Home / Portfolio / Articles / -4- ወንጌል በመጀመሪያይቱ ቤተክርስቲያን ሕይወት፡ ወንጌልን ከማጥበብ መቆጠብ

-4- ወንጌል በመጀመሪያይቱ ቤተክርስቲያን ሕይወት፡ ወንጌልን ከማጥበብ መቆጠብ

Posted on

 (If you would like to read the whole article in English, click here 

)

1 ቆሮንቶስ 15፥ 1-11

አሁንም፣ ወንድሞች ሆይ፣ የሰበክሁላችሁንና የተቀበላችሁትን ደግሞም ጸንታችሁ የቆማችሁበትን ወንጌል ላሳስባችሁ እወዳለሁ፤ የሰበክሁላችሁን ቃል አጥብቃችሁ ብትይዙ፣ በዚህ ወንጌል ትድናላችሁ፤ አለዚያ ያመናችሁት በከንቱ ነው። እኔ የተቀበልሁትንና ከሁሉ በላይ የሆነውንም ለእናንተ አስተላልፌአለሁ፤ ቅዱሳን መጻፍት እንደሚሉት ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፤ ተቀበረ፣ በቅዱሳን መጽሐፍት እንደ ተጻፈውም በሦስተኛው ቀን ተነሳ፣ ከዚያም ለኬፋ ታየ፣ ቀጥሎም ለአስራ ሁለቱ ታየ፣ ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ በላይ ለሚሆኑ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነዚህም አብዛኞቹ በሕይወት አሉ፣ አንዳንዶቹ ግን አንቀላፍተዋል። ከዚያም ለያዕቆብ ታየ፣ በኋላም ለሐዋርያት በሙሉ ታየ፣ ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምቆጠር ለእኔ ደግሞ ታየ። እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ፣ ሐዋርያ ተብዬ እንኳን ልጠራ የማይገባኝ ነኝ ፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን አሳድጃለሁ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ አሁን የሆንሁትን ሆኛለሁ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋ ከንቱ አልሆነም ፤ እንዲያዉም ከሁሉ በላይ በትጋት ሰርቻለሁ፤ ዳሩ ግን እኔ ሳልሆን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው። ከንግዲህ እኔም ሆንሁ እነርሱ የምንሰብከው ይህንኑ ነው፤ እናንተም ያመናችሁት ይህንኑ ነው።

ሮሜ 1፥1-4

ጳውሎስ፤ የክርስቶስ ኢየሱስ ባርያ፤ ሐዋርያ ሊሆን የተጠራና ለእግዚአብሔር ወንጌል የተለየ፤ ስለዚህ ወንጌል በነቢያቱ በኩል በቅዱሳት መጻፍት አስቀድሞ ተስፋ ተሰጠ። ወንጌሉም ስለልጁ፣ በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለሆነ፣ በቅድስና መንፈስ ደግሞ ከሙታን በመነሳቱ የእግዚአብሔር ልጅ ስለ መሆኑ በኃይል ስለ ተገለጠው ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

2ጢሞቴዎስ 2፥8-9

ከሙታን የተነሳውን፣ ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስብ፣ የእኔም ወንጌል ይሄው ነው፤ ስለዚህም እንደ ወንጀለኛ እስከ መታሰር ድረስ መከራን እየተቀበልሁ ነው፤ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም።

ሮሜ. 16፥25-27

በዘላለማዊ አምላክ ትእዛዝ ህዝቦች ሁሉ አምነው እንዲታዘዙ፣ በነቢያት መጽሐፍት አሁን በተገለጠው፣ ላለፉት ረጅም ዘመናት ተሰውሮ በነበረው ምስጢር መገለጥ፣ በአስተማርሁት ወንጌልና በኢየሱስ ክርስቶስ መሰበክ ሊያጸናችሁ ለሚችለው እርሱ ብቻ ጥበበኛ ለሆነ አምላክ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለዘላለም ክብር ይሁን! አሜን።

(1 ) ወንጌልን ከማጥበብ መቆጠብን መማር

“አሁንም፣ ወንድሞች ሆይ፣ የሰበክሁላችሁንና የተቀበላችሁትን ደግሞም ጸንታችሁ የቆማችሁበትን ወንጌል…”

