Home / Portfolio / Articles / -5- ወንጌል በመጀመሪያይቱ ቤተክርስቲያን ሕይወት፡ የወንጌልን ንጽሕናና ቀዳሚነት አጥብቆ መያዝ

-5- ወንጌል በመጀመሪያይቱ ቤተክርስቲያን ሕይወት፡ የወንጌልን ንጽሕናና ቀዳሚነት አጥብቆ መያዝ

Posted on

(If you would like to read the whole article in English, click here AcrobatPDF The Story of the Gospel)

(ለ) የወንጌልን ንጽሕና አጥብቆ መያዝ

 የሰበክሁላችሁን ቃል አጥብቃችሁ ብትይዙ፣ በዚህ ወንጌል ትድናላችሁ፤ አለዚያ ያመናችሁት በከንቱ ነው።  ( 1 ቆሮ.15፥ 2)

የወንጌልን ማዕከላዊነት የምንጠብቅበት ሁለተኛው መንገድ ወንጌልን አጥብቆ በመያዝ ነው። ይህ “አጥብቆ መያዝ” ጳውሎስ  ለቆሮንቶስ ሰዎች አንዳስጠነቀቃቸው የወንጌልን የመጀመሪያ ይዘት/መልዕክት (originality) መጠበቅ ማለት ነው። ይህም የተቀበሉትን የወንጌል ይዘትና አጽንዖት አስከ መጨረሻው መጠበቅና ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ ነው። የቆሮንቶስ ሰዎችን የሚያስተነቅቃቸውም ይህንኑ ነው፤ እርሱ የሰበከላቸውን የወንጌል እውነት ልክ እንደተሰበከላቸው አጥብቀው እንዲይዙ ት ነው። ለምን? ምክንያቶቹ ቀጥሎ በተመለከቱት ጥቅሶች ተሰጥተዋል።  “እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን….”እርሱ ጳውሎስ እራሱ የወንጌልን እውነት የተቀበለው ቃል ነው። ጳውሎስ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በሥጋው ወራት ሲያስተምር ከተከተሉት ሐዋርያት አንዱ አልነበረም። የእግዚአብሔር መንግሥት በእግዚአብሔር ልጅ መገለጡና በልጁ መስዋዕትነት ወደዚህ ኪዳናዊ መንግሥት ለመግባት የሚያስችል ቤዛነት መገኘቱ ከዚህም የተነሳ በአሕዛብ መካከል በስሙ የሀጥያት ሥርየትና ንስሃ መሰበኩ አንደዚሁም ሁሉን ጠቅልሎ ሊፈርድ መገለጡ ይህ የሰማው የወንጌል ትረካ ነበር። ቅደም ተከተሉም “ለኬፋም ታየ…ቀጥሎ ለአሥራ ሁለቱ ታየ…. ” ጳውሎስ የተቀበለውን አጥብቆ በመያዝ አስተላልፏል። አንድ ሰው ወንጌልን እስከመጨረሻው ቢጠብቀው እስከመጨረሻው ይድናልና። ግን እንዴት ወንጌልን መጠበቅ ይቻላል? መልሱ የወንጌልን እውነትና ይዘት በመረዳት/በማስተዋል እንደዚያው እንዳለ ለሌሎችም በማስተላለፍ ነው፤

መንግሥትን ቃል ሰምቶ በማያስተውል ሁሉ፥ ክፉው ይመጣል፥ በልቡ የተዘራውንም ይነጥቃል፤ በመንገድ ዳር የተዘራው ይህ ነው።

አለያማ [የቆሮንቶስ ሰዎች] የወንጌልን እውነት ካልተረዱ እንዴት አድርገው ወንጌልን አጥብቀው ሊይዙት ኖሯል?

1 ጢሞ. 3፥9 “ የእምነትን ትልቅ ምስጢር በንጹህ ኅሊና መጠበቅ አለባቸው።“

2 ጢሞ. 1 ፥ 8 “ እንግዲህ [ጢሞቴዎስ]  ስለ ጌታችን ለመመስከር ወይም የእርሱ እስረኛ በሆንሁት በእኔ አትፈር፣  ነገር ግን በእግዚአብሔር ኃይል ስለ ወንጌል ከእኔ ጋር መከራን ተቀበል ፣ እኛ ስላደረግነው አንዳች ነገር ሳይሆን ከእቅዱና ከጸጋው የተነሳ ያዳነን ወደ ቅዱስ ሕይወትም የጠራን እርሱ ነው። …ከእኔ የሰማኸውን በከርስቶስ ኢየሱስ ባለ እምነትና ፍቅር፣ የጤናማ ትምህርት ምሳሌ አድርገህ ያዝ። የተሰጠህን መልካሙን አደራ፣ በእኛ ውስጥ በሚኖረው በመንፈ ቅዱስ ጠብቅ። “

