Home / Portfolio / Articles / በወንጌል የተቃኘ እምነትና አስተምሕሮት!

በወንጌል የተቃኘ እምነትና አስተምሕሮት!

Posted on

ልማድና ልምድ ሁለቱም ‘ለመደ’ ከሚለው ሥርወ-ቃል የመነጩ ቃላቶች ናቸው። ሁለቱም ለሰው ልጆች አስፈላጊ ብቻ ሳይሆኑ መሰረታዊ ናቸው። ልማድ አንድን ተግዳሮት ደጋግሞ በማሰብና በማድረግ የሚገኝ ተመክሮ ሲሆን፤ ‘ልምድ’ ግን በመጀመሪያ ከዚህ ድግግሞች The-Gospel-in-Focus-amharic(ልምምድ) የሚገኝ ክሂል ነው። አንዳንድ ሰዎች የሕክምና ሙያን በልምድ ብቻ ስላካበቱ፤ ምንም እንኳ የሕክምና ሳይንሳ ረቂቅ ሐሳብ ባይገባቸውም፤ ነገር ግን በልምምድ ያካባቱት ልምድ ጥሩ ግልጋሎት እንዲሰጡ ይረዳቸውዋል። ለዚህ ብዙዎቻችን ተጠቃሚዎች ሆነናል። ነገር ግን ይህ ‘ልምድ’ በቂ አይደለም።

ከልምምድ ውጪ የሆነ ክስተት ቢገጥማቸው ያንን መቋቋም አይችሉምና፤ ምክኒያቱም በልምድ እንጂ በግንዛቤ የተገኘ ክህሎት አይደለምና! በስፖርቱም ዓለም፤ በልምምድ አንድ ሰው ጥሩ ስፖርተኛ መሆን ይችላል፤ ወይም አንድ ወታደር ጥሩ ተዋጊ ሊሆን ይችላል። ሁሉም ግን በልምድ ያካበቱት ብቃት እንጂ መረዳትን ገንዘቡ ያደረገ ብቃት አይደለም። ይህም ሆኖ ግን አንድ ወታደር የውትድርናን ስልት እንደዚሁም አንድ ስፖርተኛ የውድድሩን ሕግ ገንዝቡ በማድረግ ሲለማመድ ልምዱ ትክክለኛ ልምድ ይሆናል። አሊያ እንስሳትም እኮ ጥሩ ስፖርተኛ ይወጣቸዋል! የዝሆን ሰርከስ፤ የጦጣ አክሮባት! የርግብ ለማዳነት እጂግ ያስደንቃል! ሁሉም ግን ከልምድ የተገኘ ችሎታ እንጂ፤ ዝሆኑም ይሁን ጦጣዋ ሁለቱም የሚያደርጉትን ትርዒት ከመጫወት ያለፈ ግንዛቤ የላቸውም!

በወንጌል ላይ ያነጣጠረ/ ያተኮረ መንፈሳዊነት!

እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ በጎ ወታደር ሆነህ፥ አብረኸኝ መከራ ተቀበል። የሚዘምተው ሁሉ ለጦር ያስከተተውን ደስ ያሰኝ ዘንድ ትዳር በሚገኝበት ንግድ ራሱን አያጠላልፍም። ደግሞም በጨዋታ የሚታገል ማንም ቢሆን፥ እንደሚገባ አድርጎ ባይታገል፥ የድሉን አክሊል አያገኝም። የሚደክመው ገበሬ ፍሬውን ከሚበሉት መጀመሪያ እንዲሆን ይገባዋል። የምለውን ተመልከት፤ ጌታም በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጥህ። በወንጌል እንደምሰብከው፥ ከሙታን የተነሣውን፥ ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስብ፤ ይህንም በመስበክ እንደ ክፉ አድራጊ እስክታሰር ድረስ መከራ እቀበላለሁ፥ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም።