ከሁሉ አስቀድሞ ከላይ የተመለከተውና ከ 1 ቆሮንቶስ 15፥ 1-11 የተወሰደው ጥቅስ ወንጌል ምን ማለት እንደሆን ጠቅለል አድርጎ የሚያቀርብ ‘ማጠቃለያ’ ሃሳብ እንደሆነ ማወቅ አለብን። እዚህ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ የቆሮንቶስ ሰዎችን ከዚህ በፊት ያስተማራቸውን ወንጌል እያስታወሳቸው እንጂ ወንጌል ምን ማለት እንደሆን እያስተማራቸው አይደለም። “ ላሳስባችሁ ..” የሚለውም አነጋገር የሚጠቁመን ጳውሎስ ቀጥሎ የሚናገረው ይህንኑ እንደሆን ነው። ይህም የቆሮንቶስ ሰዎች ቀደም ብሎ በጥልቀት የተማሩት የወንጌል ትምህርት እንዳለ ያስገነዝበናል። ይህንንም ሁኔታ በግንዛቤ በማስገባት ጳውሎስ በማጠቃለያ ለማለፍ መረጠ።   ስለዚህ ጳውሎስ እንደሚያውቁ በመገመት ለቆሮንቶስ ሰዎች በጥቅሉ በመናገር ያስታወሳቸውን የወንጌል እውነት ‘ላሳስባችሁ እወዳለሁ…’ ያለውን እኛም እንደ እነርሱ እንድንረዳ ጥቅሉን አርፍ ተነገር  መተርተር ይኖርብናል። እንደማንኛውም ማጠቃለያ ሃሳብ፣ በ 1 ቆሮንቶስ 15፥ 1-11 የተጠቀሰው እያንዳንዱ አረፍተ ነገር ጳውሎስና የቆሮንቶስ ሰዎች በጋራ የሚያውቋቸውን ጥቅል ሃሳቦች፣ ትርጉሞችና አውዶችን ያሳያል።

ለምሳሌ፣ “9/11 አሜሪካን ለዘላለም ለውጧታል! ” ብዬ ብጽፍ አንባቢው ስለምን እየተናገርሁ እንደሆን በትክክል እንደሚገባው አውቃለሁ። በሌላ አባባል አንባቢው ቀደም ሲል ስለ 9/11 ዝርዝር እውቀት እንዳለው አስቤአለሁ ማለት ነው። ስለዚህ ይህ ማጠቃለያ እሳቤ አንባቢዬና እኔ በጋራ የምናውቀውን ክዋኔ አስታውሰዋለሁ። በሰጠሁት ምሳሌ ውስጥ ይህ ይህ አጭር ማጠቃለያ የኒውዮርክ ከተማን በሽብር የሞላቻትን ያቺን አስፈሪ የማክሰኞ ማለዳ፣ የሁለቱ መንትያ ህንጻዎች መውደቅ፣ በሽብርተኝነት (terrorism) ላይ የታወጀው ጦርነት፣ የፍይናንስ ገበያ ውድቀት ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተ አለመረጋጋት፣ በጣም የጠበቀ የደህንነት (security) ቁጥጥር እርምጃ………ዝርዝሩ ይቀጥላል። ያቺ አንድ ማጠቃለያ ሃሳብ እነዚህንና ሌሎችንም መሰል ዝርዝር ሁንታዎችን ወደ አንባቢው አእምሮ ታመጣለች ማለት ነው።   “ 9/11 አሜሪካን ለዘላለም ለውጧታል!” ስልም አንባቢዬ ስለ እነዚህ ከላይ ስለ ተዘረዘሩት እንዲያስብ ፈልጌ ነው፤ ለማለት የፈለኩትም ይህንኑ ነው። ስለ ማጠቃለያ ሃሳቡ አሉታዊ ይዘት በጥቅሉ ከመጠቆም ባሻገር 9/11 ምን እንደሚወክል አልገለጽኩም። ይሁንና ከጥቂት አስርተ አመታት በኋላ እነዚህ ማጠቃለያ ሃሳቦች የሚያስተላልፉት መልዕክት ምናልባት አደናጋሪ ሊሆን ይችላል ፤ ምናልባትም ከበርካታ አመታት በኋላ፣ በተለይም ቁጥሮችን በተመለከተ (9/11)፣ ይህ የማጠቃለያ ቃል “መስከረም-አሥራ አንድ” መሆኑን ላላወቀ አንባቢ ሌላ ትርጉም ሊሰጠውም ይችላል።