2 ጢሞ. 2፥2 ፣ 8-9፣ “ በብዙ ምስክሮች ፊት ከእኔ የሰማኸውን ፣ ሌሎች ለማስተማር ብቃት ላላቸው ለታመኑ ሰዎች አደራ ስጥ። …ከሙታን የተነሳውን ፣ ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስብ ፣ የእኔም ወንጌል ይኸው ነው ፤ ስለዚህም እንደ ወንጀለኛ እስከመታሰር ድረስ መከራን እየተቀበልሁ ነው ፤ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም ። 

2ጢሞ. 4፥ 1-5 “  በእግዚአብሔር ፊት እንዲሁም በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ ባለው በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት፣ መገለጡንና መንግስቱን በማሰብ ይህን አደራ እልሃለሁ፤ ቃሉን ስበክ፣ ጊዜው ቢመችም ባይመችም ዝግጁ ሁን፣በታላቅ ትዕግስትና በማስተማር አቅና ፣ገሥጽ ፣ አበረታታም። ምክንያቱም ሰዎች ትክክለኛ የሆነውን ትምህርት የማይቀበሉበት ጊዜ ይመጣል፤ ከዚህ ይልቅ ለገዛ ምኞታቸው የሚስማማውን፣ የሚያሳክክ ጆሮአቸው ሊሰማ የሚፈልገውን እንዲነግሯቸው በዙሪያቸው ብዙ አስተማሪዎችን ይሰበስባሉ።እውነትን ከመስማት ጆሮአቸውን ይመልሳሉ፣ ወደ ተረትም ዘወር ይላሉ። አንተ ግን በሁኔታዎች ሁሉ የረጋህ ሁን፤ መከራን ታገስ፤ የወንጌል ሰባኪን ተግባር አከናውን፤ አገልግሎትህንም ፈጽም።“

የወንጌል ይዘት ሐዋርያት ተሰብስበው “ወንጌል” የሚባል የቤተክርስቲያን መተዳደሪያ ደንብ እንዳዘጋጁ የሚቆጠር አይደለም። ይልቁንስ ተቃራኒው እውነት ነው። ይህ ወንጌል የክርስቶስ ወንጌል ሲሆን እርሱም ሐዋርያትን በህዝቦች መካከል እንዲስብኩት አዟቸዋል (ማቴ. 10፥1-37)።  አንድ ወንጌል ብቻ አለ፤ ሌላ ትርጉም ወይም መግለጫ የለውም። ወንጌል ከኢየሱስ ወደ ሐዋርያት አለፈ ፣ ከሐዋርያት ደግሞ ያንኑ ሌሎችን ማስተማር ለሚችሉና ታማኝ ለሆኑ ሰዎች በኃላፊነት ተሰጠ። የሚሰበከው ቃል ወይ ወንጌል ነው ወይ ደግሞ ወንጌል አይደለም!  (ገላ. 1 ፥ 7 ፣ 1 ቆሮ. 3፥11)። ጳውሎስ ጴጥሮስን ተቃወመው፤ (ከግዝረት አቀንቃኞች) ግዝረትን እንደ ዋንኛ ነገር አንግበው የተነሱ ሐሰተኛ ወንድሞችን ተጋፈጣቸው፤ ለአፍታ እንኳን ለማንም አልተሸነፈም። ጳውሎስ እዚህ ሁሉ ተቃውሞና ጥል ውስጥ የገባው የወንጌል እውነት ለእኛ ይጠበቅልን ዘንድ ነው።  ማዕከላዊ ያልሆነ ወንጌል፣ (ቢያንስ ለጳውሎስ) ከቶም ወንጌል አይደለም ለዚህ ነው ለቆሮንቶስ ሰዎች ወንጌልን አጥብቀው ባይዙ የሚላቸው፤ “አለዚያ ያመናችሁት በከንቱ ነው። “

“ አሁን ግን ነውርና ነቀፋ የሌለባችሁ ቅዱሳን አድርጎ በእርሱ ፊት ሊያቀርባችሁ፤ በክርስቶስ ሥጋ በሞቱ በኩል አስታረቃችሁ፤  ይህም የሚሆነው በእምነታችሁ ተመስርታችሁና ተደላድላችሁ በመቆም ከሰማችሁት የወንጌል ተስፋ ሳትናወጡ ጸንታችሁ ብትኖሩ ነው። እናንተ የሰማችሁትና ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ የተሰበከውም ወንጌል ይኸው ነው ፤ እኔም ጳውሎስ ለዚህ ወንጌል አገልጋይ ሆንሁ።”

“ ነገር ግን እባብ ሔዋንን በተንኮል እንዳሳታት ምናልባት የእናንተም ልቡና ተበላሽቶ ለክርስቶስ ካላችሁ ቅንነትና ንጽሕና እንዳትወሰዱ እሠጋለሁ። ምክንያቱም አንድ ሰው ወደ እናንተ መጥቶ እኛ ከሰበክንላችሁ ኢየሱስ ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክላችሁ፤ ወይም ከተቀበላችሁት መንፈስ የተለየ መንፈስ ብትቀበሉ ወይም ከተቀበላችሁት ወንጌል የተለየ ወንጌል ብትቀበሉ፣ ነገሩን በዝምታ ታልፋላችሁ ማለት ነው (2 ቆሮ. 11 ፥3-4) ።

