩ እናነባለን። በሁለቱም መጻሕፍት ውስጥ የተጠቀሰው ዜና ከዳዊት ተቀናቃኞች ( ከንጉሥ ሳኦልና ከልጁ ከአቢሰሎም) ሞት ጋር የተያያዘ ነበር።

የመንግሥቱ የድል ምስራች ዜና

“ብሦራ” የሚለው ቃል የጎላ ትርጉም ኖሮት ጥቅም ላይ የዋለው ቀደም ሲል እግዚአብሔር ህዝቡን ከግብጽ ለማዳን ሲል ባህር ከፍሎ የተቀዳጀውን ድል እንደ ምሳሌ (እንደ ሞዴል/ ጥላ/) በመውሰድ ለሁለተኛና ለመጨረሻ ጊዜ በሰው ልጆች ሁሉ ፊት (አሕዛብን ጨምሮ) ደግሞ ስለሚገልጠው  ማዳን፤  ወይንም ወደፊት ስለ ሚቀዳጀው የመጨረሻ ዘመን ድል (Eschatological or End-Time-Salvation) ለማመልከት ነው። የዚህን የቃሉን የጎላ አጠቃቀም በኢሳ. 40፥ 1-9፣ 41፥27፣ 52፥ 7፣ 61፥ 1 ፣ 60 ፥ 6 ፤ ናሆም 1 ፥ 15 ፤ ኢዮኤል 2፥ 32 ፤ መዝ. 40፥ 9  67፥ 12፣ 96፥ 2፣ 68፥ 11  ላይ ማየት ይቻላል።  ኢሳይያስ ምዕራፍ 52 እና 53 ውስጥ ሌሎች ነቢያት የሚጋሩት ትንቢት አለው። ይሄውም እግዚአብሔር በቅርቡ የተፋፋመ አስፈሪ ጦርነት በማድረግ ጠላቶቹን ድል እንደሚነሳ ተናግሯል። ኢሳያይስ የጦር ሜዳ መልክተኞችን/ ወሬ-አቀባዮችን (የዘመኑን የጦር ሜዳ ሪፖርተሮች) “የምሥራች ይዘው የሚመጡ እግሮች” ይላቸዋል። ኢሳያስ ይህንን ዘይቤያዊ ዕይታ በመጠቀም፤ እግዚአብሔርን ድል ሲቀዳጅ የዓይን ምስክር የሆኑት፣ ይህንኑ የድል ዜና ለማብሰር ወደ ከፍ ወዳለ ማማ በሩጫ በመቅረብ ለከተማይቱ ጉበኞች በርቀት በመጮህ “ጦርነቱ አብቅቷል፤ መልካም ዜና፣ ሰላም፣….ድነት፣ ….አምላክሽ ነግሷል” ይላሉ

          “ በተራሮች ላይ የቆሙ፣  የምስራች ይዘው የሚመጡ እግሮች፣

                ሰላም የሚናገሩ፣ 

                መልካምን ዜና የሚያበስሩ፣

          ድነትን የሚያውጁ ፣ ጽዮንንም፣

            ‘አምላክሽ ነግሶአል’ የሚሉ እንዴ ያማሩ ናቸው።”

           “ ስሚ፣ ጠባቂዎችሽ ድምጻቸዉን ከፍ አድርገዋል

       በአንድነት በእልልታ ይዘምራሉ። እግዚአብሔር ወደ ጽዮን ሲመለስ፣

      በዓይኖቻቸው ያያሉ።” (ኢሳ. 52፥7-8)

የጦርነቱን  ውጤት በጉጉት የሚጠባብቁት ጉበኞች (ጠባቂዎች) በተራቸው ዜናውን ወደ ጽዮን ኗሪዎች ያስተላልፋሉ። በመጀመሪያ (በስቃይና በባርነት አገዛዝ ስር ላሉት) የጽዮን ነዋሪዎች፣ ከዚያም እስከምድር ዳርቻ ላሉት ህዝቦች ዜናውን ይነግራሉ። ይህ የዜና አደራረስ በሮሜ 1፥16-17 ላይ የተጠቀሰዉን “ በመጀመሪያ ለአይሁድ ከዚያም ለአሕዛብ” ከሚለው ጋር የሚነጻጸር ነው።