ብዙ ጊዜ ይህ ክፍል ሲጠቀስ ቁ. 3-7 ብቻ ነው። ነገር ግን ቁ.8፤ የቁ.3-7 ዋና ማሰሪያ ነው። ያለ ቁ.8 ከላይ ያለው ሃሳብ ትርጉም የለውም። ከነፍስ የተለየ ሥጋ ሙት እንደሆነ ሁሉ “ከአውዱ የተነጠለ ጥቅስ ነፍሰ ገዳይ ነው!” በዘመናችን ቤተክርስቲያንን እንዳታድግ አክል የሆነባት “መጽሀፍ ቅዱስን አለማወቅ” ሳይሆን በከናፍርታችን ቃሉ ሞልቶና በቃላችን ሸምድደነው ነገር ግን ጌታ ሊናገር የፈለገውን ሙሉው የሐሳብ ፍሰትና መልዕክት እንግዳ ሆኖ ማየት እጅግ የሚያሳዝን እውነታ ሆኖብናል። በሌላ አባባል ቃሉን በጠብታ መልኩ ይዘነው፤ መልዕክቱን ግን ልብ አለማለት ሲሆን፤ ይህም ቃሉን እንደ መልዕክት ሳይሆን እንደ ምትሃሐት-ቃል መውሰድ አይሆንም ትላላችሁ? ብዙ ጊዜ ጥቅስን ስንጠቅስ ወይም ሰዎች ጥቅስ ሲለዋወጡ፡ ጥቅሱ ከምዕራፉ ፍሰት ሀሳብ ተነጥሎ፤ ጠቃሹ ሊልለት የወደደውን እንዲሊለት ሲያስገድደው እንመለከታለን። በሌላ አነጋገር ጥቅሱን ከዋናው ሐሳብ ነጥለን የመናገር መብት ለቃሉ ታማኝ አለመሆን ነው። ለምሳሌ በማቴ 18፡ 15-20፡ “ሁለት ወይም ሶስት ሆናችሁ በምትሰበሰቡበት መካከል እኔ በዚያ እገኛለሁ…” ይህ ክፍል ጨርሶ ስለጸሎት አይናገርም። የሐሳቡ ፍሰት በአማኞች መካከል ስላለ መቀያየምና ይቅር ስለመባባል ነው። ኢየሱስ ጉዳይህን ለተቀየምሀው ሰው ንገረው ይለናል። ባይሰማህ በሁለት ወይ በሦስት ምስክር ፊት ውቀሰው፤ አሁንም ባይሰማህ ጉዳይህን ለሶስተኛ ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን አቅርብ። ቤተክርስቲያን እንደ ጉባኤ በመስማማት ጉዳዩን ቢያስሩት ሆነ ቢፈቱት (ይህም ሁለት ወይም ሶስት ሆናችሁ ጉዳዩን ለመፍታት እንደ ቤተክርስቲያን ብተሰበሰቡ)፤ ኢየሱስ የቤቱ ፈራጅ አብሮአችው በውሳኔ ወንበር ይቀመጣል። ቤተክርስቲያን እንደ ጉባኤ እንደ ክርስቶስ ቃል ስትዳኝ፤ ከዚህ ዳኝነት ጀርባ ራሱ ክርስቶስ ስለሚቆም (ይህ በግልጽ የክርስቶስን ቃል ሲጣረስ እንጂ አማኞች ትርፍ በሆነ ነገር ሲለያዩ አይደለም) ለዚያ ሰው ከንስሐ በስተቀር ሌላ አማራጭ የለውም። ይህ ነው የሃሳቡ ፍሰት። የዚህ ጥቅስ ቦታው በቤተክርስቲያን ግሳጼ/ እርማት (church discipline) አውድ ሥር ነው። ነገር ግን በጸሎት ሥፍራ ይህ ቢጠቀስ ይህንን በጸጋ ማለፍ ይኖርብናል። የቃሉ ባለቤት እግዚአብሔር እንጂ እኛ ባለመሆናችን። ሆኖም ግን ደግሞ ቅዱሳን የዚህን ጥቅስ ዓላማ ክርስቶስ እንደተናገርው መስማት ደግሞ ግዴታችን በመሆኑ ይህንን ስህተት እንደ ትርፍ ነገር መቁጠርም ተገቢ አይደለም። የቃሉን ሥልጣን አከብራለሁ የምንል ከሆነ፤ የቃሉን መልዕክት መስማት ሥልጣኑን ማክበር ነው። ልጆቻችን ትዕዛዛቶቻችንን በደንብ ሳይሰሙን ሲቀሩ የምናዝን ብዙዎች አይደለንም? ታዲያ ለመናፍስት አባት ቃል በርጋታና በሰከነ መንፈስ ከፍና ዝቅ እያልን የተናገርውን ለምንና እንዴት እንደተናገረ የመልዕክቱን ይዘት ማጤን፤ ‘ኢየሱስ ጌታ’፤ ‘ቃሉም ሕያው’ መሆኑን ማመን እንጂ፤ ይህ አጉል የአካዳሚ መንፈስ የተጠናወተው አንባቢ መሆናችን ነውን? አያችሁ፤ ይህ ጥቅስ ከአውዱ መነጠሉ ሳይበቃ፤ ስንጸልይ አንድ ከመሆን ሁለት ወይም ሶስት ስንሆን ኢየሱስ ይገኛል ብለን “በትምህርት” መልክ አስተምህሮት ስናደርገው፤ ራሳችንንም ሰሚዎችንም ወደ ስህተት ከተትን ማለት ነው (ይህ ክፍል ሊደርስ ያልፈለገው ድምዳሜ ላይ እንዲደርስ ስላደረግነው ነው) ከአንድ በላይ በሥምምነት መጸለይ ተገቢና ሊበረታታ የሚገባ ነው። ለዚያ ሌላ የመጽሀፍ ቅዱስ ክፍሎች አሉ፤ ይህ ዓይነት ድምዳሜ ላይ የማይደርሱ። ይህ የተሳሳተ መረዳት የተመሰረተው ከሃሳቡ በተነጠለ ጥቅስ ላይ (የጥቅሱ ሐሳብ ድምዳሜ ሌላ) ስለሆነ አስተምህሮቱ ስህተት ነው። ምክኒያቱም ኢየሱስ አንድም ብንሆን ጸሎታችንን ይሰማል ይመልስማል። የቁጥር መብዛትና ማነስ ለጸሎት እክል አይደለም ። ኤልያስም እንደኛው ሰው ነበር! አንድ ኤልያስ ጸለየ፤ እግዚአብሔርም ሰማው። ይህ አንግዲህ አንድ ቀላል ምሳሌ መስጠቴ ነው; ሆኖም ግን በዚህ ረገድ በጣም ከባባድ የሥህተት አስተምህሮት ላይ የወደቅንባቸው ጉዳዮች አሉ። ይህን ሁሉ የምለው ከላይ የጀመርነው የሐዋርያው አደራ ታላቅነት ለማሳየት ነው። የዚህን የወንጌል ታላቅ አደራ ማየት የምንችለው የጥቅሱን ሙሉውን የሐሳብ ፍሰት የተረዳን እንደሆን ብቻ ነው። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ አሁን ባነበብነው ክፍል ላይ ወረድ ብሎ፡ መረን ከለቀቀ አስተምህሮት ራሱን አንዲያነጻ ሲመክረው፡