ጳውሎስ እነዚያን የማጠቃለያ ቃሎች በጻፈበት ጊዜ ይዘቱና የመልዕክቱ ክብደት አንባቢዎቹ በሚገባ ተረድተውታል። ጳውሎስ መልዕክቱን በግልጽ ማስተላለፍ እንዲችል የወንጌልን ጥልቅ ሚስጢር ጠበብ ማድረጉ ወይም ይዘቱን መቀነሱ አልነበረም። ጨርሶ! ይልቁንስ ተቃራኒው እውነት ነው። ከላይ ስለ 9/11 በጥቂት ቃላት የቀረበው ማጠቃለያ የ9/11 ይዘትና ክበደት ዝቅ እንዳላደረገ ሁሉ፣  ጳውሎስም “ቅዱሳን መጻፍት እንደሚሉት ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፤  ተቀበረ፣ በቅዱሳን መጽሐፍት እንደ ተጻፈውም በሦስተኛው ቀን ተነሳ…“  በሚሉ ማጠቃለያ ቃላት የተቀበለውን ወንጌልን ሲገልጽ ጠበብ አድርጎ ማቅረቡ አይደለም።    እነዚህ ቀላል ቃላቶች የታቀዱት ጳውሎስ ስለ ወንጌል በስፋትና በጥልቀት ያስተማረውን የወንጌልን ሙሉ እውነት ወደ ቆሮንቶስ አማኞች አእምሮ ለማምጣት ነበር። ጳውሎስ ለአንድ ዓመት ተኩል በቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን ቆይቶ እንደ ነበር በዚህ አጋጣሚ ላስታውሳችሁ እውዳለሁ። በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 18 ቁጥር 5-11 እንደ ተጠቀሰው ጌታ ሌሊት በራዕይ ተገናኝቶት አበረታች መመሪያ ከሰጠው በኋላ ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለአንድ ዓመት ከሥድስት ወር ያህል ቆይቶ አስተምሯል፤ ይህም በኤፌሶን ካሳለፈው 3 ዓመት ቀጥሎ ረዥሙ ጊዜ መሆኑ ነው።

ይህንን ብሂል ስምታችሁ ታውቃላችሁ? “ወንጌል “ABC” ነው!’ ይህም ከሆነ ወንጌል ጥልቅ ሚስጢሩን ያጣል። ለሕይወት የሚያስፈልገንን ሁሉ የምናገኝበት ይሆን ዘንድ የሚጨመርበት ያስፈልጋዋል ማለት ነው። ይህም ወንጌልን ጠባብ ያደርገዋል። እንዲህ ካለ ስለ ወንጌል ከሚሰነዘር አስተያየት መቆጠብ አለብን።   በአንድ ጸሀፊ አባባል ወንጌል “ A-Z ” ነው። “ABC” ከ D-Z ያሉትን አይጨምርም። “A-Z” ግን ሁሉንም ሆሄያት (ፈደሎች) ያካትታል ሆኖም ግን ጠቅለል ባለመልኩ እንጂ እያንዳንዱን ፊደል በመዘርዘር አይደለም።:  ስለዚህ ጳውሎስ የወንጌልን ማጠቃለያ ሃሳብ ያቀረበው በዚሁ በ“A-Z” መልኩ ነው። ጳውሎስ ወደ ቆሮንጦስ ቤተክርስቲያን መጀመሪያ በመጣ ጊዜ እንዲህ ብሏቸዋል ፤

“…..ወንድሞች ሆይ፤ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ፤ የእግዚአብሔርን ምስጢር በረቀቀ የንግግር ችሎታ ወይም በላቀ ጥበብ ልገልጽላችሁ አልመጣሁም። በመካከላችሁ ሳለሁ ኢየሱስ ክርስቶስን ያውም የተሰቀለውን ፣ እርሱን ብቻ እንጂ ሌላ እንዳላውቅ ወስኜ ነበርና። …… ቃሌም ስብከቴም የመንፈስን ኃይል በመግለጥ እንጂ፣ በሚያባብል የጥበብ ቃል አልነበረም፤ ይሄውም እምነታችሁ በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ ላይ እንዳይመሰረት ነው። በበሰሉ ሰዎች መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን ፤ ይሁን እንጂ የዚችን ዓለም ጥበብ ወይም የሚጠፉትን የዚችን ዓለም ገዦች ጥበብ አይደለም። ነገር ግን ተሰውሮ የነበርውን የእግዚአብሔርን ምስጢር ጥበብ ነው ፤ ይህም ጥበብ እግዚአብሔር ከዘመናት በፊት ለክብራችን አስቀድሞ የወሰነው ነው። ” ( 1 ቆሮ. 2፥1-7)