የወንጌልን ንጽህና ለመጠበቅ የዚህ ዓይነት ከፍተኛ ኃላፊነት አለብን፤ ወንጌል ከሌላ ዓይነት ሀይማኖታው ተግዳሮቶችና በራስ የመጽደቅ ከንቱ ጥረት መጠበቅ አለበት። በተለይም የእግዚአብሔርን ቃል ለማካፈል በሰው ፊት የምንቆም ሰዎች ሞትና ሕይወት በረከትና መርገም ከፊታችን አለ። የተለየ ወንጌል የምንሰብክ ከሆንን፣ ሌላው ቀርቶ በስብከታችን ውስጥ ከጥንቃቄ ጉድለት ወይም ከጥቅም የተነሳ በወንጌል ላይ ቢቀነስ ወይም ቢጨመር  ሐዋሪያው “ርጉም ይሁን!” ይላል ( 1ገላ 1፥ 8-9፣ ያዕቆብ 3 ፥ 1 )። ለዚህም ነው ብዙዎቻችን አስተማሪዎች እንዳንሆን የምንመከረው!

(ሐ)  የወንጌልን ቀዳሚነት መጠበቅ

 እኔ የተቀበልሁትንና ከሁሉ በላይ/በፊት የሆነውን ለእናንተ አስተላልፌአለሁ፤”

የወንጌልን ማዕከላዊነት የምንጠብቅበት ሦስተኛው መንገድ ወንጌልን ተቀዳሚ በማድረግ ነው። ለምሳሌ ያህል አንድ ባል ሚስቱን ለምን አንዳገባት ቢጠየቅ የሚሰጠው መልስ ወይ ሚስቱን ያስደስታታል አልያም ያሳዝናታል። “አንድ ቀን ምግቧን ቀምሼ ተማረክሁ” ብሎ ቢመልስ; ይህ ያሳዝናታል ምክንያቱም ይህ ተቀዳሚ አይደለምና። ግን ይህ ባል የሚስቱን ማዘን አይቶ አንዲህ ሊል ይችላል “ርግጥ ነው ስለምወዳት ነው!” ብሎ ለማሳመን ይፈራገጣል። ያጠፋው ጥፋት ግን ዋነኛውን ነገር ተቀዳሚ ባለማድረጉ ነው። ስለምወዳት አንደሆን በመጀመሪያ ተናግሮ ከዚያ ደግሞ ስለ ምግቧ ጣዕም ቢናገር ቅደም ተከተሉን ስላስያዘ ሞገስ በሆነለት ነበር።

ሁላችንም በወንጌል እናምናለን፣ ነገር ግን አጥብቀን መያዝ ያለብን በወንጌል ማመን ማለት ቀንና ሌሊት ወንጌልን  ማንሰላሰል (meditate ማድረግ ) እና ወንጌልን ተቀዳሚ ማድረግ ነው።  እስራኤላውያን ከግብጽ የወጡበትን የእግዚአብሔርን የድነት ሥራ  ማንሰላሰልና ያንኑ ለልጆቻቸውና ለልጅ ልጆቻቸው መንገር ካለባቸው እኛ ምን ያህል የበለጠ ስለ መስቀል ማንሰላሰል ይገባን ይሆን? ወንጌልን ለመረዳት ምን ያህል ሀሳባችንን እንደሰጠን እና በልባችንም ወንጌል ምን ያህል ቦታ እንዳለው መገንዘብ ጠቃሚ ነው። የወንጌልን ማዕከላዊነት ለማስተማር በአዲስ ኪዳን ምን ያህል ቦታ እንደተሰጠው ጊዜ ወስደን ብናይና ይህንኑ ከአሁኑ ሁኔታችን ጋር ብናገናዝብ ልዩነቱ ወደ ንስሐ ያመጠናል ። በመስቀል ውርደት ይህን የክብር ወንጌል ወደ ብርሃን ያወጣው የእግዚአብሔር ልጅ ዙፋን ፊት እንድንደፋ ያደርገናል። 

 


 

[1] በራዕይ መጽሐፍ ውስጥ ሰባቱ አብያተክርስቲያናት ስራቸው የተለካው ስለ እግዚአብሔር ልጅ በመመስከር ረገድ ምን ያህል ውጤታማ እንደሆኑ በመመርመር ነበር። በዮሐንስ መጽሐፍ ውስጥ ‘ምስክርነት ‘ የሚለው ቃል ወንጌል የሚለውን ቃል ይወክላል፤ ዮሐንስ ስለ ምስክርነት ያብራራው ወንጌል ከማድረስ (share ከማድረግ ) ጋር አያይዞ ነው። ለምሳሌ በራዕይ 12፥11 ላይ ቅዱሳን በምስክርነታቸው ቃል ሰይጣንን ድል እንደነሱት እናነባለን። ይህ ግን  ዘውትር እንደሚደረገው) እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ እያደረገ ስላለው መመስከር ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ቅዱሳን የእግዚአብሔር በግ ስለ ሰራው ሥራ የሚሰጡት ምስክርነት ነው። እውነቱን ለመናገር እግዚአብሔር ቢላችንን ቢከፍል ባይከፍል ፣ ከህመማችን ቢፈውሰን ባይፈውሰን ሰይጣንን አያስጨንቀውም። ሰይጣን የሚጨነቀው ወንጌልን መረዳትና የተረዳነውን መመስከር ስንጀምር ነው። ሰይጣን የሚሸነፈው ወንጌል ሲታወጅና ሲመሰክር ነው።