የዚህን አዲስ የምስራች ዜና (የእግዚአብሔር ንግሥና መመለስ) ጉልህ አስፈላጊነት ለማየት እግዚአብሔር እስራኤልን አንዲተዋት ያደረገውን ምክንያት ማጤን አለብን። በሕዝቅኤል 10፥1-19 መሠረት (ምዕራፍ 9 እና 10 ሙሉውን አውድ ይሰጡናል) የእግዚአብሔር ክብር የሰለሞንን ቤተመቅደስ፤ ማለትም ጽዮንን ሲተው እናያለን። ጽዮን ደግሞ የእግዚአብሔር አገዛዝ ክልል ነች (ኤር 17፥ 12)። ሕዝቅኤል በራዕይ አራት ፍጥረታትን አየ። እነዚህም ኋላ በቤተመቅደሱ ላይ የተቀመጡት ኪሩቤሎች እንደሆኑ ተናግሯል።  “ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ክብር ከቤተመቅደሱ ደጃፍ ላይ ተነስቶ ከክሩቤል በላይ ቆመ። ክሩቤልም እኔ እያየሁዋቸው ክንፎቻቸውን  ዘርግተው ከምድር ተነስተው ሄዱ፤ መንኮራኩሮቹም አብረዋቸው ሄዱ፤ በእግዚአብሔርም ቤት በምስራቁ በር መግቢያ ላይ ቆሙ፤ የእስራኤልም አምላክ ክብር በላያቸው ላይ ነበር” ሕዝቅ. 10፥18-19።[እዚህ ላይ እግዚአብሔር ቤተመቅደሱን ትቶ ለመሄድ እንዳመነታ እናያለን፤ ነገር ግን የህዝቡ ኃጢያት እንዲለቅ ገፋው።]

ይህ ከባድ ፍርድ (ማለትም የእግዚአብሔር ክብር መገኘት ከእስራኤላውያን መካከል ለቆ መውጣትና በውጤቱም የከተማይቱ መፈራረስ)[1] በኢየሩሳሌም ላይ የተፈረደው በ586 ዓ. ቅ. ክ. የባቢሎን ጦር ቤተመቅደሱን አፍርሶ ከተማይቱን በአወደመበት፣ ነዋሪዎቹን በገደለበትና ቅሬታዎቹንም ለግዞትና ለባርነት[2] በወሰደበት ጊዜ ተከናውኗል (2 ነገስታት 24-25፣ 2 ዜና 36)። ይህ ሁሉ የሆነው በእስራኤል አጸያፊ የጣኦት አምልኮ ተግባር ነበር (ሕዝቅ.8፥5-9)። እግዚአብሔር ሕዝቡን ከጥፋትና ከውድመት ማዳን ተስኖት አልነበረም። የናቡከደንጾር ጦር ገብቶ  ከተማይቱን ሲያወድም አምላካቸው በቤተመቅደሱ ውስጥ አልነበረም። እግዚአብሔር ለቃልኪዳኑ ታማኝ የልሆነውን ሕዝቡን ለመቅጣት ናቡከደናጾርን እንደፍርድ መሳሪያ እየተጠቀመበት እንደነበር፤ ለይሁዳ መጥፎውን ዜና የተናገረው ነብዩ ኤርምያስ ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር ለቃልኪዳኑ ታማኝ አምላክ ስለሆነ፤ ታማኝነቱም ለቅድስናው ስለሆን ፤ የኪዳን መተላለፍ ፍርድ ጫፍ የሆነውን ሕዝቡን ለምርኮ አሳልፎ ሰጠ (ዘዳ. 28፥15-68)። በሌላ በኩል ደግሞ እግዚአብሔር ከናቡከደናጾር ጋር ያለውን ጉዳይ ከጨረሰ በኋላ እርሱ እራሱን፣ ላሳየው ትዕቢት፣ መልሶ ይቀጣዋል (እዚህ ጋር አንባቢው የእግዚአብሔርን ሉዖላዊነትና ሰዎች በፊቱ ለሥራቸው ተጠያቂነት የማይጋጩ እውነታዎች እንደሆኑ ሊረዳ ተገቢ ነው። God’s sovereignty and human responsibility are compatible) ስለዚህ በኢሳይያስ 52 መሠረት፤ የምሥራቹ ቃል ይዘት“አምላክሽ ነግሷል” የሚለው ቃል  ነው። ይህ ዜናውን መልካም ዜና አድርጎታል። እግዚአብሔር አሁን የመንግስቱ ርስት ወደሆነው ወደ እውነተኛ ውርሱ ተመልሷል። እግዚአብሔር ወደ ጽዮን ሲመለስም ጠባቂዎቿ በዓይኖቻቸው ያያሉ። የእግዚአብሔር አገዛዝ (መንግስት) መመለስ የተከናወነው ጌታ ከከተማው በር ውጭ በተቀዳጀው ድል ነው። ይህንን ድል የተቀዳጀለት ያህዌህ ባሪያዬ ብሎ የጠራው ሰው ነው ( ኢሳ 52፥13-53፥12)። የሕዝቡን በደል በሰውነቱ የተሸከመና ያህዌህ ስለበደላችን ያደቀቀው ሰው ነው። (ይህንን በተመለከተ እዚህ ጋር ቢጫኑ ስለዚህ ባሪያ መስማት ይችላሉ) በዚህም ሥራ ጠላት፣ ኃጢአትና ሞት ድል ተመቱ!የደስታ ዝማሬ በጽዮን ይሰማል!! ከዚህ በኋላ ህዝቡ ከእርሱ አይለይም።  “በድንኳኒቱም የሚያገለግሉ ከዚያ ሊበሉ መብት ያላገኙበት መሰዊያ አለን። ሊቀ ካህናቱ ስለ ኃጢአት ስርየት የሚሆነውን የእንስሳት ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ይገባል፣ የእንስሳቱ ሥጋ ግን ከሰፈር ዉጭ ይቃጠላል። እንዲሁም ኢየሱስ በራሱ ደም አማካይነት ሕዝቡን ሊቀድስ ከከተማው በር ውጭ መከራን ተቀበለ። ስለዚህ እኛም እርሱ የተሸከመውን ውርደት ተሸክመን ከሰፈር ውጭ ወደ እርሱ እንውጣ። ምክንያቱም በዚህ ቋሚ ከተማ የለንም፤ ነገር ግን ወደፊት የምትመጣዋን  ከተማ እንጠብቃለን።” (ዕብ. 13፥0-14)

