Home / Portfolio / Articles / -3- ወንጌል በአዲስ ኪዳን:- ወንጌል የብሉይ ተስፋ ፍጻሜ ነው!

-3- ወንጌል በአዲስ ኪዳን:- ወንጌል የብሉይ ተስፋ ፍጻሜ ነው!

Posted on

(If you would like to read the whole article in English, click here AcrobatPDF The Story of the Gospel)

ጌታ እየሱስ “ ጊዜው ደርሷልየእግዚአብሔር መንግስት ቀርባለች፣ ንስሃ ግቡ፣ በወንጌልም እመኑ” በማለት የእግዚአብሔርን ወንጌል አውጇል (ማር. 1፥15)። “ዩዋንጌልዮን” (εὐαγγέλιον, euangelion) የሚለው የግሪክ ቃል ወንጌልን cropped-thomas_christ1.jpgለመጥቀስ ከ 100 ጊዜ በላይ በአዲስ ኪዳን (በብሉይ ነብያት በእብራይስጡ ‘ብሦራ‘ ብለው የተጠቀሙት ነገር ግን በአዲስ ኪዳን ግሪክ ሲዞር ‘ዩዋንጌልዮን’ ያሉት) አገባቡን ሳይለውጥ ጥቅም ላይ ውሏል።   (“ወንጌል” የሚለው የአማርኛችን ቃልም የተገኘው ከዚሁ ከግሪኩ “ዩዋንጌልዮን”ቃል ነው) ይህን ቃል በቋሚነት የተጠቀመበት ከሱሉሱ እግዚአብሔር ጋር በማያያዝ ነበር። ከዚሁ በመነሳት ወንጌል ቀጥሎ በተመለከቱት አቤይት ስያሜዎች በተደጋጋሚ ይጠራል።

 •  የእግዚአብሔር ወንጌል፤ ይህ በቀጥታ እግዚአብሔር አብ የወንጌል ባለቤት እንደሆነ ያመለክታል። ወንጌል፣ በዘላለማዊ እቅዱ ውስጥ ድነትን ያሰበው፤ የእግዚአብሔር የግል ኦላማው ነው፤ (ማር. 1:14፣ ሮሜ. 1:1፣ ሮሜ. 15፥16፣1 ተሰሎ. 2፥2፣ 1 ተሰሎ. 2፥8፣1 ተሰሎ. 2፥9፣1 ጴጥ. 4፥17)።
 • የክርስቶስ ወንጌል፤ በመስቀል ላይ በመሞት በደሙ የድነትን ሥራ ያከናወነውን ክርስቶስን የሚመለከት ወንጌል ማለት ነው። ( ሮሜ. 15፥19፣ 1 ቆሮ. 9፥12፣ 2 ቆር.2፥12፣ 2 ቆር.9፥13፣2 ቆሮ. 10፥ 14፣ ገላ. 1፥7፣ ፊልጵ. 1፥27፣1 ተሰ. 3፥2)
 • መንፈስ ቅዱስ የእውነት መንፈስ በመባል ይታወቃል፤ [ይህም እውነት የወንጌል እውነት ነው)። በዚህ መሠረት የመንፈስ ቅዱስ ተግባር በክርስቶስ የተፈጸመውን ሥራ በወንጌል በአመኑት ሕይወት ዉስጥ እንዲሰርጽና እንዲሠራ ማድረግ ነው። ( ዮሐ. 14፥17፣15፥26፣16፣13፣ ገላ. 3፥14፣ ኤፌ. 1፥13፣ ራዕ 19:10)