ለጳውሎስ ወንጌል ተቀዳሚ ነው፤ በመሆኑም ከወንጌል አስቀድሞ የክርስቲያን  ስነምግባር፣ የቤተክርስቲያን ችግር፣ ወይም ከጌታ የተሰጠ መመሪያም ሲሰጥ አይደመጥም። ወንጌል ሳይቀድም ትዕዛዝ አትቅመስ አትንካ ነው:; ምክንያቱም ወንጌል የሰውን ልብ ሳይቀይር አድርግ ብሎ አያዝምና። ወንጌል ትዕዛዝን ሲከተል: ሰሚውን ወደ ከንቱ ጥረት ይጋብዘዋል።   ጳውሎስ ግን ከሁሉ አስቀድሞ አድማጩን በማያሻማ ሁኔታ በወንጌል እውነት አንዲማረኩ በማድረግ። የእስራኤል አምላክ፣ (አሁን በተለየ መልኩ  የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ሆኖ የታወቀው) በልጁ አማካይነት ያከናወነውን የፈቃዱን ምስጢር ለአድማጮቹ ያውጅና ይነግራቸው ነበር። 

እንዲሁም ይህ ምስጢር ባለፉት ዘመናት ተሰውሮ የነበረ፣ አሁን ግን ልጁን ወደ ዓለም በመላክ የተገለጠ እንደሆነ ያስተምራቸዋል። እግዚአብሔር ለሕዝቡ ኃጢአት ይቅርታ ሲል ልጁን ለመስቀል ሞት አሳልፎ ሰጠው ፣ በሶስተኛው ቀን አስነሳው፣ ከዚያም የዓለም ንጉሥና ጌታ እንዲሆን ከፍ አደረገው። ከዚያና ከዚያ በህዋላ ነበር ጳውሎስ ፣  እንደዚህ በጥልቀት ባስተማረው ወንጌል ላይ ተመስርቶ ከዚህ ከወንጌል እውነታ የተነሳ ተዛምዶን (applications) ፣ እንደምታዎችን (implications)፣  መመሪያዎችንና ምክሮችን ማውጣት የሚጀምረው ። አነዚህ ትዕዛዞች; ምክሮች ግን ከቀደሙ ሰሚዎችን ወደ ክርስቶስ ጸጋ አይጋብዙትም። ለዚህ ነው ወንጌል ተቀዳሚ መሆን ያለበት! ይህ የሞትና የሕይወት ምክንያት ነው። “ጠጣ!” ትዕዛዝ ነው! ውሃ ሳያቀርቡ ጠጣ ማለት ሰሚውን ወደ ውሃ ፍልጋ የገፈትረዋል። ነገር ግን ወደ ውሃው ቧንቧ አመልክቶ “ጠጣ!” ወደ ምንጩ ያመራዋል! ወንጌል ኢየሱስን ፊት ለፊት ያቀርባል! ያለወንጌል እየሱስ አይገኝም። በወንጌል በምንም ዋጋ ሊገኝ የማይቻለውን የእግዚአብሔርን ልጅ በነጻ ያቀርብልናል በእርሱም ዘንድ ጽድቅና የዘላለም ሕይወት ተስፋ ይገኛል።

እኛም ለአባቶች የተሰጠውን ተስፋ የምስራቹን ለእናንተ እንሰብካለን፤  ይህን ተስፋ እግዚአብሔር በሁለተኛው መዝሙር ደግሞ። አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወለድሁህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ኢየሱስን አስነሥቶ ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሞአልና….እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፥ በእርሱ በኩል የኃጢአት ስርየት እንዲነገርላችሁ፥ በሙሴም ሕግ ትጸድቁበት ዘንድ ከማይቻላችሁ ሁሉ ያመነ ሁሉ በእርሱ እንዲጸድቅ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን” ሐዋ 3:32–39.