በትልቅም ቤት የእንጨትና የሸክላ ዕቃ ደግሞ አለ እንጂ የወርቅና የብር ዕቃ ብቻ አይደለም፥ እኵሌቶቹም ለክብር፥ እኵሌቶቹም ለውርደት ይሆናሉ፤ እንግዲህ ማንም ራሱን ከእነዚህ ቢያነጻ፥ ለክብር የሚሆን የተቀደሰም ለጌታውም የሚጠቅም ለበጎም ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ዕቃ ይሆናል።

ይህን ስል እባካችሁ ተወደዳችሁ ቅዱሳን፤ በትችትና በእብሪት መንፈስ አንዳልሆነ እንድታውቁልኝ እወዳለሁ። ይህን የምለው እንደ እግዚአብሔር አገልጋይ እሬትን እሬት ለማለት፤ ገለባና ስንዴን ለመለየት ያህል ብቻ ነው። ይህን ስጽፍ ከጥቂት ዓመታት የጀመረ አስከ አሁን ድረስ ያለ የውስጥ ለቅሶ ይዤ እንጂ በሌላ መንፈስ አይደለም። ለማነጽ እንጂ ለመኮነን አይደለም። ለምሳሌ ያህል፡- ኢየሱስንና ዲያብሎስን የለየ አጥር ይህ ነበር። ትዝ ይላችሁ እንደሆን ዲያብሎስ ለኢየሱስ ከመዝሙር 91 ቃል በቃል መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ፥ ወደ ታች ራስህን ወርውር አለው። ችግሩ የመዝሙሩ መልእክት በእግዚአብሔር መግቦት ጥበቃ በእምነት ስለማረፍ እንጂ ስለጀብደኝነት አይናገርም። “በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምልካ ጥላ ሥር ያድራል…” ነገር ግን ዲያብሎስ የመዝሙሩን የመታመን መልዕክት ወደ መፈታተን ለወጠው። ይህን ያደረገው ታድያ የጠቀሰውን ክፍል ከጠቅላላው የመዝሙር 91 ሐሳብ ለይቶ የጥቅስ ጠብታ ለኢየሱስ በመስጠት ነው። በዚህ መልኩ ዲያብሎስ ታድያ ቢፈትነን ምን አልባት ፈተና አንደሆን አናውቅ ይሆንን? እንዲያውም ጌታ ተናገረን እንል ይሆንን? ምክኒያቱም ብዙ ጊዜ መጽሀፍ ቅዱስን የምናውቀው በጠብታ መልክ ስለሆነ ነው። ትዝ አይላችሁም ጥቅስ በሚታደልበት ዘመን! በጥቅስ ፈንታ መልክቱ ቢታደለን በወደድሁ! ለምሳሌ ያህል ከጥቂት አመታት በፊት አንድ አገልጋይ ለጉባኤው ምርኮ ፈጠነ፥ ብዝበዛ ቸኰለ!” እያስባለ ጉባኤውን ሲያስደጋግም፤ በልቤ ግን ጩሀት ነበር! ምክኒያቱም ለቃሉ አክብሮት የሚጀምረው ቃሉ የሚለውን በማድመጥ ነው! ባርነታችን በመጀመሪያ ደረጃ ለቃሉ መሆን አለበት። ይህ ቃል የተጻፈው በኢሳያስ ምዕራፍ 8 ላይ ሲሆን መልዕክቱም የእግዚአብሔር