ማርቆስ፣ የኢየሱስ ስብከት ይዘት አድርጎ በቅድሚያ ያቀረበው “ ጊዜው ደርሷል” የሚለውን ነው። የዚህም የተወሰነው ጊዜ መድረስ የወንጌሉ አዋጅ ማዕከል (center) ነበር። የተጠበቀውም ስለመጣ ከእንግዲህ ወዲያ ጥበቃው አብቅቷል ማለት ነው። እግዚአብሔር ቃሉን ጠብቋል፤ በልጁ ሕልወት አማካይነት አገዛዙን [ እንደ ቀድሞው] ወደ ህዝቡ መልሷል ( ሉቃ. 17፥20-21)። ለዚህም መልካም ዜና (ማለትም ለወንጌል) ተገቢው ምላሽ ንስሐ መግባትና እምነት ነው። ማርቆስ ግን በዚህ ብቻ አያበቃም፤ ገና የሚነግረን አለው። ከዚያም አልፎ የእግዚአብሔር መንግስት እንዴት በትክክልና ሙሉ በሙሉ ወደ ቀድሞው ቦታው እንደተመለሰ ይተርክልናል። በዚህም መሠረት፣ የእግዚአብሔር አገዛዝ በመስቀሉ ስቃይና በትንሳኤው ድል ወደ ቅድሞ ቦታው ተመልሷል[1]

___________________________

[1] ወንጌል እንደ ሞኝነት የታየው’ የእግዚአብሔር መንግስት መምጣት’ ሳይሆን ወይንም በእምነት የሚቀበል መሆኑ ሳይሆን የአመጣጡና በገሃድም የታየበት ሁኔታ ነው። አይሁድ የተሰቀለ ወይም የሚሰቀል መሲህ አልጠበቀም፤ ከዚያም አልፎ የሙታን ትንሣዔ ለዓለም ፍጻሜ ቀን ማለትም እግዚአብሔር በዓለም ላይ ለሚፈድባት እለት የተወሰነ ተደርጎ ተወስዷል። ነገር ግን ወንጌል ንጉሡ አንደመጣና እንደተሰቀለ ግና ህያው እንደሆነ አውጇል። ክርስቶስ በርሱ ለሚያምኑቱ የመጀመሪያ በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነስቷል። ትንሣኤውም የሆነው የተባለው የዓለም መጨረሻ ሳይደርስ ከወዲሁ በዚህ ዘመን አጋማሽ ላይ ነው። ይህን ምስጢር ጌታ ኢየሱስ እራሱ በምሳሌ ሲያስተምር የመንግስተ ሰማይ ምስጢር መሁኑን ተናግሯል ( ማቴ. 13)። ሐዋርያው ጳውሎስም “ ይህም ጥበብ እግዚአብሔር ከዘመናት በፊት ለክብራችን አስቀድሞ የወሰነው ነው” …( 1 ቆሮ. 2፥7)….” እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ መሰናክል፣ ለአሕዛብ ደግሞ ሞኝነት ነው። እግዚአብሔር ለጠራቸው ግን፣ አይሁድም ሆኑ ግሪኮች፣ ክርስቶስ የግዚአብሄር ኃይል፣የእግዚአብሔርም ጥበብ ነው። ” (1 ቆር. 1፥23-24) ብሏል።