ሁላችንም የአብያተ ክርስቲያናት ችግሮችና መንስኤዎቻቸው ሲመረመሩ አጋጥሞናል። ለችግሮቹም “ የሕያው እግዚአብሔር ቤተክርስቲያን በይበልጥ ይህ ወይም ያ ያስፈልጋታል” የሚል መፍትሄም ተሰንዝሮ አይተናል፤ አንዳንድ ጊዜ ብዙ ተአምራት፣  ብዙ የክትትል ጥናት ቡድኖች፣ እጅ የመጫን አገልግሎት፣ ረጅም የአምልኮና የጸሎት ጊዜ; የበለጠ ኃላፊነት፣ የበለጠ መንፈሳዊ ስርዓት፣ የበለጠ ደቀመዝሙርነት፣ ወዘተ፤ እንደ መፍትሄ ቀርቦ አስተውለናል። ነገር ግን የወንጌል ማዕከላዊነትና ዋነኛነት ብቸኛ መድኅናችን (መፍትሄያችን) እንደሆነ ለማመንና በዚያም ለመጽናት በጣም ተገፋፍቻለሁ። ሁሌ መፍትሔ መመንጨት ያለበት ከወንጌል ማዕከላዊነት ነውና!  ለምሳሌ ጳውሎስ ለኤፈሶን ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ ከምዕራፍ 1-3 የወጌልን እውነት የገለጸ ሲሆን ከምዕራፍ 4-6 በመጀመሪያዎቹ ሶስት ምዕራፎች ከአስተማረው ወንጌል ማለቂያ የሌለው ተዛምዶና እንደምታ (application and implication) ማውጣት ይጀምራል። ይህም “ ስለዚህ” በሚለው አያያዥ ቃል  ተረጋግጧል (ኤፌ 4 ፥1)። “ ወንጌል ማለት ይህ ነው”…” ስለዚህ”   …” ይህን አድርጉ…”

ኤፌ. 4፥1  እንግዲህ በጌታ እስረኛ የሆንሁ እኔ ፣ለተቀበላችሁት ጥሪ (፪ ተሰ 2፥14) የሚገባ ኑሮ ትኖሩ ዘንድ (ፊልጵ. 1፥27) እለምናችኋለሁ።“

ይህ ጥሪ በ 2 ተሰሎንቄ ላይ ወንጌል አንደሆነ ጳውሎስ ሲያመለክት ፤

2 ተሰሎንቄ 2፥14 የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ተካፋዮች እንድትሆኑም በወንጌላችን አማካይነት ጠርቶአችኋል ።”

ፊልጵ. 1፥27  ብቻ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ፤ ይህ ከሆነ መጥቼ ባያችሁ ወይም በርቀት ሆኜ ስለእናንተ ብሰማ ፣ ለወንጌል እምነት እንደ አንድ ሰው ሆናችሁ በመጋደል በአንድ መንፈስ ጸንታችሁ እንደምትቆሙ አውቃለሁ።“

 ጳውሎስ፣ በማናቸውም ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ወንጌልን ሳያስቀድም መፍትሄና ትዕዛዝ ሲሰጥ አይታይም። በሁሉም ደብዳቤዎቹና በሐዋርያት ሥራ[2] በተደጋጋሚ ተረጋግጧል (ቀጥሎ ያለውን ሰንጠረዥ ይመልከቱ)። ደብዳቤዎቹ በማናቸውም መስክ  ሐዋርያው ለወንጌል ማዕከላዊነት ባለው የጋለና የመቆርቆር ስሜት የተሞሉ ናቸው። ይኽውም፣ ጳውሎስ አርአያ አድርጎ የሚያስተምረን፣ የትኛውም የክርስትና አስተምህሮት(doctrine) እና የሕይወት መርህ (application/ ሞራል) ወንጌልን ማዕከልና መነሽ ሊያደርግ አንደሚገባው ነው። ተገላቢጦሹ ይህም ከሕይወት መመሪያ ወደ ወንጌል ጉዞ ከቶም መታሰብ የለበትም። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቶስ ወንጌል ምስክር መሆኑ በዋነኛነት ቀርቶ የግብረገብ መመርያ መርህ ያደርግብናል።  የጳውሎስን ደብዳቤዎች ብንመለከት የመጀመሪያዎቹን ጥቂት ምዕራፎች ከተከተልን፤ ከዚያው ቀጥሎ ያሉትና ለማንበብ ውስብስብ የሚመስሉት እንደምታዎች ከቶም የማያስፈሩ ሆነው እናገናቸዋልን።   

 የወንጌሉ መግለጫ

(The description of the Gospel)

የወንጌል እንደምታ/ትእዛዝ

( the Implication/ Imperative of the Gospel)