በመካከላችሁ ሳለሁ እየሱስ ክርስቶስን ያውም የተሰቀለውን ፣ እርሱን ብቻ እንጂ ሌላ እንዳላውቅ ወስኘ ነበርና። ” የሚለው የጳውሎስ አባባል አሁንም ማጠቃለያ ነው። ይህም ማጠቃለያ ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት እስከ የመቤዠት ሞቱ (መሰቀሉ) ድረስ የሚሸፍን የማቴዎስን ወይም የማርቆስን ወይም የሉቃስን ወይም የዮሐንስን ሙሉ ወንጌል መስበኩን የሚወክል ነው። ጳውሎስ እዚህ ላይ የተናገረው በደብዳቤዎቹ ውስጥ ከተናገረው ጋር ሁሉ የሚስማማ ወይም አብሮ የሚሄድ ነው። ጳውሎስ በመጀመሪያ ወደ ቆሮንጦስ በመጣ ጊዜ አንዳች ሳያስቀር ወንጌልን በ“ A-Z ” ገጽታው አስተምሯቸዋል።   ነገር ግን በበሰሉት ዘንድ ወንጌል የእግዚአብሔር ዘላለማዊ አላማ መሆኑን በማመላከት በጥልቀትና በሙላት ትምሕርቱን አቅርቧል። (ለተጨማሪ ማብራሪያ “ወንጌል የምስጢሩ መገልጥ ነው”  የሚለውን ክፍል ይመልከቱ )።

_________________ “ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ያድን ዘንድ የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአል….” 1 ቆሮ. 1፥ 18-31. አንድ በአንክሮ መታሰብና መስተዋል ያለበት ነገር የወንጌል ሞኝነት እንዲያው በእምነት ተቀባይነት ማግኘቱ እንዳልሆነ ነው። አይሁዶችም ስለ እምነት መታዘዝ ራሱን የቻለ ልዩ ክፍል አላቸው፤ የእያሪኮ ቅጥር ግንብ የፈረሰው በባዶ እጅ ነበር፣ እስራኤል ቀይ ባህርን የተሻገረው ያለምንም እርዳታ ነበር ….ወዘተ. በጥቅሉ አይሁዶች ወንጌል በእምነት ስለመሆኑ ቅሬታ የላቸውም። ወንጌልን አሳፋሪ እንዲሆን ያደረገው የመስቀሉ ቃል ነው። “መስቀል” የሚለው ቃል መጠቀሱም አይደለም፣ ይልቁንም ችግሩ ያለው ቃሉ በሚወክለው ላይ ነው። ቅዱሱን መሲህ ውርደት ከሆነው የመስቀል ሞት ጋር የተያያዘ አድርጎ ማመን እጅግ በጣም ቅር የሚያሰኝ ነው። እኛ አሁን የምንኖረው “መስቀል” የሚለው ቃል ሃይማኖታዊ ትርጉም አግኝቶ በመልካም ገጽታው በተለመደበት ዘመን ስለሆነ በተጨማሪም የምንኖርበት አውድ (Context) በዚህ ደረጃ ስላመቻቸን በቀድሞው ዘመን ቃሉ ይወክል የነበረው እፍረትና ቅሌት ተነስቶልናል ወይም አይሰማንም። ነገር ግን “ከወነጀለኛ፣ ከነፍሰ ገዳይ ..ወዘተ” ጋር እስከተያያዘ ድረስ ቃሉ ቅሬታንና ዉርደትን የሚወክል እንደሆነ ማወቅ አለብን። ቅሬታውም ይሄው ነው እንጂ ወንጌል የእምነት ሥራ መሆኑ አይደለም።

 