ማርቆስ ምዕ. 1 ቁጥር 1 ላይ “ የወንጌል መጀመሪያ…” የሚለውን እናነባለን። መጥምቁ ዮሐንስና ጌታ ኢየሱስ ስለ እግዚአብሔር ወንጌል እንዳበሰሩ ማርቆስ ጽፏል። ይሁን እንጂ መጥምቁ ዮሐንስ ወንጌልን ያወጀው አመልካች ጣቱን ከእርሱ በኋላ ወደሚመጣው በማመልከት ነበር። ጎንበስ ብሎ የጫማውን ማሰሪያ መፍታት የማይገባውና ከእርሱ የሚበልጥ እንደሚመጣ በጣቱን አመለከተ፤ በዚህም፣ ከራሱ ይልቅ ትኩረት ወደሚመጣው እንዲሆን ያላሰለሰ ጥረት አደረገ። ኢየሱስ ግን የእግዚአብሔርን ወንጌል ያወጀው (ያበሰረው) ትኩረት ሁሉ ወደ ራሱ እንዲሆን በትክክል በማመልከትና የእግዚአብሔር አገዛዝም ማዕከል እርሱ እንደሆነ በማሳወቅ ነበር። የእግዚአብሔርን አገዛዝ አምጪ እንደመሆኑ፣ የኢየሱስ ድርጊትና ሥልጣን ማንኛውም ሰው ሲያስብ ከነበረው ከማንኛውም ነገር ያለፈና ምጡቅ የሆነ ነበር። ዓሳ አጥማጆችን “ ተከተሉኝ…” ብሎ ነበር የጠራቸው። አጋንንቶች “ ልታጠፋን መጣህን?” እያሉ ጮሁ፤ “…ሕዝቡም በመገረም ‘ ይህ ነገር ምንድነው? ሥልጣን ያለው አዲስ ትምህርት መሆኑ ነው! ርኩሳን መናፍስት እንኳን ይታዘዙታል” (ማር. 1፥ 25-27) በማለት ተጠያየቁ። ህሙማንን መፈወስ፣ አጋንንት ማስወጣት፣ ሙታንን ማስነሳት፣ ለምጻሞችን ማንጻት፣ ኃጢአትን ይቅር ማለት…የመሳሰሉት የኢየሱስ ስራዎች ለእግዚአብሔር አገዛዝ ወደዚህች ምድር መምጣት ያለአንዳች ጥርጥር ማስረጃና ምልክቶች እንደሆኑ ማርቆስ ለይቶ አውቆአል። ኢሳይያስ ምዕራፍ 61. ቁጥር 1 ላይ “የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፣ ለድሆች የምስራች እንድሰብክ እግዚአብሔር ቀብቶኛል” ይላል። በሉቃስ ምዕራፍ 4 ቁጥር 21 መሰረት ኢየሱስ የተቀባ የእግዚአብሔር አገልጋይ እንደሆነ እራሱን አሳወቀ፤ እርሱም “ ይህ በጆሮአችሁ የሰማችሁት የመጻፍ ቃል ዛሬ ተፈጸመ” በማለት በትኩረት ለተመለከቱት ተናገረ። “ አምላክሽ ነግሷል” በማለት ኢሳይያስ የተነበየው (ኢሳ 52:7-10)፤ ‘የናዝሬቱ ኢየሱስ’ በተበላው የገሊላ ነብይ ተፈጽሟል። ይህም የመንግስቱ የምስራች ዜና አዋጅ ነበር።

የዚህ አጭር ጥናት ዓላማ ሕግና ነቢያት የመሰከሩለት በኢየሱስ ክርስቶስ ሕልወትና ሥራ የተፈጸመ መሆኑን ለማመልከት ነው። ያም የወንጌል መጀመሪያ ነው። በተሻለ መልኩ ወንጌልን ለመረዳት ደግሞ ወንጌል ወደ ብርሃን ያመጣውን ምንነት በትክክል መርምረን መረዳት አለብን። ስለዚህም ይህን ለማድረግ ወንጌል ምንጊዜም የማይነጣጠሉና ሁሌ አብረው ያሉ ሶስት ክፍሎች (አካላት) እንዳሉት ማወቅ አለብን።

 1. የወንጌል አውድ (the context of the gospel)፤ ይህም በብሉይ ኪዳን ጊዜ የተጠበቀውን የተስፋውን ቃል ማወቅ ነው፤ ያለዚህ አውድ እውቀት ወንጌል ትርጉም አልባ ይሆናል። ዜናውን በእርግጥም መልካም ዜና የሚያሰኘው ይሄው አውድ ነው።
 2. ወንጌል ራሱ ሲታወጅ (the proclamation of the gospel itself)፤ ይህም የመሲሁ ኢየሱስን ሕልወትና ሥራ ማወቅን ያመለክታል።
 3. የወንጌል ፍሬ ( the fruit of the gospel)፤ ይህ ደግሞ ወንጌል መልእክቱን በተቀበሉት ሕይወት ውስጥ የሚያስገኘውን ፍሬ ያመለክታል።