ህዝብ የነበረው ኤፍሬምና ደማስቆ የመከሩት ሴራ አንደሚፈርስና ራሱ እግዚአብሄር በቁጣ በሕዝቡ ላይ እንደሚገለጥ፤ የቃል ኪዳኑ ሕዝብ ኤፍሬም እንደ አሕዛብ በአሶር እንደሚማረክ፤ ይበዘበዝ ዘንድ ይህ ቁጣ እንደማይዘገይ ሲናገር ለነብዩ ለኢሳያስ በምስክሮች ፊት በሰሌዳ ላይ ጻፍ ይለዋል፤ እንደዚሁም ደግሞ ወንድ ልጅ ወልዶ ስሙን “ምርኮ ፈጠነ፥ ብዝበዛ ቸኰለ” ይለው ዘንድ ይታዘዛል። ይህ ለምህረት የሚለቀስበት ቃል እንጂ ሀሳቡ ተለውጦ የድል ቃል ሊሆን አይገባም። ለምን? ምክኒያቱም የዚህ ቃል ትርጉም መለወጥ ስለሌለበት ነው! ነገርግን ሰባኪው ከሌላ ሥፍራ መልዕክቱን የሚያንጸባርቅለት ቃል በጥንቃቄ ቢፈልግ ጥሩ በነበር። ስለዚህ ሰባኪውም ጉባኤውም ቃሉን አላከበሩም ማለት ነው!ጥንቃቄና ትኩረት ለቃሉ ይዘትና መልዕክት እጅግ ያስፈልጋል። ጌታ ጸጋውንና ማስተዋሉን ያብዛልን::

ስለዚህ ወደ ጀምርኩት ሀሳብ ልመለስና፤ ለጢሞቴዎስ ሶስት ምሳሌዎችን በዘይቤአዊ አነጋገር ይሰጠዋል፤ የወታደር፤ የስፖርተኛና የገበሬ ዘይቤ። ወታደር መዋጋቱ ብቻ አይደለም፤ ሲዋጋ ለጦር ያስከተተውን ደስ ያሰኝ ዘንድ መዋጋት አለበት፤ የጌታውን ፈቃድ ይገነዘብ ዘንድ ያስፈልገዋል ማለት ነው! ስፖርተኛም የድሉን አክሊል እንዲጎናጸፍ የጨዋታውን ሕግ መገንዘብ አለበት! ስለገበሬ ሲናገር ግን ዘይቤውን ይለውጠዋል። ገበሬ ደግሞ በግብርና ‘መድከም’ አለበት። ሰነፍ ገበሬ አለ። ጎበዝ ገበሬ አለ! ጥሩ ገበሬ በመዝራት፤ በማረም፤ ወስኖ በመቀየስ ‘ይደክማል። አነዚህ ሦስት ምሳሌዎች ታዲያ ከቁ. 8 ከተለዩ የመለእክቱ ይዘት “ባዶ ሙላ” ይሆንና “በርትተን እንዋጋ” “ድልን እንያዝ” “ደክመን እንዝራ” ይሆናል። ይህም ይዘቱ ሰባኪው አሊያም አንባቢው ትኩረቱ ልምምዱ ላይ ይሆንና የልምምዱ አላማ ግን አንባቢው ለወቅቱ ሊል የፈለገውን በባዶ ሥፍራ ይሞላዋል። ለምሳሌ፦ ለስኬታማ ሕይወት መትጋት! በአገልግሎት መትጋት! ለአላማ መትጋት! ጌታን ለማስደሰት መትጋት! የእግዚአብሔርን ሐሳብ ለመጨበጥ መትጋት ወዘተ…እነዚህ ሁሉ እውነት ናቸው። ነገር ግን ሁሉም የዚህ ምንባብ መልእክቶች አይደሉም።፡ተመለከታችሁ ቁ.8 የዚህ ትጋት ይዘት ምን እንደሆነ ጸሐፊው ጳውሎስ ለመንፈሳዊ ልጁ ለጢሞቴዎስ የእርሱን ፈለግ እንዲከተል ይመክረዋል!