ዘወትር ወንጌል ከወንጌልነቱ ቀንሶና ጠቦ የሚታየው ቀጥሎ በተመለከቱት ሁለት መነገዶች ነው። በቅድሚያ፣ ለብዙዎቻችን፣ ወንጌል ወደ እግዚአብሔር መንግስት መሻገሪያ ነው፤ ስለሆነም ከወንጌል ስርጭት (evangelism) ጋር እኩል አድርገን እናየዋለን።   ከዚህም የተነሳ ወንጌልን የምናስበው በወንጌል ስብከት (evangelism) አውድ ውስጥ ነው።   ለምሳሌ ፣ ነጻ የፊልም  ትኬት ቢሰጠኝ ትኬቱ ዋጋ የሚኖረው ወደ ትያትር ቤት እስከሄድኩ ድረስ ብቻ ነው። ከገባሁም በኋላ ለመክፈሌ ማስረጃ እንዲሆነኝ በኪሴ አስቀምጬ በፊልሙ መደሰቴን እቀጥላለሁ። ትኬቱ ወሳኝ ነው። ወንጌልም እጅግ በጣም ጠቃሚያችን ነው ፤ ነገር ግን እንደ ትኬቱ ሁሉ  ወንጌል አስፈላጊነቱ  ወሳኝና ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ነው። ሕይወት የሚለውጥ ሂደት  የሚመጣው በመንፈሳዊ ስርዓት (discipline)፥ በደቀመዝሙርነት፣ በጾም፣ በማስተማር፣ በቡድን ጥናት(small groups)፣ በኃላፊነት፣ በእምነት ምስክርነት፣በእጅ መጫን ፣ አስራት በመስጠት… ይመስለናል፤ ባብዛኞቹ በእነዚህ ነገሮች አምናለሁ።   ነገር ግን እነዚህ ሁሉ፤  ወንጌልን በግልጽና በማያሻማ ሁኔታ ከመረዳት የተነሳ፤ ከውስጥ የሚመነጩ/ የሚፈሱ ካልሆነ ወደ አትንካ አትቅመስ የሥጋ ጥረት መንገድ ላይ እየትጓዝን ነው። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት “ሐይል” አይደሉም። ወንጌል ብቻ ነው የእግዚአብሔር ሐይል የሚል ሥያሜ የተሰጠው። የመለወጥ ሂደት፤ መንፈሳዊ ብሥለትና እድገት የሚጀምረውም ሆነ እንደሞተር የሚያንቀሳቅሰው ወንጌልን መሰረቱ ያደረገ እንደሆን ብቻ ነው። “የልጁን መልክ እንዲመስሉ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን። ይህ የሚሆነው መንፈስ ከሆነ ጌታ ነው።…የክርስቶስ ወንጌል ብርሀን… በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን እንዲሰጥ በልባችን ውስጥ የበራ። በጨለማ ብርሃን ይብራ ያለ እግዚአብሔር ነውና።”

በጌታ ኢየሱስ ቃል መሠረት፤ “ ከሁሉ አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥና ጽድቁንም እሹ፣  እነዚህ ሁሉ ይጨመሩላችኋል። ”  ወንጌል የእግዚአብሔር መንግስት አዋጅ በመሆን ይታወቃል። በየዕለቱ ያለማሰለስ በክርስቶስ ወንጌል (የኢየሱስ የመሲሁ ነጉሥ የምስራች ዜና) ማሰብና እራሳችንን በዚያ ውስጥ ማገኘት መቻል አለብን፤ ምክንያቱም ወንጌል የእግዚአብሔር የድነት ኃይል ነውና። የወንጌልን ክብር መረዳት እንድንችል የጌታ መንፈስ  ልባችንን ያቀጣጥለው፣ ለዚህም መረዳት ውስጣችንን ያብራው።  

“ወንጌላችን የተከደን ቢሆን እንኳን፣ የተከደነው ለሚጠፉት ነው። የእግዚአብሔር አምሳል የሆነውን የክርስቶስ፣  የክብሩን ወንጌል ብርሃን እንዳያዩ ፣ የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን ሰዎች ልቡና አሳውሮታል። እኛ የምንሰብከው ክርስቶስ እየሱስ ጌታ መሆኑን እንጂ ራሳችንን አይደለምና፣ እኛም ራሳችን  ስለ ኢየሱስ ስንል የእናንተ አገልጋዮች ሆነናል። በክርስቶስ ፊት እግዚአብሔር የክብሩን እውቀት ብርሃን ይሰጠን ዘንድ፣ ‘ በጨለማ ብርሃን ይብራ’  ያለው እግዚአብሔር ብርሃኑን በልባችን አብርቶታልና። ”  2 ቆሮ. 4፥3-6