 ገላትያ ምዕራፍ 1 እስከ  4 ወንድሞች ሆይ ፣ የሰበክሁላችሁ ወንጌል ሰው ሰራሽ አለመሆኑን እንድታውቁ እፈልጋለሁ። (1፥11)   ገላትያ ምዕራፍ 5  እና 6 1 ክርስቶስ ነጻ ያወጣን በነጻነት እንድንኖር ነው ። ስለዚህ ጸንታችሁ ቁሙ ፤ ዳግመኛ በባርነት ቀንበር አትጠመዱ። 
 ኤፌሶን ምዕራፍ 1 እስከ 3 1 ፥3በሰማያዊ ስፍራ፣ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ በክርስቶስ የባረከን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤
 ኤፌሶን ምዕራፍ4 እስከ6 1 እንግዲህ በጌታ እስረኛ የሆንሁ እኔ፣  ለተቀበላችሁት ጥሪ የሚገባ ኑሮ ትኖሩ ዘንድ እለምናችኋሁ።
 ቆላስይስ ምዕራፍ 1 እስከ 2 15እርሱ የማይታየው አምላክ አምሳል ነው፤ ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር ነው፤ 28እኛም እያንዳንዱን ሰው በክርስቶስ ፍጹም አድርገን ማቅረብ እንችል ዘንድ፣ ሰውን ሁሉ በጥበብ ሁሉ እየመከርንና እያስተማርን እርሱን እንሰብካለን ፤  29እኔም በብርታት በውስጤ በሚሰራው በእርሱ ኃይል ሁሉ እታገላለሁ፤ ለዚህ ዐላማ እጥራለሁ።
 ቆላስይስ ምዕራፍ 3 እስከ 4 1 እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሳችሁ ፣ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ በተቀመጠበት በላይ ያሉ ነገሮችን እሹ፣
 1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 1 እስከ 2
የመስቀሉ ኃይል ለሚጠፉ ሞኝነት ነው፤ ለእኛ ለምንድነው ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው ፤
 
 1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 3 እና ከዚአ በህዋላ ያሉት ፣
ጳውሎስ የቆሮንጦስ ሰዎች የጻፉለትን ጥያቄዎችና ጉዳዮች ሁሉ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ምዕራፎች በአቀረበው ወንጌል መሠረት መመለስና መፍታት ይጀምራል
  
 ሮሜ 1፥16 -11
15በሮም ለምትኖሩ ፣ ለእናንተም ወንጌልን ለመስበክ የምጓጓው ለዚህ ነው። 16በወንጌል አላፍርም፤ ምክንያቱም ለሚያምን ሁሉ ለድነት የሚሆን የእግዚአብሔር ኃይልነው፤ በመጀመሪያ ለአይሁድ ፣ ቀጥሎም ለአሕዛብ ነው።
 ሮሜ 12 -16
እንግዲህ ወንድሞች ሆይ ፤ ሰውነታችሁን ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕያው መስዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ ፤ ይሕም እንደባለ አእምሮ የምታቀርቡት አምልኮአችሁ ነው። 

 


[2] በመጀምሪያ፣ እንደ ፍልጵስዩስ ያሉ የወዳጅነት ደብዳቤዎች፣ ከጽሁፉ ዓላማ አንጻርና ከተጻፈበት ወቅታዊ አውድ የተነሳ ይህን ቅደም-ተከተል የሚከተሉ አይመስሉም፤ ይሁን እንጂ እነዚህ ደብዳቤዎች ራሳቸው በወንጌል ቃል የተሞሉ ናቸው፤ ይህ ማለት የደብዳቢው ተደራስያን/ተቀባዮች ከወንጌል የወጣ ሥነ-ምግባር ስለማይንጸባርቅባቸውና በወንጌል ላይ መመስረታቸው ለሐዋርያው ጥርጥር ስለሌለው ነው። ሆኖም ግን ከላይ ያለውን መርህ በተለየ መልኩ ይከተላሉ፤ እነዚህ ደብዳቤዎች ወንጌልን የተመረኮዙ በመሆናቸው ነው።

ቁልፉ ጉዳይ ይህ ነው! ወንጌል አጽንዖት ተሰጥቶት ተቀዳሚ ካላደረግን አድማጩ ትውልድ በአንጻሩ የሚሰማው ወይም የሚተኮረው በስነምግባር፣ አድርግ አታድርግ ፣ ሕግጋት፣ የብልሃት (ቴክኒካዊ) አሰራር ፣…… ወዘተርፈ ስለሚሆን ሳናስተውለው  እጅግ በጣም አሰቃቂ የሆነውን ኃጢአት ውስጥ ወድቀናል ማለት ነው። ጳውሎስ ይህንን አስመልክቶ የገላትያን ሰዎች ሲናገር “የማታስተውሉ” ብሏቸዋል።  አዎ፣ ሥነምግባር  እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። አዎ፣ አምልኮና ጸሎት አስፈላጊዎች ናቸው። አዎ፣ ኃላፊነት አስፈላጊ ነው። ነገር ግን እነዚህ ነገሮች ሁሉ ከወንጌል ውስጥ የሚመነጩ (ከውስጥ ወደ ውጭ የሚፈሱና የሚጨለፉ) መሆን አለባቸው። አነዚህ ሁሉ የወንጌል ፍሬዎች ናቸው። አንዘዚህን ነገሮች ያለወንጌል መፈለግ “የብርቱካንን ዛፍን ሳይተክሉ ፍሬውን መጠበቅ ነው” 