“በወንጌል እንደምሰብከው፥ ከሙታን የተነሣውን፥ ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስብ፤  ይህንም በመስበክ እንደ ክፉ አድራጊ እስክታሰር ድረስ መከራ እቀበላለሁ፥ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም።”

እንደ ወታደር ፤ እንደ ስፖርተኛና እንደ ገበሬ የሚተጋው፤ ለሌላ ነገር ሳይሆን ጢሞቲዎስ ትኩረቱንና ስብከቱን፤ አገልግሎቱንና ሕይወቱን “ከሙታን የተነሣውን፥ ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን” እንዲያስብ ነው። ይህም ይዘት የሚታወጀው፤ “በወንጌል አንደምስብከው” በማለት ይነግረናል። ከዚህ የተነሳ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሯል። ጢሞቴዎስም እግዚአብሔር ማስተዋልን እንዲሰጠው የሚጸልይለት፤ በሁሉ ነገር “ኢየሱስ ክርስቶስን” እንዲያስብ ነው። እርሱም ከሙታን የተነሳ፤ ከዳዊት ዘር የሆነ ነው። ጢሞቴዎስ ስደትን ልመደው! መከራን ልመደው፤ ሐሰተኛ መባልን ልመደው! ስለ ክርስቶስ ወንጀለኛ መባልን ልመደው። በገዛ ድካምህ እለት እለት እንደ ስፖርተኛ እንደ ገበሬ፤ እንደ ወታደ መኖርን ልመደው! ነገር ግን የዚህ ሁሉ ዓላማ የሆነውን “ወንጌልን” አትልመደው! “ከሙታን የተነሣውን፥ ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስብ” “ወንጌሌ ይሔ ነው!!” [አዲሱ መደበኛ ትርጉም] ወንጌልን መካከለኛ፤ ዋነኛና መጀመሪያ አድርግ! አስበው!

ዋነኛው ነገር፤ ዋነኛውን ዋነኛ ማድረግ ነው!

እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን ከሁሉ በፊት [ዋነኛ የሆነውን] አሳልፌ ሰጠኋችሁ እንዲህ ብዬ። መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፥ ተቀበረም፥ መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ፥

ለሰው ጥሩም መጥፎም የሆነ ነገር ቢኖር ‘ልማድ’ ነው፡ አንዳንድ ነገሮች መለመድ አለባቸው፤ አንዳንድ ነገሮች ግን ሲለመዱ እጅግ በጥንቃቄ መሆን አለበት። አለመልመድ አይቻልምና! እስኪ የሁለት ወጣት ሴትና ወንድ የፍቅር ጉዞ እንመልከት። በመጀመሪያ ቀኑን ሙሉ እርስበርሳቸው የተሳሰባሉ! ፍቅራቸውን ሊለምዱት አይችሉም! ትንሽ ይቆይና ተጫጭተው ሰርግ ሲደግሱ፤ ትኩረታቸው ‘በሰርጉ’ ላይ ይሆንና ፍቅራቸው ይለመዳል! ከዚያ ከተጋቡ በሁላ በጫጉላ ሽርሽር ጊዜ ያ ፍቅር ጫፍ ይደርሳል! ሁሉቱም ሳያውቁት ፍቅራቸው ሁለተኛ ደረጃ ይሆንና ትኩረቱ የሰርጉን ወጪ ዕዳ ለመክፈል ‘በሥራ’ ላይ ይሆናል። በተጨማሪ ገና የትዳር ጎጆ ሦስት ጉልቻ በመጣል ላይ ስለሆነ ቤት፤ መኪና፤ አስፈላጊ ቁሳቁስ…ላይ ይሆናል። ይህ ሁሉ አስፈላጊና ተገቢ ነው። መለመድ የማይገባው “ፍቅራቸው” ግን ይለመዳል። ይዋደዳሉ! ግን ፍቅራቸውን ለምደውታል፡፡ በዚህ ግርግር ልጅ ይመጣል! ደግሞ ሌላ ቆንጆ ልጅ…ከዚያ ልጆች ማሳደግ የወላጆቹ ዋነኛ ትኩረት ይሆንና ይህን ሁሉ ወደመሆን ያመጣው “የመጀመሪያው ትኩስ ፍቅር” ይዳፈናል! የብዙ አሜሪካን ባልና ሚስት እንደሚሆኑት፤ ልጆች አድገው ቤት ሲለቁ፤ ጡረታ ሲመጣ! በመሃል ያለፈው ዘመን ከእንቅልፍ የመንቃት ይሆንባቸዋል! በዚህ ምስሌ ውስጥ ሆነን እስኪ ኢየሱስ ለኤፌሶን ቤተክርስቲያን የተናገረውን እንመልከት፡