እንግዲህ ይህን ስታነቡ፣  የክርስቶስን ምስጢር እንዴት እንደማስተውል ለመረዳት ትችላላችሁ። ይህም ምስጢር  አሕዛብ በወንጌል አማካይነት ከእስራኤል ጋር አብረው ወራሾች ፣ አብረው የአንዱ አካል ብልቶች እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነው ተስፋ አብረው ተካፋይ መሆናቸው ነው። ኤፌ. 3፥4 ፣ 6

“ ይህም የሆነው በሰማይ ተዘጋጅቶላችሁ ከተቀመጠላችሁ ተስፋ የተነሳ ነው፣ ስለዚህ ተስፋ በወንጌል የእውነት ቃል አስቀድማችሁ ሰማችሁ ፤ ይህም ወደ እናንተ ደርሷል።  …እግዚአብሔር የፈቃዱን እውቀት በመንፈሳዊ ጥበብና መረዳት ሁሉ ይሞላችሁ ዘንድ መጸለይና መለመን አላቋረጥንም ፤ የምንጸልየውም ለጌታ እንደሚገባ እንድትኖሩና በሁሉም ደስ እንድታሰኙት ነው” (ቆላ. 1 ፥ 5 ፣6 ፣ 9፣ 10)

ሁለተኛው ወንጌል ከወንጌልነቱ እንዲጠብ የሚያደርግብን ወንጌልን ለመረዳት በምንመርጠው መንገድ ነው። ዘወትር ወንጌልን የምንረዳው በጥቅል መልኩ ነው፤ ይሄውም “ ክርስቶስ ሞተ ፣ ተቀበረ ፣ ከዚያም ተነሳ እናም በስሙ የሚያምኑ ዘላለማዊ ሕይወትን ይቀበላሉ” የሚል ነው። ይህ መግለጫ በርግጥ እውነት ነው። ነገር ግን ወንጌልን ከመግለጥ ወደ ማጠቃለል ያመዝናል።

ስለዚህ፣ በወንጌል ድነው ከሞት ወደ ሕይወት እንደተሻገሩ ሰዎች፣ ሁሌ የወንጌል እውነት ውስጥ ሰርስሮ የገባ መረዳት እንዲኖረን ያስፈልገናል። የምንላቸውና የምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ በትክክል ከወንጌል አውድ (Context ) ተፈልቅቀው ይወጡ ዘንድ የወንጌልን ምስጢር ልባችን ውስጥ እንቅበረው። ይህም ቀጥሎ ጳውሎስ ወደሚያወሳው  ነጥብ ይወስደናል።

(2) ወንጌል ማዕከላዊ ነው

“አሁንም፣ ወንድሞች ሆይ፣ የሰበክሁላችሁንና የተቀበላችሁትን ደግሞም ጸንታችሁ የቆማችሁበትን ወንጌል ላሳስባችሁ እወዳለሁ፤ 2የሰበክሁላችሁን ቃል አጥብቃችሁ ብትይዙ፣  በዚህ ወንጌል ትድናላችሁ፤ አለዚያ ያመናችሁት በከንቱ ነው። 3እኔ የተቀበልሁትንና ከሁሉ በላይ የሆነዉንም ለእናንተ አስተላልፌአለሁ፤…”

(ሀ) ወንጌልን እንደ ንጽረት ዓለም መጠበቅ………እንደ አንድ ታላቅና ሁሉን አቀፍ እውነታ!

የተቀበላችሁትን ደግሞም ጸንታችሁ የቆማችሁበትን ወንጌል ላሳስባችሁ እወዳለሁ፤ የሰበክሁላችሁን ቃል አጥብቃችሁ ብትይዙ ፣  በዚህ ወንጌል ትድናላችሁ፤