__________________________

[1]አዲስ ኪዳን መንፈስ ቅዱስን ተስፋ በማለት ደጋግሞ የሚጠራው የሚያስደንቅ አይደለም። የመንፈስ ቅዱስ ተመልሶ መምጣት የእግዚአብሄርን ፍርድ ማብቂያና የመጨረሻ ዘመን ድነት ምልክት ነበር። “ እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል ይህም የድነታችሁን ወንጌል በሰማችሁ ጊዜ ወደ ክርስቶስ ተጨምራችኋል፤ አምናችሁም በእርሱ በመሆን ተስፋ ሆኖ በተሰጠው በመንፈስ ቅዱስ ማህተም ታትማኋል (ኤፌ. 1፥13)። “ ንስሐ ግቡ፣ ኃጢያታችሁም እንዲሰረይላችሁ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፣ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ” (ሐዋ. 2፥38)። ይህን ያለው በእርሱ የሚያምኑ ስልሚቀበሉት መንፈስ ነበር፤ “ምክንያቱም ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ አልተሰጠም ነበር” ( ዮሐ. 2፥39)

[2] የቅሬታዎቹ ለባርነት ተግዞ መወሰድ ለእግዚአብሔር የወደፊት ድነት መሠረት ሆኖ ነቢያትን አገልግሎአቸዋል (ወይም በመሰረትነቱ ተጠቅመውበታል)። ልክ እግዚአብሔር ሕዝቡን ከግብጽ እንደዋጀ ሁሉ አሁንም ከአሶርና ከባቢሎን ይዋጃቸዋል። ይህ በነቢያት በተለያዩ ቦታዎች በትኩረት ተጠቅሷል። የሚመጣው ድነት ከተደረገው ከግብጽ መውጣት (ዘጸአት) ጋር ይመሳሰላል። ሆሴዕ 2፥14-15፣ 11፥1፣ 12፥9፣ 13፥4-5አሞጽ 2፥9-10፣ 3፥1-2፣ 9 ፥7፤ ሚክ. 6፥4፤ ኢሳ. 10 ፥:24-26፣ 11፥15-16፤  ኤር. 2፥6-7 ፣ 7፥22 ፣ 25 ፣ 11 ፥ 4 ፣ 7፣ 23፥7-8 ፣ 16፥14-15 ፣ 31፥32፣ 32፥20-22 ፣ 34፥13-14 ፤ ሕዝቅ. 20፥5-10. ጌታ እየሱስ ታልፎ የተሰጠባት ሌሊት የመውጣት ወይም የዘጸአት ሌሊት እንደሆነች አሳወቀ። ልክ እስራኤላውያን ከመውጣታቸው በፊት በፋሲካ ምሽት በግ በማረድ ደሙን የበራቸውን መቃንና ጉበን ቀብተው የፋሲካ እራት እንደበሉ ሁሉ ኢየሱስም በመስቀል ላይ በመሞት የእግዚአብሔር ፍርድ እንዲያበቃ ያደረገ የፋሲካ በግ ነበር። 

ዘካርያስ ስለዚህ ሲመሰክር እንዲህ ብሏል፤

“…እነሆ ጻድቁና አዳኙ ንጉስሽ

ትሁት ሆኖ፣ በአህያ ላይ ተቀምጦ፣

 በአህያ ግልገል፣ በውርንጭላይቱ ላይ ሆኖ

ወደ አንቺ ይመጣል……እግዚአብሔር በምድር ሁሉ ላይ ይነግሳል፤

በዚያን ቀን እግዚአብሔር አንድ ስሙም አንድ ብቻ ይሆናል።”

(ዘካ. 9፥ 9፣14፥9፤ ከዮሐንስ 12፥15 ጋር ያንጻጽሩ)

ነብዩ ኤርምያስም እንዲህ ብሏል፤

“ እነሆ ለዳዊት ጻድቅ ቅርንጫፍ የማስነሳበት ጊዜ  ይመጣል ፤

       እርሱም ፍትህንና ጽድቅን የሚያደርግ፣

     በጥበብ የሚገዛ ንጉሥ ይሆናል “ ይላል እግዚአብሔር

“ በእርሱም ዘመን ይሁዳ ይድናል፤ 

      እስራኤልም በሰላም ይኖራል ፤

የሚጠራበትም ስም ፣ ‘ እግዚአብሔር ጽድቃችን ‘ የሚል ይሆናል” (ኤር. 23፥5-6)

ስለዚህ፣ ከሁሉ አስቀድሞ የእግዚአብሔር አገዛዝ፣ በጣዖተ-አምልኮው ምክንያት፣ ወደ ተወው ወደ ቃልኪዳን ህዝቡ ሲመለስ (ኢሳ. 52፥7)፣ የሰሩትን ሀጥያት ሊሰርዝላቸው፥ እግዚአብሔር እራሱ የመቤዥት`እርምጃ እንደወሰደ ያመለክታል። እግዚአብሔርም በመጨረሻ የዳዊት ዘር የጽድቅ ቅርንጫፍ በሆነው በናዝሬቱ ኢየሱስ አማካይነት ይህን እንዳደረገ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች በአንድነት ይመሰክራሉ። በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን መሠረት ይህን የመጨረሻ ዘመን ድነት አመጣ።  (ሮሜ. 1፥1-4፤ 2 ጢሞ. 2፥8፣ 2 ጢሞ. 1፥9-10፣ ሮሜ. 15፥8-13፣ሮሜ. 16፥25-26)። 