“ሥራህንና ድካምህን ትዕግሥትህንም አውቃለሁ፤ ክፉዎችንም ልትታገሥ እንዳትችል፥ እንዲሁም ሳይሆኑ። ሐዋርያት ነን የሚሉቱን መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው አውቃለሁ፤  ታግሠህማል፥ ስለ ስሜም ብለህ ጸንተህ አልደከምህም።  ዳሩ ግን የምነቅፍብህ ነገር አለኝ የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃልና። እንግዲህ ከወዴት እንደ ወደቅህ አስብ ንስሐም ግባ የቀደመውንም ሥራህን አድርግ፤ አለዚያ እመጣብሃለሁ ንስሐም ባትገባ መቅረዝህን ከስፍራው እወስዳለሁ።”

የኤፌሶን ቤተክርሲቲያን ዳተኛ አልነበረችም; ከላይ እንዳየነው ፍቅረኛሞች፤ ትኩረቷን በድካሟ ላይ አድርጋ፤ ዋነኛውን ነገር ዋነኛ ማድረግ ተሳናት! የደከመችበት ጉዳይ በጣም ወሳኝ ነበር! የዘመናችንም ችግር ነው! በዚህ ሁሉ ግብግብ እጅ ሳትሰጥ የተዋጋችው የኤፌሶን ቤተክርስቶያን ስለዚህ ሁሉ ስትመሰገን፤ ነገር ግን በዚህ ሁሉ ትኩረቷን ፍልሚያው ወስዶባት “የመጀመሪያውና ዋነኛውን” ወደ ጎን አደረገች። ማስጠንቀቂያው “ንስሐም ባትገባ መቅረዝህን ከስፍራው እወስዳለሁ” ነበር። ይህም በራዕይ ትእምርታዊ አነጋገር፤ መቅረዙ ቤተ ክርስቲያንን ያመለክታል። ማስጠንቀቂያው ሽልማትህን ታጣለህ አይደለም። ያለ መጀመሪያው ፍቅር መቅረዝህን ታጣለህ። ይህም የኤፌሶንን ጉባኤ የክርስቶስ ጉባኤ (ቤተክርስቲያን) እንዲሆን ያደረገውን የመጀመሪያውን ዋነኛ ፍቅር ወደ ጎን ስላደረጉ ነበር። ጉባኤው ቤተክርስቶያን መሆኑ ይቀራል ማለት ነው!

ጳውሎስም ለቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን ከላይ ባየነው ክፍል፤ ወንጌል ዋነኛ እንደሆን ይነግራቸዋል! ትኩረታችን በዚህ በዋነኛው ነገር መሆን አለበት። ይህም ቤተክርስቲያን ሁለንተናዋ የመነጨው ከወንጌል መሆኑ ነው። ይህ ቅደም ተከተል አይደለም። በፍጹም! ዋነኛነቱ የተመሰረተው ለምሳሌ ያህል ለፊልጲስዩስ ቤተክርስቲያን እርስ በርስ ስለመዋደድ ሐዋርያው ሲጽፍ፤ “ተዋደዱ” ማለቱ በቂ አልነበረም። ሲዋደዱ ግን በወንጌል አማካይነት የተገለጠውን ዓይነት ፍቅር አንዲሆን ሲመክራቸው፤ በቅዱሳት መጻህፍት ከተጻፉት በጣም ውብ ከሆኑት ክፍል ፊልጵስዩስ ምዕራፍ ሁለትን ጻፈ። የጻፈበት አላማ ግን “በነገራችን ላይ ኢየሱስ ማን ነው?” የሚለውን ለማስተማር ፈልጎ አልነበረም (ይህ ቢሆን ችግር ነው ለማለት ፈልጌ አይደለም)። ተዋደዱ ሲል ይህ መዋደድ ከወንጌል ተጨልፎ የወጣ መሆኑን ሲያሳይ፡

ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤  እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ

ይህን ብሎ አላበቃም፤ ምንጩ ግን

“በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን።  እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥   በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ።”