ጳውሎስ ያስተማራቸው ወንጌል የሕይወታቸው መሠረት እንደሆነ ለቆሮንጦስ ሰዎች ያስታውሳቸዋል። ወንጌል ስፋቱና ይዘቱ ሁሉን አቀፍ እንደዚሁም በእንደምታው (implication) ሁሉን የሚዳሥስ ነው። ቀደም ሲል ሲያምኑ የተቀበሉት ወንጌል ዛሬ የቆሙበት ያው የተቀበሉት የድሮው ወንጌል ነው። ይሄው የተቀበሉት ወንጌል ደግሞ እለት በእለት እስከ ዘመኑ መጨረሻ ድረስ በቀጣይነት የሚለውጣቸውና የሚያሳድጋቸው ነው። በእርግጥ የዚህ ዓይነት ለውጥና እድገት ከወንጌል የሚገኘው አጥብቀው ሲይዙት ብቻ ነው። ጳውሎስ የመሠረታቸው ቤተክርስያናት ሌሎች ነገሮችን እንደ ወንጌል ማዕከላዊነት ማስቀመጥ ሲጀምሩ ከቦታቸው መንሸራተት ታይቶባቸዋል።
ጳውሎስ የወንጌልን ማዕከላዊነት በማይነኩ ጉዳዮች (ማለትም ቀናትን ማክበርና ድግሥ የመሳሰሉት) ላይ የቤተክርስቲያን አባላት እንዲቻቻሉ ያበረታታቸዋል። ሮሜ ላይ እንዲህ ሲል ምክር ሰጥቷል ፤

“ አንድ ሰው አንዱን ቀን ከሌላው የተሻለ ቅዱስ አድርጎ ይቆጥራል ፣ ሌላው ደግሞ ቀኖች ሁሉ እኩል እንደሆኑ ያስባል ። እያንዳንዱ የራሱን ውሳኔ ልብ ብሎ ይወስን። አንድን ቀን ከሌላው የተለየ አድርጎ የሚያስብ ሰው ፣ እንዲህ የሚያደርገው ለጌታ ብሎ ነው፣ ….” ( ሮሜ. 14፥5-6)

ይሁን እንጂ የወንጌል ማዕከላዊነት ለድርድር ሲቀርብና አማኞት የጎላ ዋነኛነት/አስፈላጊነት ለሌላቸው ነገሮች ከፍተኛ ትኩረት ሲሰጡ ጳውሎስ በሰላ ትችት ከመገሰጽ አልተመለሰም። የቆላስይስ ሰዎችን በዚህ መልኩ ቀርቧቸዋል፤

“ እንግዲህ በምትበሉትም ሆነ በምትጠጡት ወይም በዓልን፤ ወር መባቻንና ሰንበትን በማክበር ነገር ማንም አይፍረድባችሁ፤ እነዚህ ሊመጡ ላሉ ነገሮች ጥላ ናቸውና፤ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው። ” (ቆላ. 2፥16-17)

ወይም ቤተክርስያናት የአማኝ ሕይወት ለመለወጥና ለማሳደግ የተለያዩ አትቅመስ አትንካና መንፈሳዊ መሰል ቴክኒክን ሲጠቀሙ ሲያይ ጳውሎስ እነርሱንም የሚስጻቸው አለው ፤

“ አጉል ትህትናና የመላእክትን አምልኮ የሚወድ ማንም ሰው እንዳያደናቅፋችሁ ተጠንቀቁ ። እንደዚህ ያለ ሰው ስላየሁ ራእይ ከመጠን በላይ እራሱን እየካበ በስጋዊ አእምሮው ከንቱ ሃሳብ ተሞልቶ ይታበያል ፤ ይህ ሰው ፣ አካል ሁሉ በጅማትና በማሰሪያ እየተጋጠመ ምግብንም እየተቀበለ እግዚአብሔር በሚሰጠው ከሚያድግበት ራስ ከሆነው ግንኙነት የለውም። ” (ቆላ. 2፥18-19)

አማኞች ከመንፈሳዊ ድነትና እድገት ጋር ባልታከከ መልኩ በራሳቸው ምርጫ መገረዝ ቢፈልጉ (ከባህልና ከተላዩ ምክኒያቶች የተነሳ) አይቃወማቸውም፣ እርሱ ራሱ አድርጓልና።

“ጳውሎስም ይህ ሰው [ጢሞቴዎስ ] ከእርሱ ጋር እንዲሄድ ፈለገ፤ ስለዚህ በዚያ አካባቢ በነበሩ አይሁድ ምክንያት ይዞ ገረዘው፤ እነዚህ አይሁድ በሙሉ የጢሞቴዎስ  አባት የግሪክ ሰው እንደ ሆነ ያውቁ ነበርና ። “ ( ሐዋ. 16፥ 3)

ነገር ግን የወንጌል ብቃት ጥያቄ ውስጥ ሲገባና ለድርድር ሲቀርብ ጳውሎስ ከመጋፈጥ ወደኋላ አይልም።

“የምለውን አስተውሉ፤ ትገረዙ ዘንድ ብትፈልጉ፣ ክርስቶስ ፈጽሞ ለእናንተ እንደማይበጃችሁ እኔ ጳውሎስ እነግራችሁዋለሁ ። ” ( ገላ. 5 ፥ 2)