ይህን ለማስረዳት አውሮፕላንና ክንፎቹን እንደ ምሳሌ መጠቀም እንችላልን። የግራ ክንፉን እንደ ወንጌል አውድ፣ የቀኝ ክንፉ እንደ ወንጌል ፍሬ፣ ራሱ አይሮፕላኑን እንደ ወንጌል መውሰድ እንችላለን። ወይም ኢየሱስ እራሱ የተጠቀመበትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሃሳብ ብንወስድ፣ ወንጌል እንደ ወይን ተክል ነው። የወይኑ ስር እንደ ወንጌል አውድ ፣ የወይኑ ግንድ እንደ ወንጌል፣ ቅርንጫፎቹ ደግሞ ወንጌል በአማኞች ሕይወት ፍሬ ሲያፈራ አድርገን ማየት እንችላለን። ስለዚህ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል በተዘጋጀ መሬት ላይ አንደተዘራ ዘር፤ ብናስብ ገበሬው እግዚአብሔር አባት ነው፣ የወይኑ ስር የብሉይ ኪዳን አውድ ነው፣ ግንዱ ኢየሱስን በወንጌል ወስጥ ያመለክታል፣ ፍሬው ደግሞ በቅርንቻፎቹ (ወንጌልን አምነው በተቀበሉት) ሕይወት ውስጥ የሚታየው ውጤት ነው፤ ይህም አንዱ መቶ፣ አንዱ ስልሳ፣ አንዱ ሠላሳ እጥፍ የሚያፈሩበት!

ይህ በሚቀጥሉት ክፍሎች የበለጠ ይብራራል፤ ለአሁን ግን በመጀመሪዊቷ ቤተ/ክርስቲያን ሐዋርያት በዕለት ስብከቶቻቸው ወንጌልን እንዴት እንደተረዱትና እንዴትስ እንዳስተለለፉ እንቃኝ። ለዚህም የሚረዱን ነጥቦች ከ 1 ቆሮ. 15፥1-10፤ ሮሜ. 1፥1-7፣16፥25-26፤2 ጢሞ. 2፥8 ተወስደዋል።

——–ዋና ሃሳብ (Outline)—

በደበዳቤዎችና በሐዋርያት ሥራ የወንጌል ባህርያት

 1. ወንጌልን ከማጥበብ መቆጠብን መማር
 2. ወንጌል ማዕከላዊ ነው
 3. ወንጌል ክርስቶስን ማዕከል ያደረገ ነው
 4. ወንጌል የእግዚአብሔር ክብር ነው
 5. ወንጌል የተስፋ-ቃሉ ፍጻሜ ነው 
 6. ወንጌል የምስጢሩ መገለጥ ነው
 7. ወንጌል ታሪካዊ ክዋኔ ነው
 8. ወንጌል ሐዋርያዊ ምስክር ነው

የወንጌል አውድ

 1. ፍጥረት፤የእግዚአብሔር አብ ሥራ የጀመረበት
 2. የሰው ውድቀት/አመጽ፤ የሰው ልጅ በፍርድ ሥር
 3. የመቤዠት ተስፋና ቃልኪዳናት፤ ሕግና ነቢያት

ወንጌል

 1. የወንጌል መጀመሪያ፤ [የተስፋው] ፍጻሜ… የመንግስቱ መቅረብ
 2. ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ የመሲሁ ኢየሱስ ማንነት
 3. ኢየሱስ የጌታ ባሪያ  ነው፤ የመሲሁ ኢየሱስ የመቤዠት ሥራ
 4. ኢየሱስ ክርስቶስና ጌታ ነው፤ ትንሣዔና እርገት

የወንጌል ፍሬ

 1. የመንፈስ ቅዱስ መምጣት፤
 2. የክርስቶስ ሥራ መጠናቀቅ/ መረጋገጥ
 3. የመጨረሻው [ዘመን] ጅማሬ፤ የመጨረሻው ዘመን ድነት አሁን ቀርቧል/ተጀምሯል
 4. የሁሉም ፍጻሜ፤ የመጨረሻው ዘመን ድነት ሙሉ በሙሉ ገና የሚመጣ ነው
 5. አዲስ ፍጥረት፤ እነሆ ሁሉ ነገር አዲስ ሆኗል

© 2013 – 2014, Samson Tilahun. All rights reserved.

Like Be the first one who likes this post!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Top