ከወንጌል ቃል ዶፍ የተከተለ ትእዛዝ

ስለዚህ ትልቁ ችግር ይህ ነው። ስብከታችን ይሁን ዝማሪያችን የወንጌሉን ቃል ለምዶአል። ይህም ሁላችንም ገና ወንጌል ሲባል ስለለመድን ውስጣችንን አይቀሰቅሰንም። ውስጣችንን ፈንቅሎ የሚቀሰቅሰን ሌሎች ነገሮች እንዳይሆኑብን መጠንቀቅ ይኖርብናል፤ ግን ደግሞ እንደነዚህ አይነት ግሳጼ ስንሰማ “ወንጌልማ ዋነኛ ነው!!!!!” እንላለን። ችግሩ አያችሁ፤ ወንጌልን ለምደነው፤ ደስታችንና አጥንት ትምሕርታችን ግን ያነጣጠረው በሌሎች ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ሆኗል። በሌሎች ርዕስ-ጉዳይ ላይ መነጋገር ችግር ነው እያልኩ ሳይሆን፤ እነዚህ ረዕሰ ጉዳዮች በቀጥታ በወንጌሉ ቃል አስተርእዮ አለመቃኘታቸው ነው። ከዚህ የተነሳ መረዳታችን ሆነ ትምህርታችን “አድርግ አታድርግ፤ ቅመስ አትቅመስ” ላይ ይሆናል! ጸጋ ያለ ክርስቶስ አይለቀቅም! ሁልጊዜም ጸጋና መንፈሱ የሚከተሉት ከወንጌሉ ቃል ጀርባ ነው። ስለዚህ ለምሳሌ ያህል፦ ባል ሚስቱን እንዲወድ ቢታዘዝ፤ ይህ ትእዛዝ “አትንካ አትቅመስ” ሊሆን ይችላል ወይም የጸጋ ትእዛዝ ሊሆን ይችላል። እንዴት? በመጀመሪያ “ውደድ!” ተብሎ ከማዘዝ በፊት፤ አዛዡ:

  • እንዴት እግዚአብሔር ሐጥያተኞችን በማዳን ዘላለማዊ ክብሩን ሊገልጽ የወደደበትን አሰራር ማስረዳት፤
  • ይህም የአባቱን ፈቃድ ሊያደርግ መሲህ ይሆን ዘንድ ወልድ በዳዊት ቤት እንዴት እንደተወለደ፤
  • ደግሞም  የህዝቡን ሐጥያት በእንጨት ላይ ስለአባቱ ፈቃድና ስለወደዳቸው ወንድሞቹ ፍቅር “ራሱን ዝቅ አድርጎ” መገለጡ
  • ከሙታን በመነሳቱ ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአባቱ: መዋረዱንና መስዋእቱን በማክበር የመለኮት ልጁን መሲሐዊ ንጉስ አድርጎ መሾሙ…ወዘተ..

ይህንና መሳይ ሚስጢር በየሳምንቱ ካብራራ በኋላ፤ ይህ ባል፤ በክርስቶስ ትህትና ሲመሰጥ፤ ራስ-ወዳድነትን ገንዘቡ ባላደረገ በክርስቶስ በማይነጥፍ ፍቅር ሲማረክ፤ በዚህ ሁሉ ማስተዋሉ ከመታወቅ በላይ የሆነው የአብ ጥበብ ሲሰርጽ፤ በአጭር ቃል ይህ “ሚስትህን ውደዳት” የሚለው ትዕዛዝ ከወንጌሉ ቃል ዶፍ በኋላ ሲከተል፤ “ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን እንደወደዳት” የባል ትኩረትም ክርስቶስ እርሱን የወደደበት ጸጋ፤ አብ እርሱን የወደደበት ፍቅር፤ ቅዱሱ መንፈስ እርሱን የወደደበት መገኘት ላይ ሲተከል! ምን ያህል ኢየሱስ ወደ ራሱ ጥቅም ሳይመለከት የአባቱን ክብርና የሐጥያተኞችን መዳን ዓላማው ያደረገበት ዓላማ፤ ለዚህ ባል ዓላማው ሲሆንለት፤ በዚህ ከተረዳው የወንጌል ቃል ዶፍ ተከትሎ የሚወጣው ጮራ “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ” ነፍሱን ሰንጥቆ ፍቅሩ እለት እለት ሲያንበረክከው፤ ውደድ የሚለው ትእዛዝ ከጸጋ ሐይል ጋር ስለሚከተል ትእዛዙ ሕይወት ይሆንለታል። ከወንጌል ቃል ዶፍ የተከተለ ትእዛዝ፤ አንድ ሠዓሊ ወደ መስክ ወጥቶ መልከዓ ምድር እንደሚስል ሰው ነው። ዛፍ እያየ ዛፍ ይስላል።፡ተራራ እያየ ተራራ ይስላል። በወልድ ላይ ያረፈውን የአብን የአንድያ ልጅ ፍቅር በወንጌል አማካይነት እያየ፤ ያን ልዩ ሕብረትና አንድነት ከእርሱ ጋር አንድ-ሥጋ ትሆን ዘንድ በተሰጠች ስጦታው:- ባል ሚስቱን ክርስቶስ ቤተክርስቶያንን የወደደበትን ፍቅር እያየ ይወዳታል! ሲወዳት እርሱ ከእርሷ የሚያገኘውን እያሰበ ከወደዳት ፍቅሩ በአጭር ቃል የአህዛብ ፍቅር ነው። ራሴን በዚህ የወንጌል ዶፍ ማኖር እስክማር ይህ ፍቅር ከብዶብኝ የኖርኩበትን ዘመን አለመጥቀስ ግብዝነት ይሆንብኛል! ሐላፊነትን ብወስድም ነገር ግን ለዚህና ለመሳሰሉት ችግሮቻችን በክርስቶስ ፊት ተጠያቂዎች እኛ “የአገልጋይነትን” ማዕረግ የጫንን ሰዎች ይመስለኛል! ሐላፊነታችን የእግዚአብሔርን ሕዝብ በወንጌል ዶፍ ማጥለቅለቅ ነበር።  ለዚህ ነው ጸጋ በቤቱ ላይ ያነሰው። ጸጋ ‘ነገር’ አይደለም፤ ጸጋ ክርስቶስ ነው። ጸጋ በስሉሱ አምላክ የተገመደ ልዩ ቀመር ነው! ይህ ከአብ-ወልድ-መንፈስ ቅዱስ በስተቀር ማንም የማያውቀው ቀመር ነው። ጸጋ አብ በሚወደው ወልድ የተዋረደ ሞት የተገኘ ቤዛነት እንጂ በሰዎች ጥረትና ተቆጣጣሪነት የሚገኝ አይደለም። ጸጋ ከአብና ከወልድ ዘንድ በሚወጣው በሕያው ቅዱስ መንፈስ ሐይል የሚገኝ እንጂ በሰዎች ብልሀትና ቴክኒክ ወይም ደስ-ደስ በሚል አጽናኝ ቃል የመነጨ አይደለም! በቀኑ መጨረሻ ጸጋንና ቴክኒክን መለየት አለበት።