ማጠቃለያ

“እኛም እያንዳንዱን ሰው በክርስቶስ ፍጹም አድርገን ማቅረብ እንችል ዘንድ ፣ ሰውን ሁሉ በጥበብ ሁሉ እየመከርንና እያስተማርን እርሱን እንሰብካለን ፣ እኔም በብርታት በውስጤ በሚሰራው በእርሱ ኃይል ሁሉ እየታገልሁ ለዚህ ዓላማ እጥራለሁ ። ” (ቆላ. 1 ፣ 28-29)

  • ገና ከጅምሩ ላይ ላማያምኑት የሚሰበከው ወንጌል ነው ፣
  • ያንኑ ወንጌል ያመኑት ይማሩታል
  • ይሄው ወንጌል በዘመን መጨረሻ የእግዚአብሔርን መንግስት በሙላት እንደሚያመጣ ተስፋ ይደረግበታል

መርከብ ወዲያና ወዲህ እየተንሳፈፈና እየዋዠቀ ስፍራውን እንዳይለቅ መልሕቅ በአስተማማኝ ሁኔታ እንድሚይዘው ሁሉ ወንጌልም እንደ መልሕቅ ማንኛውንም  የምናውቀውንና የምንሰራውን ነገር አማክሎ መያዝ አለበት። በወንጌል እውነት ላይ ያልታሰረ አንዳች ነገር ቢኖረን ከወንጌል መንገድ ወጥተናል ወይም ስተናል ማለት ነው። ብዙዎች ክርስቶስን ቢቀበሉም ገና ፍሬ ስላላሳዩ “ ከአመንን በኋላ ሌላ ምን ነገር ማድረግ ይኖርብናል”  በሚል አነጋገር ዙሪያ ውይይት መሰማት ተጀምሯል። ለዚህ የተሰጠው መፍትሄ በገላትያ ቤተክርስቲያን ከተከሰተው ሁኔታ ጋር የሚመሳሰልና አፍራሽ የሆነ ነው። የዚህ ዓይነት ውይይት ማስወገድ አለብን፤ በክርስቶስ የተገኘ ድነት በቂ ነውና።   እኛን ለመለወጥና ለማሳደግ ወንጌል በቂ ነው ። የእግዚአብሔር ቃል ኃይል ቢያጣ ምናልባት ወንጌሉን ከቃሉ ለይተናል ማለት ነው።

ለሐዋርያት የእግዚአብሔር ቃል ማለት ወንጌል ማለት ነው፣ ( የእግዚአብሔር ቃል=ወንጌል)።

“ ….እርስ በርሳችሁም አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ። ዳግመኛ የተወለዳችሁት  ከሚጠፋ ዘር ሳይሆን ሕያው በሆነና ጸንቶ በሚኖር፣ በእግዚአብሔር ቃል አማካይነት ከማይጠፋ ዘር ነው። ….የተሰበከላችሁም የምስራች ቃል ይህ ነው። ” (1 ጴጥ. 1 ፥22-25)

ለሐዋርያት፣ ማስተማርና መስበክ የእግዚአብሔር ቃል እንዴት ወደ ወንጌል እንደሚያመለክት ማሳየት ማለት ነው።

“ በየእለቱም ፣ በቤተ መቅደስም ሆነ በየቤቱ ፣ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ከማስተማርና ከመስበክ ወደኋላ አላሉም። ” (ሐዋ. 5 ፥ 2)

ስለዚህ፣ ወንጌል የመጀመሪያ መግቢያችን ብቻ ሳይሆን፣ ከገባን በኋላ የምንቆምበትና ቀጣይ ድነትም የምናገኝበት ነው። ለማያምኑት የምናዘው ወይም የምናቀርበው እርሱኑ ነው። በአመኑት ልብ ላይ የምንቀርጸው እርሱኑ ነው፤ በመጨረሻው ዘመን እያንዳንዱን የበሰለ ሰው ማቅረብ የምንችለው በእርሱ ነው።   የወንጌል እውነት ሁሉን አቀፍ ነው ፣ ስለዚህ ወንጌል  ማእከላዊም ነው።

© 2013 – 2015, Samson Tilahun. All rights reserved.

Like 1 People Liked this
avatar

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Top