በሁለተኛ ደረጃ የእግዚአብሔር አገዛዝ (መንግሥት) ወደ ጽዮን መመለስ በዚያኑ ጊዜ ለሕዝቡ የንሥሃ ጥሪ እንዲቀርብ መንሥዔ ሆኖአል። ከግዞቱ ጊዜ ጀምሮ የእግዚአብሔር የጽድቅ አገዛዝ አልተለወጠምና የንስሃው ጥሪ አስፈላጊ ነበር። እስራኤል በአደረገችዉ አምልኮተ ጣኦት እግዚአብሔር ከፈረደባት በኋላ በምህረት መመለሱን በንስሐ መንፈስ መቀበል አለባት። ከዚህ አንጻር ሲታዩ የአዲስ ኪዳን ወንጌላውያን በመንደርደሪያቸው ላይ የጻፉት ትርጉም ያላቸዉና ስሜት የሚሰጡ ይሆናሉ። ወንጌላወያኑ ( ማቴዎስ፣ ማርቆስና ሉቃስ)የወንጌል ዜናን የከፈቱት በዚሁ በእግዚአብሔር መንግስት መመለስ (በንስሐ መንፈስ) ጽንሰ ሃሳብ ነው። የምስራቹም ቃል “ጊዜው ደርሷል፣ የእግዚአብሔር መንግስት ቀርባለች፣ ንስሐ ግቡ፣ በወንጌልም እመኑ” (ማር. 1፥15) የሚል ነበር።

“ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል

 ‘ያለ ዋጋ ተሸጣችሁ ነበር

ያልገንዘብ ትቤዣላችሁ። ’”  ( ኢሳ. 52፥4)

“ እናንተ የኢየሩሳሌም ፍርስራሾች

  በአንድነት በእልልታ ዘምሩ

  ኢየሩሳሌምንም ተቤዥቶአልና” ( ኢሳ. 52፥9)

“ተለዩ፣ ተለዩ፣ ከዚያ ውጡ፣

ርኩስ ነገር አትንኩ ፣

ከዚያ ውጡ ንጹሃንም ሁኑ:፡” ( ኢሳ. 52 ፥11)

 እነሆ ባርያዬ የሚያከናውነው፣ በማስተዋል ነው፣

ገናና ይሆናል ከፍከፍ ይላል፣

እጅግ  ይከብራልም።” ( ኢሳ. 52፥13)

“ነገር ግን እርሱ

  ስልመተላለፋችን ተወጋ፣

  ስለበደላችንም ደቀቀ፣

በእርሱ ላይ የወደቀው ቅጣት ለእኛ ሰላም  አመጣልን፣

  በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን።” ( ኢሳ. 53፥5)

“ እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፣

እያንዳንዳችንም በየመንገዳችን ነጎድን፣

እግዚአብሔርም

   የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ ጫነው።” ( ኢሳ. 53፥5)

ስለዚህ፣ ኢሳያስ 52 እና 53 ሰብሰብ ባለ መልኩ ሲታይ ፣ ቀጥሎ የተመለከቱት አራት ጽንሰ ሃሳቦች የብሉይ ኪዳን የምስራች ዜና አዋጅ ይዘት ሆነው እናገናቸዋልን።

  1. ሕዝቡን በመተው የተከናወነው የእግዚአብሔር ፍርድ አብቅቷል።  (ኢሳ. 52፥3-5)
  2. የእግዚአብሔር አገዛዝ ስለክብሩ ሲል ወደ ህዝቡ ተመልሷል። (ኢሳ. 52፥6-8)
  3. ጣኦት አምላኪዋ እስራኤል ንስሐ እንድትገባ እግዚአብሔር ጥሪ አቅርቦላታል። (52፥11-12)
  4. እግዚአብሔር በባርያው ስቃይ አማካይነት ስለ ህዝቡ የመቤዠትን ሥራ ሠራ። (ኢሳ. 52፥9-10፤ 52፥13-53፥12)[3]

__________________________

[3] ኢሳ. 52፥1 ላይ ከሚሆን በኢሳ. 52፥13 ላይ አዲስ ምእራፍ ቢጀምር  የተሻለ ይሆን ነበር። ምክንያቱም አንባቢዉ በእግዚአብሔር መንግስት መመለስና በአገልጋዩ ስቃይ የተገኘውን መቤዤት በቀላሉ ማገናኘት ስለሚያስችለዉ ነው። የምእራፎቹ አከፋፈል መንፈሳዊ እንዳልሆነና ኢሳይያስ ትንቢቱን ሲጽፍ ምዕራፍ እንዳልነበረዉ ማወቅ አለብን።

© 2013 – 2014, Samson Tilahun. All rights reserved.

Like Be the first one who likes this post!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Top