የወንጌል እውነታ በመካከላችን አውን ሳይሆን ቅዱሳን በአምልኮ ወቅት ትልቅ ስሜትና ከውስጥ የመነጨ ፍቅር አንዲያንጽባርቁ  መጠየቅ እንዴት ይቻላል? የዳኑት ለአዳናቸው የሚዘምሩት “መጽሐፉን ልትወስድ፣ ማህተሞቹን ልትፈታ ይገባሃል፤ ምክንያቱም ታርደሃል …..”  እያሉ አይደለምን ? የሰማይ ሰራዊት መዝሙር ያነጣጠረው አግዚአብሔር በልጁ በፈጸመው ሥራ ላይ ነበር። በአንጻሩ ግን መዝሙሮቻችን በክርስቶስ የድነት ስራዎች ላይ ያተኮሩ ና ከዚህ ሥራ የተነሳ የተገኘ በረከት መሆኑን ሳያውጁ – ኢየሱስን ስንፈልገው ወዲያው መጥቶ የሚያስፈልገንን የሚያደርግልን የግል  አገልጋይ እንደሆነ የሚያስመስሉ መሆናቸው አያስደንቅም። ከዚህ የተነሳ አድርገህልኛል- አክብረሀኛል; የሚሉ እልፍ መዝሙሮች አሉን። ወይም ከጌታ ጋር ያለ የቅርብ ወዳጅነት (intimacy) – ፊቱን መፈለግ- በራስ-መስዋዕትነት የሚገኝ ና ልዩ የእግዚአብሔር መገኘትን ልዩ ለሆኑ ሰዎች የሚሰጥ ይመስል አንድን ክርስቲያን የጌታ ወዳጅ እንዲሆን መጠየቅ እንዴት ይቻላል? በ2ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 4 ቁጥር 6 ላይ “በክርስቶስ ፊት የግዚአብሄር የክብሩን እውቀት ብርሃን” የሚገኘው በወንጌል አይደለምን? ከዚያና ከዚያ በኋላ ብቻ ነው አንድ ሰው በክርስቶስ ፊት  የበለጠ የወንጌልን ብርሃን የሚያየው፣ የበለጠ የእግዚአብሔርን ክብር የሚያየው።  እውነተኛ ወዳጅነት የምለው ይህንን ነው። [3] ወይም አንድ ሰው በወንጌል ውስጥ ያለውን ተስፋ ገና ያልጨበጠውን ሰው በጸሎት እንዲተጋ ሊጠይቀው እንዴት ይችላል? ( ኤፌ. 1፥17-19 ፣ ቆላ. 1፥5)።  ይህ ሲባል እነዚህ ነገሮች አግባብ እንዳልሆኑ ተቆጥረው መጣጣል የለባቸውም ። እንደ እውነቱ ከሆነ ያጣናቸው ወይም የሌሉን ጸሎት፣ ዕውነተኛ አምልኮ ፣ ጌታን በወዳጅነት ማወቅ፣ ኃላፊነት፣…የመሳሰሉትን ነው። ነገር ግን እነዚህ አስፈላጊ ነገሮች ከወንጌል ውስጥ መፍሰስ አለባቸው። ስለ አምልኮ ጥልቅ ስሜትና ከውስጥ የሆነ ፍቅር እንዲኖረን የሚያስፈልገን ወንጌል ነው።  በጸሎት ትጉ መሆን ቢያስፈልገን የመጀመሪያው ማድረግ ያለብን ወንጌል ማወቅ ነው። ይህም የሚሆነው  ወንጌል ዋነኛና ተቀዳሚ  የሆነና የታወጀ ጊዜ ነው። ወንጌላችን ከትይንት በስተጀርባ ያለ ወንጌል ሳይሆን መድረክ ላይ በግልጽ የሚንጎራደድ  ወንጌል ይሆን ዘንድ  እግዚአብሔር ይርዳን።  ወንጌልን ከበስተጀርባ (background) ሳይሆን መሆን የሚገባው ቦታ ፊትለፊት( foreground) እንናስቀምጠው ማርቲን ሉተር; የፕርቴስታንት ተሐድሶ መሪዎች ከሆኑ አንዱ  አንዲህ አለ:

“ወንጌልን እለት እለት ለራሴ አሳስበዋለሁ ምክንያቱም እለት እለት የመርሳት ዝንባሌ ስላለኝ። እንደዚሁም ወንጌልን ለማገለግለው ሕዝብ በየሰንበቱ አስተምራለሁ ምክንያቱም በየሳምንቱ ሕዝቡ የመርሳት ዝንባሌ አላላቸው።”  

ይህ ቃለ አጋኖ መሆኑን ሁላችንም አንገነዘባለን። ነገር ግን ሊናገር የወደደው ግልጽ ነው። ወንጌል በየሳምንቱ አጽንዖት ሊሰጠው የተገባ አውነት ነው። ምክንያቱም የምናደርገውንና የምንሆነው ሁሉ ስለወንጌልና ከወንጌል የተነሳ መሆን ስላለበት ነው። አሊያ መንፈሳዊነት ሀይማኖት ወይም አጥንካና አትቅመስ ይሆናል። ሰው የመካከለኛውን ስፍራ ይወስድና ክርስቶስ የሁአላውን ወንበር ይይዛል። ወንጌል ግን የክርስቶስን ሀልወት: ዙፋንና ና የመስቀሉን ሥራ  ላይ በማነጣጠር የጉባዔውን ልብና መንፈስ በመማረክ ወደ ጸጋ ያስገባናል። ቤተክርስቲያን በጋለ መንፈስ አጽንዖት ልታደርግ ይገባል። አንዳንድ ቤ/ያን በጋለ መንፈስ የምታውጀው “ስኬትን ነው”; አንዳንዶች “የስጋ ፈውስን ነው” አንዳንዶች “ታምራቶችን ነው” ለአንዳንዶች “ትንቢታዊ አምልኮ ነው”; ለአንዳንዶች በዘመናችን ያለውን “የሞራል ውድቀት ላይ ነው”