ይህ እጅግ የማከብራችሁ በክርስቶስ የተወደዳችሁ ወገኖች፤ የሞትና የሕይወት ጉዳይ ነው። የወንጌል እውነት እንደ ካፊያ መሆኑ ቀርቶ በዘመናችን የወንጌል መረዳት እንደ ዶፍ ይሆንል ዘንድ ጸሎቴና ልምናዬ ነው! ይህንን ብሎግ የምጽፈው የወንጌልን ቃል አንደ ዶፍ በላያችን ይወርድብን ዘንድ ብቻ ነው። ምክኒያቱም ዶፉን ተከትሎ የሚወጣ የብርሃን ጮራ አለና ይህም ጮራ የሚፈነጥቀው በክርስቶስ ላይ ነው! አይናችን ሲበራ -አብርሆት ሲሆንልን- ክርስቶስን እናያለን! እርሱን አይተን እንለወጣለን። እርሱን ማየት ደግሞ ያለው በወንጌሉ እውነት ላይ ነው “በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን እንዲሰጥ በልባችን ውስጥ የበራ። በጨለማ ብርሃን ይብራ ያለ እግዚአብሔር ነውና።” ሙሉውን ሐሳብ ተመልከቱ፦

ነገር ግን የሚያሳፍረውን ስውር ነገር ጥለናልና በተንኮል አንመላለስም የእግዚአብሔርንም ቃል በውሸት አንቀላቅልም፤ እውነትን በመግለጥ ግን በእግዚአብሔር ፊት ለሰው ሕሊና ሁሉ ራሳችንን እናመሰግናለን።  ወንጌላችን የተከደነ ቢሆን እንኳ የተከደነባቸው ለሚጠፉ ነው።  ለእነርሱም የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፥ የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን አሳብ አሳወረ። ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታ እንደ ሆነ እንጂ ራሳችንን አንሰብክምና፥ ስለ ኢየሱስም ራሳችንን ለእናንተ ባሪያዎች እናደርጋለን። በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን እንዲሰጥ በልባችን ውስጥ የበራ። በጨለማ ብርሃን ይብራ ያለ እግዚአብሔር ነውና።  ነገር ግን የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን”


በዚህ ዙሪያ በየሳምንቱ ለመጻፍ እሞክራለሁ! ርዕሶቹም:

ከወንጌል ጋር የሚስማማ…! ከእኔ የሰማሀውን…! ጤናማ እምነት…! ጤናማ ሕይወት…!ጤናማ አስተምሕሮት…!

© 2013 – 2014, Samson Tilahun. All rights reserved.

Like Be the first one who likes this post!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Top