አንድ ጸሐፊ አንደዚህ ካለው ጋር በሙሉ ልብ እስማማለሁ:-

…ወንጌል ወደ መንግስቱ አሾልኮ የሚያስገባን ብቻ ከሆነና ከዚያ በኋላ ያለው የመለወጥና የማደግ ሂደት (transformation) ግን ከወንጌል በኋላ በተነደፉ ሥርዓቶችና ስትራቴጂዎች የሚካሄድ ከሆነ ያለጥርጥር የሰዎችን ትኩረት ከወንጌል ፣ ከመስቀልና ከትንሣዔ ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዲመለስ እናደርጋለን። ወዲያውም ወንጌል በጋለ መንፈስ  የምንሰብከውና የእግዚአብሔር ኃይል መሆኑ ይቀርና ለድነት ብቻ የሚያስፈልገን  መሿለኪያ ብቻ ይሆናል። በአንጻሩ …..ቴክኒካዊ አሰራሮችና መንፈሳዊ ስርዓቶች ከምንም በላይ የሚበልጡባቸውን ሰዎች  ስለዚህ ጉዳይ ብናነሳባቸው  ቅጽበታዊ የሆነ ቁጣ ሊያንጸባርቁ ይችላሉ። በእርግጥ በመስቀሉና በኢየሱስ ትንሣኤ እንደሚያምኑ ይናገራሉ። ያለጥርጥርም ያምናሉ።  ያልተመለሰው ጥያቄ ግን በጋለ መንፈስ  ያተኮሩት በምን ላይ ነው? መታመኛቸው ምንድነው? የለውጥ/የማደግ ተስፋቸው በምን ላይ ነው ያረፈው? ……የወቅቱ  መንፈሳዊ አካሄድ በተመሳሳይ መልኩ ከወንጌል እየራቀ በመጣ ቁጥር አደገኛ የአቅጣጫ ለውጥ ያደርጋል። [4]    

ስለዚህ የሀይወታችንንና የአገልግሎታችንን አቅጣጫ እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት በወንጌል በአከናወነው ሥራ ላይ ታግዘን ያንን ትልማችንን ማየትና ማሰብ አለብን። እምነት ያለሥራ ሙት እንደሆነ ሁሉ ወንጌልን ማዕከል ያላደረገ ንስሐም (confession) በተግባር ካልተደገፈ እንዲሁ ሙት ነው። የወንጌል ማዕከላዊነት ማለት ማንኛውም የምንለውና የምናደርገው ነገር ሁሉ ሙሉ በሙሉ ከወንጌል ውስጥ የፈለቀ መሆኑን  ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ እናደርጋለን ማለት ነው።  በእግዚአብሔሄር ቃል ውስጥ፣ መታዘዝ እግዚአብሔር ላፈሰሰልንና ላትለቀለቀን ጸጋው የምንሰጠው ልባዊ ምላሽ እንጂ ጸጋውን ለማግኘት የምናደርገው ጥረት አይደለም።  ስለዚህ የአንድ አማኝ ቀዳሚ ተግባር እግዚአብሔር በክርስቶስ በሰራው ሥራ እራሱን/እራሷን ሙሉ በሙሉ ማስገዛት ነው። እንዲሁም እንደቃሉ ሰባኪዎች ቅድሚያ ተግባራችን አድማጮችን በወንጌል እውነት ማጥለቅለቅ ነው ፤ ይህ እራሱ የሥነምግባር (Ethics) ጥያቄ መሠረት ነውና። በስብከቴ ውስጥ [ለመልዕክቴም መሰረት ይሆነኝ ዘንድ] በቅድሚያ የክርስቶስን  ማንነትና በወንጌል የሰራውን ሥራ ደረጃ በደረጃ ሳላሳያቸው ክርስቶስ ከሌሎች የሚፈልገውን ብሰብክ ይህ ወንጌል ሳይሆን በአዲስ ኪዳን አጠራር ሕጋዊነት (Legalism) ነው ። ይህ ኃጢአት ነው። ከኃጢአትም የበለጠ ኃጢአት !


[4] Sam Storm and Justin Taylor, eds (Editors), “ For the Fame God’s Name” : p. 165 (D.A. Carson)

© 2013 – 2014, Samson Tilahun. All rights reserved.

Like Be the first one who likes this post!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Top